Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሰሜኑ ጦርነት የተበላሹ ብድሮች ከባንኮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ አይነሱም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ልማት ባንክ አሥር ቢሊዮን ብር ታማሚ ብድር እንዲነሳለት ጠይቋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተበላሹ ብድሮች ከባንኮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ እንደማይነሳ አስታወቀ፡፡

ልማት ባንክን ጨምሮ ሁሉም የንግድ ባንኮች በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ የተበላሹ ብድሮች ከሒሳብ ደብተራቸው ላይ እንዲነሳላቸው ብሔራዊ ባንክን ሲጠይቁ ነበር፡፡ የንግድ ባንኮች በተለይ በባንኮች ማኅበር በኩል ጉዳዩን ሲከታተሉ እንደቆዩ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ ባንኮች በተለይ በአሁኑ ጊዜ የተጠናቀቀውን የ2014 ዓ.ም. ዓመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን እያዘጋጁ መሆናቸውን፣ የተበላሸ ብድር በደብተራቸው ላይ ይነሳል በሚል ሲጠብቁ እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ብድሩ እንደማይነሳ ገልጸዋል፡፡፡ ‹‹ባንኮች የተበላሸው ብድር ከባላንስ ሽታቸው ላይ እንዲነሳ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ በሒሳብ አያያዝ ሕግ ያልተደገፈ ነው ብለን አይቻልም ብለናቸዋል፡፡ ይህ እንደማይቻል ካነጋገርናቸው ቆይተናል፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አንድ ስለሆነ የልማት ባንክን ለይተን የምናነሳበት ሁኔታም የለም፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡

ባንኮች በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በትግራይ ክልል የነበሯቸው ብድሮች እንደተበላሹ በመቁጠር፣ መጠባበቂያ (Provision) ሲይዙ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት የተበላሸ ብድር ምጣኔያቸው ከፍ ሲል፣ እንዲሁም የትርፍና ካፒታል መጠናቸው ላይ ቅናሽ ታይቷል፡፡

‹‹የጠየቅነው የተበላሸው ብድር እንዲሰረዝ ሳይሆን፣ ለጊዜው ከባላንስ ሺት ውጪ እንዲቆይና ወደፊት ሁሉም ሲረጋጋ ብድሮቹ እንዲከፈሉ ማድረግ ነበር፤›› ሲሉ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ልማት ባንክ ባለፈው ሳምንት ዓመታዊ አፈጻጸሙን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ኃላፊዎች ባሉበት በሒልተን ሆቴል ባስገመገመበት ወቅት በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠሩበት ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ብቻ የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር አሥር ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ልማት ባንክ 4.1 ቢሊዮን ብር መጠባበቂያ ከትርፉ ላይ ለመያዝ መገደዱን፣ ይህም ትርፉን ከ7.8 ቢሊዮን ብር ወደ 3.7 ቢሊዮን ብር እንዲወርድ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ከጦርነቱ ወዲህ ከተከፈቱ 12 አዳዲስ ባንኮች ውጪ 18 ነባር ባንኮች በትግራይ ክልል እንቅስቃሴ ነበራቸው፡፡ ወደ ስምንት ሺሕ ከሚጠጉ አጠቃላይ የባንክ ቅርንጫፎችም አሥር በመቶ በትግራይ ይገኛሉ፡፡ ከልማት ባንክ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ወጋገን ባንክ ትልልቅ ብድር ትግራይ ክልል ውስጥ ሰጥተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

ጦርነቱ በተጀመረ በመጀመርያው ዓመት እንኳን ንግድ ባንክ እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ወጋገን እስከ 1.6 ቢሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገው ነበር፡፡

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት የተበላሹ ብድሮቹን ምጣኔ ለአፍሪካ ልማት ባንኮች ከሚመከረው የ15 በመቶ ምጣኔ በታች ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ለነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ጦርነቱ ከፍተኛ ተግዳሮት መደቀኑን ዮሐንስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ባንኩን እንዲታደጉ የዛሬ ሁለት ዓመታት ኃላፊነት ሲወስዱ የተበላሸ ብድሩ 40.9 በመቶ በመድረሱ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልማት ባንክ እንዲፈርስ ሐሳብ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ የተበላሸ ብድር ምጣኔው 24.3 በመቶ ደርሷል፤›› ያሉት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የትግራይ አሥር ቢሊዮን ብር ከዚህ ውስጥ ቢወጣ ግን የታማሚ ብድር ምጣኔው ወደ 12 በመቶ እንደሚወርድ ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር በልማት ባንክ ላይ ባጠናቀረው የ2014 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ፣ የባንኩ ታማሚ ብድር በአሁኑ ጊዜ 19.2 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ከእዚህም ውስጥ 48.5 በመቶ ሊሰበሰብ የማይችል (Loss)፣ 33.8 በመቶ ደግሞ አጠራጣሪና 18 በመቶው ከደረጃ በታች ብድሮች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ከአጠቃላይ 19.2 ቢሊዮን ታማሚ ብድር ውስጥ 93 በመቶ ለማኑፋክቸሪንግና ለግብርና የተሰጠ ነው፡፡

በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸቸው የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፈንታዬ፣ የተበላሹ ብድሮችን ከባንኮች ባላንስ ሺት ላይ ማንሳት ከባድ መሆኑን እንደሚገነዘቡት ተናግረዋል፡፡

‹‹የገቢዎች ሚኒስቴር ካልፈቀደ በስተቀር የተበላሹ ብድሮቹን መሰረዝም ሆነ ከኦዲት ደብተር ውጪ ማድረግ ወይም መጠባባቂያ መያዝ አይፈቅድም፡፡ ባይሆን ብሔራዊ ባንክ ኪሳራውን በአንዴ ከራሳችሁ ካፒታል አካክሱ ባይል ጥሩ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ትልልቅ የተበላሹ ብድሮችን በአንዴ ዕውቅና ስጡ ማለት የባንኮችን የካፒታል አቅም ያዳክማል፤›› ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች