በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙና ምሁራን ተብለው የሚመደቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ለረዥም ዘመናት የቆዩትንና የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና ለሚጫወቱት አገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ዕውቅና ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ሁለገብ አዳራሽ ለ14ኛ ጊዜ ባዘጋጀው የዘርፈ ብዙ የጥናት መስኮች ሴሚናር ላይ ነው፡፡
በሴሚናሩ ላይ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ጥናት አቅራቢዎችን ጨምሮ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ የግልና የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተጠኑ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
በሴሚናሩ ወቅት አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ሰላምንና ፀጥታን ከማስከበር አኳያ የተጫወቱት ሚና፣ በተለይም በጉራጌ ዞን የማረቆና መስቃን አካባቢዎችን ተሞክሮ በመውሰድ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመጡትና በመድረኩ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት የታሪክና አንትሮፖሎጂ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ተስፋዬ፣ አገር በቀል የግጭት መከላከያዎች ለሰላም፣ ለደኅንነትና ለዘላቂ ልማት የሚኖራቸውን አበርክቶ ከዚህ ቀደም በጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር አያይዘው ጥናት አድርገዋል፡፡
በዞኑ መስቃንና ማረቆ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እንዲሆንና እንዲቀጣጠል ያደረጉት ምክንያቶች እንደነበሩ በጥናታቸው እንደለዩ ያስታወቁት አቶ ዮሐንስ፣ አንደኛው በኢመደበኛነት የተደራጁ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሕወሓትን ደጋፊ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው ብለዋል፡፡ ነገር ግን በመስቃንና በማረቆ መካከል ያሉ አገር በቀል ግጭት መፍቻ መንገዶችና የአገር ሽማግሌዎች ችግሩን መፍታት ስለመቻላቸው ገልጸዋል፡፡
በሁለቱም አካባቢዎች በኢመደበኛነት የተደራጁ ወጣቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ የተማሩና ማኅበረሰቡ የሚሰማቸው የሚባሉ እንደነበር ያስረዱት አቶ ዮሐንስ፣ ከዚህ በሻገር በፖለቲካ ቡድኖች በአንዳንድ ባላሀብቶች አማካይነት ላለፉት አራት ዓመታት የቆየውን የአካባቢዎቹን ግጭት ማኅበረሰቡ ራሱ ባበጀው የግጭት አፈታት ሥርዓት ዕርቅ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ሃፋንዱሚቻ (የጥላ ሸንጎ) በማረቆ፣ ‹‹ፈራገዘኝ ሴራ›› በመስቃን በአገር በቀል የግጭት አፈታት የአገር ሽማግሌዎች ከቤተሰብ አንስቶ እስከ ብሔር የሚደርሱ ግጭቶችን እንደሚፈቱ የተገለጸ ሲሆን፣ እየተጫወቱት ካለው ሚና አንፃር የችግር መፍቻ ዘዴዎቹ ለመንግሥትም ትልቅ ድጋፍ የሚሰጡ ስለመሆናቸው የታሪክና የአንትሮፖሎጂ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
በየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ የተማረ ነው የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል አዲስና የተለየ ነገር ማምጣት ባይችል እንኳን፣ ለረጅም ዘመናት የቆየውን አገር በቀል የግጭት አፈታት መንገድና ተቋማት ጠብቆ መልሶ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ሚና መጫወት እንዳለበት አቶ ዮሐንስ አሳስበዋል፡፡
የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የዘርፈ ብዙ ጥናት መስኮች ሴሚናር የማኅበረሰብ ሥራ ፈጠራ በኢትዮጵያ ያለውን አሁናዊ መልክ የዳሰሱ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የጀማሪ የሥራ ፈጠራ ተቋማት የካፒታል መዋቅርና መሰል ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው መሥራችና ፕሬዚዳንት ወንደሰን ታምራት (ረዳት ፕሮፌሰር) በሴሚናሩ ላይ እንደተናገሩት፣ ተቋማቸው ላለፉት 13 ተከታታይ ዓመታት የተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የምርምር ፎረሞችንና ሴሚናሮችን አካሂዷል፡፡ በተጠቀሱት ቀናት የተደረጉት ፎረሞችና ሴሚናሮች ዓላማ ምርምርንና ፈጠራን ለማበረታታትና በተማሪዎችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባሉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ በልማት አካላት የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡