ከጥቂት ቀናት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ካገረሸው የጦርነት ሥጋት ጋር በተያያዘ በከተሞቹ የሰዓት ዕላፊ እየተጣለ ነው፡፡
የዞኑ ከተሞች ነዋሪዎች በተለይም ወልዲያ፣ ላሊበላና ጋሸና አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በርካታ ነዋሪዎች በጦርነቱ ሥጋት ወደ አቅራቢያ የገጠር አካባቢዎች ወደ ደሴ፣ ኮምቦልቻና ባህር ዳር በምሽት ጭምር በተሽከርካሪና በእግር እየተጓዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ሥጋት ከወልዲያ ከተማ ወደ ደሴ ያመሩና አምስት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የተጓዙ አንድ ግለሰብ ባልተለመደ ሁኔታ ከወልዲያ ደሴ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ለአምስት የቤተሰብ አባላት 7,000 ብር ከፍለው በኮንትራት ደሴ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ከደሴ ወደ ባህር ዳር፣ እንዲሁም ከወልዲያ ወደ ደሴ ለመጓዝ ከሚታየው የዋጋ ንረት በተጨማሪ የተሸከርካሪ እጥረት መኖሩን፣ አቶ መልካሙ ፈጠነ የተባሉ የወልዲያ ነዋሪ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
አቶ መልካሙ እንደሚሉት፣ በወልዲያ ከተማ የሚገኙ የንግድ መደብሮች ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ዝግ ሆነው ሲውሉ፣ በከተማው ያለው እንቅስቃሴ በአመዛኙ ሰላማዊ ነበር፡፡
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ የሰዓት ዕላፊ ገደብ መውጣቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ በከተማው ከተመደበ የፀጥታ ኃይል አሽከርካሪዎች ውጪ ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት መንቀሳቀስ እንደማይቻል ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት፣ ተማሪዎች ለደኅንነታቸው በመሥጋት ከግቢ እየወጡ መሆኑን በመጥቀስ፣ በቀጣይ ዓመት እንደ አዲስ ጥሪ እንደሚደረግላቸው አስታውቆ ነበር፡፡
ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋሁን ባታብል፣ የዞኑ ዋና መቀመጫ የሆነችው የወልዲያ ከተማ ሰላም መሆኗንና ምንም ዓይነት ሥጋት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከወልዲያ ራቅ ያሉ አካባቢዎቸ በተለይም ጎብየ፣ ወርቄ፣ ተኩለሽ በሚባሉ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ ቢኖርም ወልዲያ ሰላም ነች፣ ሕዝቡም ይረጋጋ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም በድንጋጤ እየተፈናቀለ ያለውን ሕዝብ ግን በመመለስ ይሠራል ብለዋል፡፡
ከተጠቀሱት አካባቢዎች እየተፈናቀሉ ያሉ ሰዎች ቁጥር ምን አንደሚመስልና ያሉበትን ሁኔታ እንዲገልጹ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት አቶ ኢያሱ መስፍን፣ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ እሰካሁን ከየቅርንጫፎቹ የደረሰ መረጃ የለም ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በአፋር ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት በአፋርና በትግራይ ክልሎች ድንበሮች የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ምን እንደሚመሰል ሪፖርተር የጠየቃቸው የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ መሐመድ ሀሰን፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተፈጠረውን ፍልሰት ለማስጠናት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች አጥኚ ቡድን መላኩን ገልጸዋል፡፡