በንጉሥ ወዳጅነው
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተገነባበት ረዥሙ ዓባይ ወንዝ ተዝቆ የማያልቅ ታሪክ፣ የተፈጥሮ ሀብትና ውበት፣ ፀጋና በረከት የሞላበት ነው። የእኛኑ ዓባይ ግብፆች የህልውናቸው መሠረት በመሆኑና በኃያልነቱ የተነሳ ‹‹ኢሲስ›› እና ‹‹ኦሲሪስ›› የሚባሉ አማልክት ፈጥረውለት ሲያመልኩት ኖረዋል። በዓለማችን 263 ያህል ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ቢኖሩም፣ ረዥም ርቀት በመጓዝና በርካታ አገሮችን በማቋረጥ ቀዳሚ የሆነው ዓባይ (ናይል) ወንዝ 6,650 ኪሎ ሜትር በመጓዝ 11 አገሮችን የሚያካልል መሆኑም የሚስጥሩ መጀመርያ ነው፡፡
ዓባይን ሦስት ወንዞች ተጣምረው ይፈጥሩታል። እነሱም ከብሩንዲ ሰንሰለታማ ተራሮች የሚመነጨው ነጭ ዓባይ፣ ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ጥቁር ዓባይና የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ሱዳን ሲደርስ ‹‹አትባራ›› በሚል ስያሜ የሚጠራው ‹‹ተከዜ ወንዝ›› ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ወንዞች ካርቱም ላይ ከተገናኙ በኋላ ‹‹ናይል›› ይሰኛሉ።
የሱዳንና የግብፅን በረሃዎችን ሰንጥቆና አቋርጦ ረዥሙ የናይል ጉዞ እስከ ሰሜናዊ ግብፅ በመዝለቅ በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ይጠናቀቃል። የናይል ወንዝ 86 በመቶ ያህሉ የውኃ ሀብት የሚሄደው ከኢትዮጵያ ነው። ከዚህ ውስጥ የዓባይ ወንዝ ብቻውን 53 በመቶ ይሸፍናል፣ የዓባይ ታላቅነት ቅኔም ሌላው መገለጫ ይኼኛው እውነታ ነው፡፡
ያም ሆኖ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መፈጠሪያ ሆና ለዘመናት በዓባይ የመጠራት እንጂ የመልማት ዕድሉ አልነበራትም፡፡ ማንኛውም አገር ባሉት ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን በማይጎዳ መንገድ በውኃ ሀብቱ የመልማት ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብት እንዳለው ቢታወቅም፣ ለዘመናት ከሀብታችን ሳንጠቀም መቆየታችን ነው የሚያስቆጨው፡፡
በእርግጥ ዓባይ ለግብፆች ብቸኛ የውኃ ምንጫቸው ነው፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ ሊኖራቸው ቢችል እንኳ ስለእሱ ማሰብ አይፈልጉም፡፡ ዓይናቸው፣ ጆሮአቸውና ልባቸው ያለው ዓባይ ላይ ብቻ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ዓባይ ለግብፆች የዕለት ጉርሳቸውና የዓመት ልብሳቸው ነው፡፡ ሥጋታቸው፣ ቅዠታቸው፣ ጌጣቸው፣ ክብራቸው፣ ኩራታቸውና አጠቃላይ ህልውናቸው በዓባይ ውኃ ደኅንነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ሊዚህም ነው ትናንትም ሆነ ዛሬ ካይሮ የትኛውንም ወጥመድና ሴራ በመፈጸም እንኳንስ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለውን ፕሮጀክት፣ የትኛውንም የውኃ ልማት ለማሰናከል ወደ ኋላ የማትለው፡፡ ትርፉ ትዝብት እንጂ በተቀየረ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፣ እያደገ በመጣ የአገራችን ሕዝብና ምጣኔ ሀብት ብሎም የማደግ ፍላጎት በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ ለመጠቀም ማሰቡ ነበር የሚበጃት፡፡ ሴራው የበረታን እንደሆን እንጂ ሊሰናከል እደማይችል በገቢር ታይቷል፡፡
ገና ከጀማሬው አንስታ አገራችን የግድቡ ተልዕኮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና ማለፍ መሆኑን፣ ግብፅን እንደማይጎዳ፣ እንዲያውም ለግብፅ እንደሚጠቅም፣ ወደ ግብፅ በሚሄደው ውኃ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንደሌለውና ለተፋሰሱ አገሮች በአጠቃላይ ለሱዳንና ለግብፅ ደግሞ በተለይ አስረድታለች፡፡ ልዑካኖቻቸውን ተቀብላ፣ የእሷንም ልዑካን ልካ በጉዳዩ ላይ ግልጽ ውይይት አድርጋለች፡፡
በዓለም አቀፍና ከሦስቱ አገሮች በተውጣጡ የዘርፉ ሊቃውንት የግድቡን ፕሮጀክት አስመርምራለች፡፡ ምክረ ሐሳብ ተቀብላለች፡፡ የግድቡ ዲዛይን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንም በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን አረጋግጣለች፡፡ በተለይ ዋናው የኃይል ማመንጫ ግድብ በጠንካራ አለት ላይ ያረፈ መሆኑን፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደማያሠጋው፣ በብዙ ሺሕ ዓመታት አንድ ጊዜ ጎርፍ ቢከሰት እንኳ ማሳለፍ እንደሚችልና አስተማማኝ መሆኑንም በጥናት አረጋግጣለች፡፡
በሒደቱ የባለሙያዎች ቡድን ባቀረበው ምክረ ሐሳብ መሠረት ቀጣዩ ሥራ ምክረ ሐሳብን ተግባራዊ ለማድረግ የሦስቱን አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ) ማዕቀፍ ማደራጀት ነበር፡፡ ሦስቱ አገሮች ተገናኝተውም መነጋገራቸው አይዘነጋም፡፡ ያም ሆኖ ግብፅ በማዕቀፉ አባላት ላይ ተቃውሞ ከመሰንዘር አልተቆጠበችም ነበር፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን ከሦስታችንም አገሮች የተውጣጡ ባለሙያዎች ሥራውን መከታተል ይችላሉ ሲሉ፣ ግብፅ ግን ‹‹አይሆንም የዓለም አቀፍ ሙያተኞችም ካልገቡበት አሻፈረኝ›› እስከ ማለት ደርሳ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የአተገባበሩን የማዕቀፍ ኮሚቴ ለማቋቋም ሌላ ዓለም አቀፍ ኮሚቴ አያስፈልግም ብትባልም አይሆንም አለች፡፡ ይህንንም ‹‹እሺ›› ቢሏት ሌላ ተቃውሞ ማምጣቷ አይቀርም ነበር፣ ደግሞም አምጥታለች፡፡ ግብፅ በዓባይ ላይ የቀረበን ሐሳብ ከመቃወም ሌላ ሥራ የላትም እስኪባል ድረስ ስትጥል ስታነሳ ከረመች፡፡
ግድቡ ከተጀመረበት ባለፉት 11 ዓመታት ውስጥ ግብፅ የግድቡን ሥራ ለማወክና በጋራ ላለመሥራት ብዙ ርቀት ሄዳለች፡፡ አንዴ ‹‹የግድቡ ሆድ ሰፍቷልና ይጥበብ›› ስትል፣ ሌላ ጊዜ ‹‹የግድቡ ቁመት ይጠር›› ብላለች፡፡ ሌላ ጊዜ ግድቡ ቢደረመስ አደጋ ያስከትልብኛል ስትል፣ ሌላ ጊዜ የውኃ ድርሻዬን መጠን ይቀንስብኛለች እያለች ለስምምነት የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ እያጓተተች፣ ቋሚ መንግሥት እስኪመሠረትና እስኪወስን ጠብቁኝ እያለች አስተጓጉላለች፡፡ ሁሉም አሉታዊ ጥረቶች ግን ፕሮጀክቱን ከዳር ከማድረስ አላወኩም፡፡
ከሁሉ በላይ በምንገኝበት የዕውቀትና የመረጃ ዝመን ለሕዝቦቿም የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ደክማለች፡፡ ዓባይ የግብፅ ብቻ ነው ትላቸዋለች፡፡ ለእኛም ጭምር የኢትዮጵያ መንግሥት የግድቡ ሥራ እየተገባደደ ነው የሚለውት ውሸት ነው፣ የግድቡ ሥራ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ገጥሞታል፣ ኢትዮጵያ ወጪውን መሸፈን አልቻለችም፣ ሕዝባዊ ተቃውሞም ተነስቶበታል፣ ወዘተ እያለች ወገኖቿን ለማጀገን እኛን ደግሞ ተስፋ ለማስቆረጥና ጥርጣሬ ውስጥ ለመክተት በሚዲያዎቿና በምሁራኖቿ አማካይነት ሰፊ ቅስቀሳ ስታካሂድ ኖራለች፡፡
‹የግድቡን አካባቢ በአውሮፕላን ልትመታ ትችላለች› እያስባለች የሥነ ልቦና ሰለባ ዘመቻ ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱና ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻከርና ለማቃቃር፣ በዚህም ምክንያት የግድቡን ሥራ ለማሰናከል ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ለዚህም የተለያዩ ሥልቶችን ትጠቀማለች፡፡
የመጀመርያ ሥልቷ የኢትዮጵያን ሕዝብ በብሔር እየከፋፈለች ማቆሚያ በሌለው የእርስ በርስ ሽኩቻ እንዲወጠር ማድረግ ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ በወያኔ አማካይነት ወደ የማያባራ ጦርነትና ከወገኑ ጋር የማጋጨት ሥራ ውስጥ ከተዋለች፡፡ ኦሮሞን በአማራ ላይ ለማስነሳት የተጀመረ የአፍራሽ ኃይሎች ሴራ ዛሬም ብልጭ ድርግም እያለ ቀጥሏል፡፡ በብሔር ብሔረሰቦች ካባ የተሸፈኑ ነፃ አውጭ ተብዬዎችና አማፅያንን በየቦታው እየደገፈች፣ ቀላል የማይባል ትርምስ ስፖንሰር ማድረጓ በመረጃ ተደጋግሞ የተረጋጋጠ ነው፡፡
ኦሮሞ ኢትዮጵያዊነቱን እንደሚጠራጠር የሚያወሩና እንዲገነጠል የሚገፋፉ፣ በአማራው ላይ ጥላቻ እንዲያድርበት ከአፄ ምኒልክ ያለፈ ታሪክ ውስጥ መጥፎ መጥፎ የሚሉትን እየለቀሙ ዘረኝነትን የሚያራግቡ የፌስቡክ አርበኞች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ሴረኛ ዜጎች የጥፋት ድግስ በስተጀርባ የግብፅ እጅ አለበት፡፡ ማንኛውንም የግብፅ እንቅስቃሴ ግድቡን ለማሰናከል ከሚደረግ ዘመቻ ጋር አያይዘን ማየት አለብን፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ መታየት ያለበት የግብፅ መንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጁ ቡድኖችን በገንዘብ እያማለለ በስፋት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡
የግብፅ ሌላኛው ሥልት በሃይማኖቶቻችን መካከል ያሉትን የግንኙነት ድሮች ለመበጣጠስና በሃይማኖት ሰበብ አገር እንዲተራመስ ማድረግ ነው፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከመንግሥት ጎን እንዳይሠለፍና ከክርስቲያኑ ኅብረተሰብም ጋር ተባብሮና ተከባብሮ እንዳይኖር የአሏህ ሕዝብ (Hizbu-Allah) እና የሰይጣን ሕዝብ (Hizbu Shaitan) በሚል ፈሊጥ እየከፋፈሉ የሕዝቡን አንድነት ለማናጋት መክረማቸው ብቻ ሳይሆን፣ በቅርቡ በአልሸባብ ዳግም ጥቃትም ሞክረዋል፣ የተሳካ ባይሆንም፡፡
በዚህ ረገድ በውስጣችን ያሉትን አክራሪ ኃይሎች በገንዘብ በማጠናከርና በማደራጀት ይህንኑ የመከፋፈያ መርዝ እንዲረጩ፣ ሁከትና ሽብር እንዲፈጥሩ፣ ወኔ ሰላቢ የሆኑ ፕሮፓጋንዳዎችን እንዲያሠራጩ፣ ከፍተኛና አሰቃቂ የኃይል ዕርምጃዎችን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየወሰዱ ሕዝቡ እንዲሸማቀቅ ለማድረግ መኳተናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ እኩይ የሆነ የእሾህን በሾህ ሴራ ሥልታቸው በፊትም የነበረና የቀጠለ ነው፡፡
የግብፅ ፖለቲከኞች የሚሉትን ሁሉ ቢሉ፣ የሚጮኹትንም ያህል ቢጮሁ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ማድረግ ያለባቸውን እያደረጉ የግድቡን ሥራ አጠናክረው በመቀጠላቸው የተደረሰበት ደረጃ ላይ መድረስ ተችሏል፡፡ ዋናው ሥራን በአግባቡና በትኩረት መሥራት እንጂ፣ የእነሱ ጩኸትና ማስፈራሪያ እንደማይበግረንና ሥራችንን የሚያስተጓጉል የገንዘብና የፀጥታ ችግር እንደሌለብን በተግባር ማሳየት በመቻላችን እንደ ሕዝብና አገር ልንኮራም ይገባል፡፡
ለወደፊቱም ቢሆን በግብፅ ፖለቲከኞችና ሐሳዊ መሲህ ምሁራን ወሬ መፈታት የለብንም፡፡ የእነሱ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆንም አይገባም፡፡ ስለኃይል ማመንጫ ግድባችን ትክክለኛውንና ወቅታዊውን መረጃ የምናገኝበት ተቀዳሚ ምንጫችን የእኛው የራሳችን መንግሥትና የግድቡ ሥራ ብሔራዊ አስተባባሪው ተቋም መሆን አለበት፡፡ መንግሥትና በዘርፉ ያሉት አዋቂዎችና ሙያተኞች የሚሉንን መስማት ብቻ ይበቃናል፡፡
በዚህ ረገድ ከብዙ ሥራዎቻችን በተሻለና ለብሔራዊ አጀንዳ ትኩረት የሚሰጡ የማኅበረሰብ አንቂዎችና በቂ የዕውቀት ባለቤቶች አሉን፡፡ ስለወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በአጠቃላይና ስለዓባይ ወንዝ በተለይ ሊያስረዱን የሚችሉ እንደ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ፣ ያዕቆብ አርሳኖ (ፕሮፌሰር)፣ መህመድ አልአሩሲ፣ ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ ጌታቸው ወልዩና የአሁኑ ዘመን ከሚባሉትም እነ ሰላም ሙሉጌታ፣ ሱሌማን አብደላ፣ ስላአባት ማናዬ፣ ደጀኔ አሰፋ፣ እስሌማን ዓባይ (የዓባይ ልጅ) እና ሌሎችም ምሁራን ስለዓለም አቀፍ የውኃ ሕግጋትና ስለወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ፖለቲካ በበቂ አሳማኝ ሁኔታ ሊነግሩን ይችላሉ፡፡
ስለሆነም ስለዓባይ ጉዳይ መረጃ ለማግኘት ጆሮዋችንን የግብፅ ፕሮፓጋንዲስቶችና ቅጥረኞች አፍ ሥር መደቀን አያስፈልገንም፡፡ የግድቡን ግንባታ ያለማቋረጥ እያስኬድን ጎን ለጎን ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና የሃይማኖት ልዩነቶቻችን ለግብፅ መሰሪዎች መጠቀሚያ እንዳይሆን መሥራት አለብን፡፡ በዚህ ረገድ የሚነሱ ጉዳዩችን በሙሉ በጥንቃቄ እንመርምር፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠንክረንና እንደ አንድ ሰው ሆነን፣ በአንድ ልብ ሊደቀንብን የሚችለውን ተግዳሮት ለመወጣት እየተዘጋጀን ፍፃሜውን ማሳመር ይጠበቅብናል፡፡
ለነገሩ እስካሁንም ከተፈጥሮ ሀብታችን ላለመጠቀማችን እንቅፋት የሆነችብን ግብፅ ብቻ አልነበረችም፡፡ ሌሎች ውጫዊ ተፅዕኖ አድራጊዎችና የራሳችንም ውስጣዊ የአቅም ውስንነት ነበረብን፡፡ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን በቅኝ ገዥነት ያስተዳድሩ የነበሩ አገሮች በውኃ ሀብቱ ግብፅ ብቻ ተጠቃሚ እንድትሆን በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸው ስምምነቶች፣ እንዲሁም ከቅኝ አገዛዝ በኋላ የግብፅ መንግሥታት ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ለማልማት የገንዘብ ድጋፍና ዕርዳታ እንዳታገኝ ሲያደርጉ ልክ ነው ብለው ሳያመነቱ የተቀበሏቸው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች በውጫዊ ተፅዕኖነት አድራጊነት ይጠቀሳሉ።
እ.ኤ.አ. ከ1890 እስከ 1950 ድረስ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ቅኝ ገዥዎች (በዋናነት እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን) በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ከስድስት ጊዜ በላይ ስምምነቶች አድርገዋል። ሁሉም ስምምነቶች ኢትዮጵያንና ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሕዝቦችን ያገለሉና በዋናነት ግብፅን በተከታይነት ሱዳንን ተጠቃሚ ያደረጉ በመሆናቸው ይመሳሰላሉ።
ከሁሉም በላይ ግን እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 ግብፅና ሱዳን የናይል ውኃን ብቸኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን የደነገጉበትን የእርስ በርስ ስምምነት አድርገዋል። እ.ኤ.አ. በ1928 ኢትዮጵያን ወርሮ የነበረው የፋሺሽት ጣሊያን መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ልማት ላለማካሄድ ከእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች ጋር ተፈራርሟል። እነዚህ ድርጊቶች ሁሉ በታሪክ ጥቁር መመዝገብ ያለባቸው ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ1959 ለናይል ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላቸው ሁለት አገሮች፣ 86 በመቶ የናይል ውኃ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የራስጌ ተፋሰስ አገሮች ጭራሽ መኖራቸውን በመዘንጋት ስምምነት አድርገዋል። እስከ ዛሬ በዓባይ ውኃ ላለመልማታችን በሁለተኛነት ምክንያት የሆነው ደግሞ በወንዙ ላይ ልማትን በራስ ሀብት ለማከናወን የሚያስችል አቅም ማጣታችን መሆኑን፣ እንደ ትልቅ መመርያ መውሰድ ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡
እዚህ ላይ ይህ የዓባይ ትውልድ የሚኮራበት ቁም ነገር ያለውን ሀብት አሟጦ በራስ አቅም ግድቡን ለመገንባት በመነሳቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ገና ከጅምሩ፣ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መርሆችን መሠረት የደረገውን የናይል ሁሉን አቀፍ የስምምነት ማዕቀፍ በማርቀቅና በመጨረሻም አብላጫው የተፋሰሱ ሕዝቦች እንዲቀበሉት በማድረግ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራቱ መደላድሉን ምቹ አድርጎታል። ለኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው እ.ኤ.አ. በ2015 በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመው «Declaration of Principles» በመባል የሚታወቀው ስምምነት ነው የሚባለውም በዚሁ መነሻ ነበር።
ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ፣ አሥር ዝርዝር ነጥቦችን የያዘና ሦስቱንም የተፋሰሱ አገሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ታሪካዊና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ብዙ የውጭ ተፅዕኖዎች ተደርገውባታል፡፡ ያንን ሁሉ ጫና በጣጥሳ በአሸናፊነት ወጥታ እነሆ የግድቡ ግንባታ ሦስተኛውን ሙሌት አጠናቆ ኃይል ማመንጨት ደረጃ እንዲደርስ አንዱ እርሾ የተፋሰሱ አገሮች በፈራ ተባም ቢሆን የደረሱበት ስምምነት ነው።
አንዲት ጠብታ ውኃ ለዓባይ ወንዝ የማታዋጣው ግብፅ በእኛ ሀብት ስትከብር ኖራ፣ ዛሬ በራሳችን ገንዘብ በሠራነው ግድብ ስካታብድ መታየቷ ግን አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሁንም ከተጣባት በሽታ አለመላቀቋን ያሳያል፡፡
ካይሮ በቅርቡ የእኛን ግድብ የውኃ ሙሌት ተከትሎ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ጠርታ በ13 ሚኒስትሮች ላይ የሹም ሽር አድርጋለች፡፡ በፀረ ኢትዮጵያዊነት በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ የሚዲያና የማኅበራዊ ሚዲያ ሥልጠና ከመላው አፍሪካ ለተውጣጡ የሚዲያ ሰዎች በተለያዩ ቋንቋዎች በመስጠት፣ በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ ዘመቻ ለመክፈት እንደ አዲስ እየሠራች መሆኗንም ነው ውስጥ አዋቂ መረጃዎች ያመለከቱት፡፡
በዚህ ረገድ አሁንም ኢትዮጵያውያን መናጋት የለባቸውም፡፡ ነቅተው፣ ተደራጅተውና ተደማምጠው የጠላትን ሴራ ማምከንና ግድቡን ከዳር ለማድረስ መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ሚዲያዎቻችንና የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ትምህርት ቤቶችና የምርምር ተቋማት ከተለመደው አሰልቺ ነገር ወጥተው ለጉዳዩ ጠንከር ያለ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ የማንንም ፈቃድ ሳይጠብቁም ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ ዓባይ ዓባይ ማለት አለባቸው፡፡
ሕዝባችንን በበቂ ሁኔታ ስለግብፅም ሆነ ስለሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ስትራቴጂካዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ማሳወቅ፣ ማስተማርና ማንቃት የዘወትር አጀንዳ መሆን አለበት። ጠላቶቻችን የሚሠሩት ለአሉታዊ ትርክትና ለኢፍትሐዊ ተጠቃሚነትም ሲሆን፣ የራሳቸውን ሕዝብ በማንቃትና ወጥ አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ ላይ አተኩረው ነው፡፡
የእኛ የሕዝብም ይባሉ አብዛኞቹ የግል ሚዲያዎች የጠላትን ፕሮፓጋንዳ ለማምከንና ሕዝባችን ለብሔራዊ ጥቅሙ መከበር በአንድ እንዲቆም ለማድረግ ብርቱ ሥራ መከወን እንደሚጠበቅባቸው ማስታወስ ያስፈልጋል። የግብፅ ሴራ በውስጥ ካሉ የአገር (የመንግሥት አላልኩም) ባላንጣዎች ዘመቻ ጋር ተቀናጅቶ የቀጠለ ሲሆን፣ ይህን ሰባብሮና አንኮታኩቶ መጣል፣ አሸናፊነታችንን በሁሉም መስክ ማስቀጠል የእኛና የእኛ ኃላፊነት ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ የካይሮና ሼሪኮቻቸው ሴራ ቢያይልም፣ ዓባይ ለወገኑ ትሩፋት ከመሆን የሚገታው የለም ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር የሚቻለውም ይህንኑ በማድረግ ብቻ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡