Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከተማ አስተዳደሩ ለማስታወቂያ በሚሆኑ ዋና ዋና 120 ቦታዎች ላይ ጨረታ ሊያወጣ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚገኙና ለማስታወቂያ  ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ጨረታ ሊያወጣ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጨረታውን የሚያወጡት የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮና የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአንድ ላይ ሆነው ነው፡፡ ቦታዎቹን የማዘጋጀቱ ሥራ ‹‹ወደ መጨረሻው›› እንደ ደረሰ የባለሥልጣኑ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አዲሱ መለሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ቦታዎቹ ለጨረታ የሚቀርቡት ለምን ዓይነት ማስታወቂያ እንደሆነ ተለይቶ መሆኑን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

ለጨረታ የሚቀርቡት ቦታዎች ከአያት ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከመገናኛ ወደ ቦሌ፣ ከመገናኛ በአራት ኪሎ እስከ መርካቶ በሚወስዱት ዋና መንገዶች፣ እንዲሁም ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት በቸርችል ጎዳና በሚያስወርደው ዋና መስመር እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ለማስታወቂያ የሚሆኑ ቦታዎችን በጨረታ ለማስተላለፍ ዝግጅት የጀመረው ሰኔ 2014 ዓ.ም. ላይ የውጭ ማስታወቂያ ደንብ ቁጥር 128/2014 በከተማዋ ካቢኔ ከፀደቀ በኋላ ነው፡፡

በከተማዋ ውስጥ ማንኛውንም ቦታ ማግኘት የሚቻለው በጨረታ አልያም በምደባ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ አዲሱ፣ ለውጭ ማስታወቂያ የሚሆን ቦታ አሰጣጥን አስመልክቶ የተጋዘጀ መመርያ እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት እስካሁን ለውጭ ማስታወቂያ የሚሆን ቦታ ይሰጥ የነበረው በምደባ እንደነበር፣ ነገር ግን አብዛኛዎቹ በከተማዋ ውስጥ የተተከሉ የውጭ ማስታወቂያዎች ሕገወጥና ፈቃድ የሌላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በከተማው በሚገኙ 400 የማስታወቂያ ቢል ቦርዶች ጥናት አድርጎ ከ200 በላይ የሚሆኑት ፈቃድ እንደሌላቸው ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከውጭ ማስታወቂያ ደንብ መፅደቅ በኋላ፣ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥን አስመልክቶ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚዘረዝር ስታንዳርድ ያወጣ መሆኑን፣ አሁን ደግሞ የውጭ ማስታወቂያ ማጫረቻ መመርያ እንዳዘጋጀ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

መመርያው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እንደተደረገበት የገለጹት አቶ አዲሱ፣ ‹‹እንደ ፀደቀ ነው የምንወስደው፤›› በማለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፀድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፣ በዚህ መመርያ ላይ ለማስታወቂያ የሚሆኑ ቦታዎች በጨረታና በምደባ ሊሰጠጡ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡ ጨረታ የሚወጣው በዋና መንገዶች ላይ በሚገኙ ቦታዎች፣ የመንግሥት ሕንፃዎችና መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰቀል ማስታወቂያ ነው፡፡ ዋና ዋና መንገዶች የሚባሉት በተለይም ከ20 ሜትር በላይ ስፋት ያላቸውን እንደሚመለከት አስረድተዋል፡፡

በእነዚህ ቦታዎች ላይ ማስታወቂያ መስቀል የሚፈልጉ የመንግሥት ተቋማት ጨረታ መሳተፍ እንደማይጠበቅባቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹መንግሥት በልዩ ሁኔታ የሚወሰንባቸው ቦታዎች ሲኖሩ በምደባ የሚሰጥበት ሁኔታ ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡

በመጋቢና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ከጨረታ ውጪ በምደባ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ መሬት የሚመራውና የሚተዳደረው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመሆኑ፣ ለጨረታ የሚቀርቡት ቦታዎች የተለዩት ከቢሮው ጋር በጋራ በመሆኑን እንደሆነ አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የተለዩት ቦታዎች አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም ማስታወቂያ ያልነበረባቸው አዲስ ቦታዎች ናቸው፡፡ የተወሰኑት ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ማስታወቂያ ተሰቅሎባቸው የነበሩና ባለሥልጣኑ በቅርቡ ባደረገው ዘመቻ ያስለቀቃቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

‹‹ቦታዎቹ ሲለዩ ምን ዓይነት ማስታወቂያ ይሰቀልባቸው የሚለውም አብሮ ተለይቷል፤›› ብለው፣ ቦታዎቹ ለቢልቦርድ ወይም ለኤሌክትሮኒክ ስክሪን ማስታወቂያ ሰሌዳነት እንደሚውሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹መመርያው ሲፀድቅ አብረን እናሳውቃለ፤›› በማለት ጨረታውን የሚያሸፉ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ቦታውን ለምን ያህል ጊዜ እንደሚይዙ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

ይሁንና በሊዝ ለተሰጠ መሬት የሚኖረውን ዘመን እንደማይከተልና ቦታው እንደሚሰቀልበት የማስታወቂያ ዓይነት እንደሚወሰን አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ፣ ‹‹የቢልቦርድ ኅትመት የሚዘጋጀውና ዲጂታል ስክሪን የሚተከልበት እኩል ቦታና እኩል ጊዜ አይኖረውም፡፡ የዲጂታል ስክሪኑ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበትና አዲስ ቴክኖሎጂ ነው የዕድሜ ዘመኑ የተለየ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በሰኔ ወር ላይ የፀደቀው የውጭ ማስታወቂያ ደንብ በመሬት፣ በሕንፃ፣ በንግድ ድርጅት፣ በአጥር ወይም በማናቸውም መሰል አካል ላይ የሚተከል፣ የሚለጠፍ ወይም በማናቸውም መንገድ የሚሠራጭ የውጭ ማስታወቂያን የሚመለከት ነው፡፡

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለአጭር ጊዜ የሚተከል፣ የሚለጠፍ ወይም በማናቸውም መንገድ የሚሠራጭ የውጭ ማስታወቂያ የሚተላለፈው ወቅታዊ ሁነቱ ከመከናወኑ በፊት ከአንድ ወር በላይ ላልበለጠ ጊዜ ሲሆን፣ ሁነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሰባት ቀናት በላይ መቆየት እንደማይችል ደንቡ ደንግጓል፡፡

የውጭ ማስታወቂያ በማናቸውም መንገድ ከማሠራጨቱ በፊት ለፈቃድ ሰጪው የአገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በምሥልና በጽሑፍ የሚሠራጭ የውጭ ማስታወቂያ የክፍያ ተመን በማስታወቂያ ሰሌዳው ስፋት በሜትር ካሬና በቆይታ ጊዜው የሚሰላ ሲሆን፣ በድምፅ የሚተዋወቅ የውጭ ማስታወቂያ በሚወስደው ጊዜ ይሰላል ተብሏል፡፡

በአዲሱ የከተማ አስተዳደሩ የውጭ ማስታወቂያ ደንብ ቁጥር 128/2014 መሠረት፣ በበራሪ ወረቀቶች የሚሠራጩ ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ሁሉንም የውጭ ማስታወቂያዎች መጠቀም የሚቻለው፣ ይዘታቸው በከተማው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ታይቶና በከተማው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች