Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኒያላ ኢንሹራንስ ለሞባይል ስልኮቻቸው የመድን ሽፋን ለገዙ ደንበኞቹ 1.4 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ከፈለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ለሞባይል (ተንቀሳቃሽ) ስልክ የመድን ሽፋን መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ15 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ስልኮች የመድን ሽፋን ያገኙ ሲሆን ሽፋን ካገኙት ስልኮች መካከል በሞባይል ጉዳት ደርሶባቸው የካሳ ጥያቄ ላቀረቡ ደንበኞቹ 1.4 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉን አስታወቀ።

ኒያላ ኢንሹራንስ ለሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ለሚሰጠው የሞይባይል ስልክ የመድን ሽፋን አገልግሎት አዲስ የአረቦን ክፍያ ፓኬጅ ይፋ እንደሚያደርግም ግልጿል፡፡ 

ከኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ‹‹ለሞባይሌ›› የተሰኘው የኢንሹራንስ (መድን) ሽፋን መጋቢት 2013 ዓ.ም. መተግበር የጀመረ ሲሆን እስካሁንም ከ15 ሺሕ በላይ ለሞባይል ስልኮቻቸው የኢንሹራንስ ሽፋን የገቡ ደንበኞችን ማፍራት ተችሏል፡፡ 

አገልግሎቱ ከጀመረ መጋቢት 2013 ዓ.ም. ወዲህ ለሞባይላቸው የኢንሹራንስ ሽፋን ከገቡ 15 ሺሕ ደንበኞች ውስጥ 400 ለሚሆኑ ደንበኞች ካሳ ከፍሏል፡፡ ስልኮቻቸው ለጠፋ፣ ለተሰረቀና የስልክ ስክሪናቸው ለተሰበረ ደንበኞቹ በገቡት የዋስትና ልክ 1.4 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉንም የኩባንያው የዲጂታል ኢንሹራንስ አልግሎቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ሚሊኬሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

የኢንሹራንስ ሽፋኑ የተሰረቀና የጠፋ የሞባይል ስልክ ቆፎዎችን ለመተካትና ስክሪናቸው ለሚሰበሩ ሞባይሎች የጥገና አገልግሎት መስጠትን የሚያጠቃልል ሲሆን እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ካሳ ከተከፈለባቸው ስልኮች ውስጥ የስልኮቻቸው ስክሪን ለተሰበሩባቸው ደንበኞች 367 ሺሕ 179 ብር እንዲሁም፣ ሞባይላቸው ለተሰረቀባቸውና ለጠፋባቸው ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ከፍሏል፡፡ 

ይህ የኢንሹራንስ አልግሎትን ሲጀምር ከአምስት እስከ 15 ሺሕ ብር ዋጋ ላላቸው የሞባይል ስልኮች የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት ሲሆን፣ ደንበኛውም የዚህን የመድን ሽፋን አገልግሎት ለማግኘት ውለታ ሲገባ ክፍያውን (አረቦን) የሚሰበሰበው ከሞባይል የአየር ሰዓት በየዕለቱ ተቀንሶ ነው፡፡ 

ለዚህም አገልግሎት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል። በስምምነቱ መሠረትም የአምስት ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸው የመድን ሽፋን ለተገባላቸው የሞባይል ስልክ ቀፎዎች በቀን አንድ ብር፣ ከአምስት እስከ አሥር ሺሕ ብር ዋጋ ላላቸው ስልኮች ደግሞ አንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም እንዲሁም ከአሥር እስከ 15 ሺሕ ብር ዋጋ ላላቸው ደግሞ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ከደንበኛው የአየር ሰዓት ላይ በመቁረጥ አረቦኑ እንደሚሰበሰብ ታውቋል፡፡ 

እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ሞባይሌ የተሰኘው የስማርት ስልኮች የኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎት ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ ከ15 ሺሕ ደንበኞቹ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አረቦን መሰብሰብ ተችሏል፡፡

ይህንን የኢንሹራንስ ሽፋን የሚገባ ደንበኛ ሞባይሉ ሲሰረቅ ወይም ሲጠፋ  በገባው የኢንሹራንስ ሽፋን ልክ ወቅታዊውን ዋጋ ባገናዘበ መልኩ የሞባይሉን ዋጋ ካሳ ያገኛል፡፡ ከዚህም ሌላ የሞባይሉ ስክሪን ሲሰበርበትም የኢንሹራንስ ኩባንያው ስክሪኑን ከፍሎ ያስለውጣል፡፡ 

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የመጀመርያ የሆነውን በሞባይል ስልኮች የኢንሹራንስ ሽፋን በመስጠት የመጀመሪያ የሆነው ኒያላ ኢንሹራንስ እስካሁን በፓኬጅ ደረጃ ሲተገበር የነበረውን ይህንን አገልግሎት ለማስፋት አሁንም ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለመተግበር እየተዘጋጀ መሆኑንም አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡  

አዳዲስ ፓኬጆቹ የክፍያ አማራጮችን በማከል ከመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲሱ ፓኬጅ ካስፈለገበት ምክንያቶች አንዱ በየጊዜው እያደገ ከመጣው የስማርት ስልኮች ዋጋ መጨመር ጋር በተያያዘ የኢንሹራንስ ሽፋኑን ለመስጠት ነው፡፡

ለሞባይሌ የተባለውን የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት ከአራት ዓመት በፊት የተደረገን ጥናት መሠረት በማድረግ ሲሆን በዚህም የመድን ሽፋን አገልግሎቱን ለማቅረብ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሰጠው እስከ 15 ሺሕ ብር ላሉ የሞባይል ስልክ ቀፎዎች ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ በላይ ዋጋ ያላቸውን የሞባይል ስልክ ቀፎዎች የያዙ ደንበኞች የመድን ሽፋኑ አግልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸው ነበር፡፡ አዲሱ ፓኬጅ ግን ወቅታዊውን የሞባይል ቀፎ ዋጋ ባገናዘበ መልኩ እንዲስተናገድ በሚያስችል መልኩ የሚተገበር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት ስማርት የሞባይል ቀፎዎች እስከ 120 ሺሕ ብርና ከዚያም በላይ ዋጋ ያላቸው ስላሉ እንዲሁም ከ15 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የሞባይል ቀፎዎች እየበዙ ስለመጡ ለእነዚህ ሁሉ የሞባይል ቀፎዎች አገልግሎለት ለመስጠት አዲሱ አሠራር ትልቅ ዕገዛ እንደሚኖረው አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህም ሌላ እስካሁን ለሞባይል ስልክ ቀፎዎቻቸው ኢንሹራንስ የገቡ ደንበኞች ለሽፋኑ በየቀኑ የሚከፍሉት አረቦን ላይ የሚደረገው ከአየር ሰዓታቸው ላይ ብቻ ተቀንሶ ሲሆን አዲሱ ፓኬጅ ግን ሌሎች ተጨማሪ የክፍያ አማራጮችን መጠቀም የሚያስችልና ደንበኛው በወር በስድስት ወርና በዓመት መክፈል የሚችልበት የተለያዩ የክፍያ አማራጮች የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ 

ለዚህም እንደ ቴሌ ብር፣ ኢብርና አሞሌ የመሳሰሉትን አማራጭ የክፍያ ዘዴዎች በመጠቀም የኢንሹራንስ ሽፋኑን ክፍያ መፈጸም ይችላል ተብሏል፡፡ አዲሱ ፓኬጅ ከ15 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የሞባይል ቀፎዎች የመድን ሽፋን የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በዚሁ መሠረት እንደ ሞባይሉ ዋጋ መጠን የአረቦን መጠኑም ከፍ እያለ የሚሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለምሳሌ የአምስት ሺሕ ብር ሞባይል ያለው አንድ ብር በቀን ይከፍላል 15 ሺሕ ብር ሞባይል ስልክ የመድን ሽፋን የገዛ ሰው በቀን የሚከፍለው አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ወይም በዓመት 547 ብር 50 ሳንቲም ይከፍላል፡፡ ይህ ክፍያ የሞባይል ዋጋው ሲጨምር እንደሚጨምር ታውቋል፡፡ ለምሳሌም ከ85 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያለው ሞባይል ስልክ ያለው ደንበኛ ደግሞ የኢንሹራንስ ሽፋኑን ሲገዛ 2850 ብር የሚከፍል ሲሆን አከፋፈሉም ኩባንያው በሚያቀርባቸው የተለያዩ የክፍያ አማራጮች ይሆናል፡፡ ከክፍያ አማራጮቹ ሌላ በየቀኑ፣ በየወሩ፣ በየስድስት ወሩና በየዓመቱ አረቦኑን መክፈል የሚቻልበት አሠራርን ይፈጥራል፡፡ 

ለሞባይሌ የኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎት ጋር በተያያዘ የካሳ ክፍያው እንዴት ይፈጸማል ለሚለው አቶ ግርማ የጊዜውን ዋጋ መሠረት ባደረገ መልኩ ክፍያው እንደሚፈጸም ገልጸዋል፡፡ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው ደንበኛው የሚጠበቅበትን አረቦን በትክክል ከፍሏል አልከፈለም የሚለው ከተረጋገጠ በኋላ በትክክል ስልኩ ስለመጥፋቱና ስለመሰረቁ ደንበኞች በፖሊስ አስመስክረው ከተረጋጋገጠ በኋላ በሞባይሉ የገበያ ዋጋ መሠረት የካሳ ክፍያው የሚፈጸም ይሆናል ተብሏል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የሞባይል ቀፎው ሳይጠፋ ጠፋብኝ ብሎ ካሳ ይከፈለኝ የሚሉ ጥያቄዎች እንዳይኖሩና የተሰረቀ ሞባይልን ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ከቴሌ ጋር በገባው ውል መሠረት እንዲዘጋ ወይም አግልግሎት እንዳይሰጥ ይደረጋል። ይህም ያልጠፋ ስልክ ጠፋ ተብሎ ካሳ እንዳይከፈልበት ዕገዛ ያደርጋል፡፡  

ከቴሌ ጋር የተገባው ውል ለስልካቸው ኢንሹራንስ ከገቡ ደንበኞች ከአየር ሰዓታቸው ላይ አረቦን እንዲሰበስብ ከማድረግ ባሻገር ጠፋ የተባሉ ስልኮች ደግሞ አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ የሚሰጣቸው አገልግሎት የካሳ ክፍያውን በተገቢው መንገድ ለመፈጸም ያስችላቸው እንደሆነም ከአቶ ግርማ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ከዚህም ደንበኞች ሽፋኑን ሲገዙ የሞባይሉን የስልኩን ሞዴል፣ ሴሪያል ነምበርና የመሳሰሉትን መረጃዎች የሚያስገቡ በመሆኑ አንድ ደንበኛ ስልኬ ስልኬ ጠፍቷል ብሎ ሲያመለክት የሞባይሉን መረጃ ለቴሌ በማሳወቅ ይህ ቀፎ ይዘጋልን ብለውም እናመለክታለን፡፡ ስለዚህ ቀፎው አይሠራም፡፡ የኢንሹራንስ ካሳውም ሲከፈል ስልኩ በትክክል በቴሌ መዘጋቱ ከተረጋገጠ በኋላ የሚከፈልም ይሆናል፡፡ 

ይህንን የኢንሹራንስ ሽፋን ለማሳደግ የሚተገበሩት አዳዲስ ፓኬጆች የደንበኞችን ቁጥር የሚያሳድግ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ግርማ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከ100 ሺሕ በላይ ደንበኞች ለሞባይል ቀፎዎቻቸው የኢንሹራንስ ሽፋን እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ 

እስካሁንም የደንበኛችን ቁጥር 15 ሺሕ ብቻ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ በአሁኑ ወቅት ያሉ ስማርት ስለኮች ከ15 ሺሕ ብር በላይ ከመሆናቸውና የኢንሹራንስ ሽፋኑ ደግመ እስከ 15 ሺሕ ብር ዋጋ ላላቸው የሞባይል ቀፎዎች ብቻ ሽፋን ይሰጥ ስለነበር ነው፡፡

የ50 እና የስልሳ ሺሕ ብር ሞባይል ይዘው ለ15 ሺሕ ብር ሽፋን አንገባም የሚሉ ስላሉ አዲሱ ፓኬጅ ግን ከ100 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ላላቸው ሽፋን መስጠት የሚያስችል በመሆኑ በቀጣይ ዓመታት በየዓመቱ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ደንበኞችን እየፈሩ መሄድ ያስችላልም ብለዋል፡፡ ለሞባይሌ የመድን ሽፋን በኦንላይን የሚሰጥ ሲሆን ደንበኞች ወደ 813 OK በማለት በሚደርሳቸው ሊክ የሚያገኙትን ፎርም በመሙላት የመድን ሽፋኑን የሚያገኙበት ነው፡፡ 

‹‹ለሞባይሌ›› የኢንሹራንስ ሽፋን ሥራውን ሲጀምር እስከ 15 ሺሕ ብር ብቻ ዋጋ ላላቸው የሞባይል ቀፎዎች አገልግሎት ለመስጠት የተወሰነበት ዋነኛ ምክንያት ከአራት ዓመታት በፊት የነበረውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት የገባው የአዋጭነት ጥናት በብሔራዊ ባንክ የተፈቀደው ደግመ ከሦስት ዓመት በኋላ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ 

ኒያላ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ27 ዓመታት በላይ በመዝለቅ የሚታወቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለግብርና የመድን ሽፋን በመስጠት ፈር ቀዳጅ የሆነው ኒያላ ኢንሹራንስበአሁኑ ወቅት 704 ሚሊዮንብር ካፒታል ያለው ሲሆን በመላ አገሪቱ 46 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች