Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት ያቆሙ ባንኮች ሥራ እንዲጀምሩ አሳሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሥር የሚገኘው የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር፣ የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት ያቆሙ ባንኮች ሥራ እንዲጀምሩ አሳሰበ፡፡

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ምላሽ ወርቅዓለም በከተማዋ ቅርንጫፍ ላላቸው ዘጠኝ ባንኮች በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹ታሪካዊ ስህተት ፈጽማችኋል፤›› ሲሉ በፀጥታ ችግር ሳቢያ የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት ያቆሙ ባንኮችን ወቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አቢሲኒያ፣ ዳሸን፣ አዋሽና አንበሳ ባንኮች ደብዳቤው ከተጻፈላቸው መካከል ናቸው፡፡

ባንኮቹ ከዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ ደንበኞቻቸው ከአንድና ከሁለት ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ እንዳያወጡ ከልክለው እንደነበር ለሪፖርተር የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ ከሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ እንዳቆሙ ገልጸዋል፡፡

ባንኮቹ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳለባቸውና ጥሬ ገንዘብ ከቀረበላቸው ከ20 ቀናት በላይ እንደሆነ መግለጻቸውን አቶ ምላሽ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ ባንኮቹ ሰቆጣ ወዳሉት ቅርንጫፎች ገንዘብ የማያስገቡት የፀጥታ ችግር ሥጋት እንዳለ በማሰባቸው ነው የሚል እምነት አለው፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ በበሬ ወለድ ምክንያት በከተማችን የፀጥታ ችግር እንደተፈጠረ ተደርጎ፣ የባንክ አገልግሎት በተገቢው መንገድ እየተሰጠ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም በባንኮቹ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር የተደረገው ስለከተማዋ የፀጥታ ሁኔታ፣ የፀጥታ ምክር ቤት ባልተጠየቀበት ሁኔታ መሆኑን ደብዳቤው ላይ አስፍረዋል፡፡

‹‹በከተማዋ ውስጥ አንድም የጥይጥ ኮሽታ የለም፤›› ያሉት አቶ ምላሽ፣  ‹‹በሁሉም አካባቢ ጥምር ጦሩ በተጠንቀቅ ቆሟል፤›› ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

ከተማዋ የምትገኝበት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተወሰኑ ወረዳና ቀበሌዎች በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሲሆኑ፣ በዚህም ምክንያት ከተያዙት አካባቢዎች የሚፈናቀሉ ሰዎች በብዛት ወደ ሰቆጣ ከተማ እንደሚመጡ አቶ ምላሽ ገልጸዋል፡፡

እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፣ በከተማዋ ውስጥ ከ70 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህ ተፈናቃዮች ለሚደረግ ድጋፍ የሚሰበሰበው ገንዘብ በባንክ የሚላክ በመሆኑ አገልግሎት መቋረጡ ተፈናቃዮችን እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡

‹‹ባንኮቹን ስናናግራቸው በእኛ አቅም የሚፈታ አይደለም፡፡ በዲስትሪክ ወይም በዋና መሥሪያ ቤት የሚፈታ ነው የሚል ሐሳብ ያነሳሉ፤›› ያሉት አቶ ምላሽ፣ የከተማ አስተዳደር ቅርንጫፎቹ ለሚመለከተው አካል እንዲያደርሱ በማሰብ ደብዳቤው እንደተጻፈ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሁኔታዎች ባንኮች የፀጥታ ችግር ሲፈጠር ሲዘረፉ እንደነበር ገልጸው፣ ባንኮቹ ጥንቃቄ እንውሰድ በሚል ለጊዜው አገልግሎት አግደው ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በአካባቢው ያለውን ተጋላጭነትና የፀጥታ ሥጋትን እየተመለከቱ ዕርምጃዎቻቸውን የሚወስኑት ባንኮቹ ራሳቸው መሆናቸውንና ብሔራዊ ባንክ ‹‹ዝጉ ክፈቱ›› የሚልበት ዕድል ጠባብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች በከተማዋ ውስጥ የፀጥታ ችግር እንደሌለ ለቅርንጫፍ ኃላፊዎች የማስረዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ‹‹ባንኮች አገልግሎት መስጠት ስለሚፈልጉ ችግር ከሌለ ይከፍታሉ፤›› ብለዋል፡፡

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፀጥታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አሥር ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ማለትም ባንኮች፣ ሱቆች፣ ሆቴልና መስል የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን መዝጋት በጥብቅ የተከለከለ ነው የሚል ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር እግረኞች ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ፣ ለፀጥታ ሥራ ሥምሪት ከተሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ውጪ፣ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀስ ታዟል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዎችም ከተሰጣቸው የመጠለያ ካምፕ ውጪ እንዳይንቀሳቀስ ዕግድ ተጥሏል፡፡ ከፀጥታ መዋቅሩ ውጪ የሆኑ ግለሰቦችም በየትኛውም ሰዓትና ቦታ የጦር መሣሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች