Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመጀመርያው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በኢትስዊች አማካይነት አገልግሎቱን ሊያቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመጀመሪያው የግል የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማግኘቱን ከዚህ ቀደም ያስታወቀው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪስ በንግድ ባንኮች፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በአነስተኛ የፋይናንስ ድርጅቶች ባለድርሻነት የተቋቋመው ኢትስዊች ባለድርሻነት በማረጋገጡ አገልግሎቱን በኢትስዊች ብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ሊያቀርብ ነው፡፡

ካቻ ከኢትስዊች የገዛውን የአባልነት ድርሻ መሠረት አድርጎ የኢትስዊች አባል ከሆኑ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች የክፍያ ሥርዓት አሳላጮች ጋር በቀጥታ በመተሳሰር፣ ማንኛውንም ክፍያ መቀበልና ማስተላለፍ የሚያስችል የግንኙነት ፕሮቶኮል በኢትስዊች በኩል የሚመቻችለት መሆኑ ተገልጿል።

በ13 ባለአክሲዮኖች በ200 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል መቋቋሙ የተገለጸው ካቻ፣ አስፈላጊ መሥፈርቶችን በማሟላት ከባንኮችና ከፋይናንስ ተቋማት በመቀጠል የኢትስዊችን አክሲዮን በመግዛት ቀዳሚው የክፍያ ሰነድ አውጪ ድርጅት አባል መሆኑን አስታውቋል፡፡

የካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል አገልግሎት የማርኬቲንግና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ አቶ ይገርማል መሸሻ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ካቻ የኢትስዊችን አክስዮን በመግዛት የባለቤትነት ድርሻ አግኝቷል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ የተሰጣቸውን የሞባይል ገንዘብ አንቀሳቃሽነት ፈቃድ ባገኙ ማግሥት የኢትስዊች አባል የመሆን እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስረዱት አቶ ይገርማል፣ ይህም ካቻ በይፋ ወደ ገበያ ከመግባቱ በፊት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ለመግባት ከመፈለግ ዕሳቤ የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ካቻ ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠው ፈቃድ የሞባይል ሒሳብ መክፈት፣ በወኪሎችና ሌሎች አማራጮች በመጠቀም ገንዘብ ገቢና ወጪ ማድረግ፣ አነስተኛ ቁጠባ፣ የንብረት መያዣ የማይጠየቅባቸውን አነስተኛ ብድሮች፣ አነስተኛ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች፣ የቀጥታ ክፍያዎች፣ ዓለም አቀፍ ሐዋላና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችለው መሆኑ ከዚህ ቀደም ተገልጾ ነበር፡፡

እንደ አቶ ይገርማል ገለጻ፣ የኢትስዊች አባል ለመሆን ሁለት ዓይነት አማራጮች ቀርበዋል፡፡ አንደኛው የኢትስዊች የተፈቀደ ካፒታል 900 ሚሊዮን ብር ስለደረሰ ከዚህ ውስጥ አንድ ተቋም በተናጠል እንዲገዛ የተፈቀደለትን ካፒታል ጣሪያ ማለትም 40.8 ሚሊዮን ብር መያዝ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የፋይናንስ ተቋማት ካፀደቁት የተከፈለ ካፒታል አምስት በመቶ በመክፈል ባለድርሻ መሆን እንደሚችሉ ተገልጾ ካቻም በሁለተኛው አማራጭ ባለድርሻ ለመሆን በቅቷል፡፡

ካቻ ከኢትስዊች ጋር በመጎዳኘቱ የሁሉንም ባንኮች ኤትኤሞች በማስተሳሰር በአንድ ካርድ በሁሉም ባንኮች ኤትኤሞች መጠቀም የሚያስችሉ አገልግሎቶች፣ የክፍያ መፈጸሚያ መሣሪያ (ፖስ) በመጠቀም የሚደረግ ግብይት፣ የክፍያ ካርዶችን ለገበያ ማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ካቻ ከራሱ በተጨማሪ የሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ወኪሎች የሚያቀርቡትን አገልግሎት ለደንበኞቹ እንዲቀርብ የሚያስችለው አገልግሎት የሚያገኝ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከኢትስዊች ጋር ከመጎዳኘት ጎን ለጎን ትስስር በጀመረባቸው ተቋማት የቅድመ አገልግሎት የሙከራ ሥራ እየተገበረ እንደሚገኝ የተገለጸው ካቻ ደንበኞችን ሒሳብ ማስከፈት፣ ገንዘብ ወጪና ገቢ ማድረግ፣ በግለሰቦች መካከል የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር፣ የግብይት ክፍያ መፈጸም የሚያስችሉ አገልግሎቶች መጀመሩ ተጠቁሟል፣ ወደፊት የውጭ ሐዋላ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ሙከራ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሙከራ ሒደት ውስጥ የተገኙትን ውጤቶች ገምግሞ የሚሰጠውን ግብረ መልስና ፈቃድ ተከትሎ መደበኛ አገልግሎት እንደሚጀምሩ የተናገሩት አቶ ይገርማል፣ የሙከራ ሥራው ከዚህ በኋላ ከሁለት ወራት ያልበለጠ ጊዜ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡

ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል አገልግሎት ኢትስዊችን በይፋ መቀላቀሉን አስመልክቶ ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ከፍተኛ የተቋሙ ኃላፊዎች በተገኙበት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።

ኢትስዊች እ.ኤ.አ. በ2011 በሁሉም ባንኮች፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በተወሰኑ አነስተኛ የፋይናንስ ድርጅቶች ባለድርሻነት በዋናነት በሁሉም የክፍያ ሥነ ሥርዓቶች የእርስ በርስ ተናባቢነት እንዲኖር፣ ብሔራዊ የክፍያ ካርድ ሥርዓት ፈጥሮ ለመተግበርና የጋራ የክፍያ ሥርዓት መሠረተ ልማቶችን ለማበልፀግ የተቋቋመ ብሔራዊ የክፍያ ስዊች መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች