Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የለማጅ ያለህ!

የዛሬው ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ መርካቶ ተጀምሯል፡፡ በሥራም ሆነ በትምህርት ምክንያት በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ገባ ብሎ መውረድ አይቀርም፡፡ ይህ አባባል የሚመለከተው መኪና የሌላቸውን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ በታክሲ ሲሄዱ አፌ ቁርጥ ይበልላችሁ የሚባሉ፣ ወይም ደግሞ አፋችሁ ይቆረጥ መባል የሚገባቸው ወያላና ሾፌር ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ሥርዓተ አልባ ወያላዎች የተማረሩ ሰዎች፣ ‹‹እግዜር ይይላችሁ›› ብለው ተራግመው ሲወርዱ፣ ሌሎች ደግሞ ለመብቴ መንግሥትንም ሆነ እግዜርን መጥራት አይጠበቅብኝም በሚመስል ስሜት የአፍ ጦርነት ይማዘዛሉ፣ ይጨቃጨቃሉ፣ የሚቧቀሱም አይጠፉም፡፡ እነሱ እንደሚሉት መብታቸውን ያስከብራሉ ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ወያላዎች፣ ‹‹መብቴ ነው!›› የሚላቸው ሰው ጠላታቸው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹መብታችሁ ታክሲ ውስጥ ትዝ አይበላችሁ›› በማለት ታክሲያቸው ውስጥ በሰቀሉት ጥቅስ ይከራከራሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው ካሳፈሩት ሰው ጋር ይጨቃጨቃሉ፣ ይወዛገባሉ፡፡ በአንድ በትንሽዬ አጋጣሚ ሳይሆን በርስት ወይም በሌላ ንብረት የሚከራከሩ ነው የሚመስሉት፡፡ አንድ ሰው፣ ‹‹ወገኖቼ ኧረ በደህና ነገር እንጨቃጨቅ፡፡ ማን ይሙት አሁን ደህና ውይይት የሚሻ አገራዊ ጉዳይ ጠፍቶ ነው እንደዚህ በረባ ባልረባው የምንነታረከው?›› አለ፡፡ ሌላው ሰው ደግሞ፣ ‹‹አየህ ሰው በርካታ ብሶቶች ሳይኖሩበት አይቀርም፡፡ ስለዚህ ትንሽ ነካ ስታደርገው በሆዱ ውስጥ አፍኖ ያቆየውን ሁሉ ይዘረግፈዋል፡፡ ወዶ አይደለም በሰው አትፍረድ…›› አለው፡፡ ምክር መሆኑ ነው!

የሁለቱ ሰዎች ክርክር ታክሲዋን በከፊል ተቆጣጠራት፡፡ የመጀመሪያው ወጣት፣ ‹‹ቢሆንም ለአገርም ለሕዝብም በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መከራከር ያዋጣል፡፡ በማይረቡ ጉዳዮች ጊዜያችንን እያጠፋን አዕምሯችንን ከምናደንዘው ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ይበጀናል…›› ሲል አንዲት ወጣት ደግሞ፣ ‹‹እውነት ነው፣ ለምን ሰሞኑን ተጀመረ ስለተባለው አስከፊ ጦርነት አናወራም? ለምን ስለአገራችን ውጥረት አናወራም? ኧረ እንዲያውም ወሳኝ ስለሆነው ህልውናችን ጉዳይ ለምን አንነጋገርም?›› በማለት አስተያየቷን ሰነዘረች፡፡ ወሬውም እየጦፈ ሄደ፡፡ ወጣቱና ወጣቷ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ወግ ቀጠሉ፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎች አፌን በዳቦ ያሉ ይመስል ጭጭ አሉ፡፡ አንድ ጎልማሳ በታፈነ ድምፅ፣ ‹‹አሁን የጦርነት ወሬ ምን ያደርጋል? ክፉ እያናገረን ለክፋት ይዳርገናል…›› አለ፡፡ ወያላው በተጀመረው ውይይት ብዙ የተመሰጠ አይመስልም፡፡ ለሾፌሩ የድሮ ታሪኩን ይተርክለት ጀመረ፣ ‹‹ድሮ ልጅ እያለሁ ጫማ የሚባል ነገር ጠላቴ ነበር…›› አለ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እግር ኳስ እንኳን ታኬታ ካደረጉ ልጆች ጋር በባዶ እግሬ ነበር የምጫወተው፡፡ የመጫወቻ ሥፍራዬ ተከላካይ ነበር…›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹እሺ እባክህ እስቲ በደንብ አጫውተኝ…›› በማለት ለታክሲዋ ነዳጅ እየሰጠ ወያላውም እንዲያወራ ቆሰቆሰው፡፡ ወያላው ቀጠለ፣ ‹‹የቅጽል ስሜ ‹ቀልጥመው› ነበር፡፡ እያቆላመጡ ‹ከቀልጥም ኳስ ቢያልፍ እግር አያልፍም› ሲሉኝ በቃ፣ እንኳን በታኬታ በታንክ ቢመጣ ማንንም አላሳልፍም ነበር፡፡ ኳሱን አታሎኝ ቢያሳልፍ ሰውዬውን ግን ተዓምር ቢፈጠር አላሳልፈውም…›› እያለ ተረከለት፡፡ ጦርነት በሉት!

በዚያ እንደ ብረት በሚከተክተው እግሩ የስንቱን ቅልጥም እንደሰበረ ሲናገር የጦር ሜዳ ውሎ የሚተርክ ይመስል ነበር፡፡ ሾፌሩ ብስጭት እያለ፣ ‹‹በፈጠረህ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንተን አሠልፈውህ ቢሆን ኖሮ ይኼኔ ስንቴ ለዋንጫ ሽሚያ ደርሰን ነበር…›› አለው፡፡ ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹እነሱን እባክህ ተዋቸው እንኳን የአፍሪካ ዋንጫን ይቅርና የበረኪና ዋንጫ አያነሱም፡፡ በዚያ ላይ ክለቦቻችን ውስጥ ያለውን ትርምስ አታውቅም እንዴ?›› አለ፡፡ ወያላው ቀጥሎ፣ ‹‹እኔን ግን ሠፈር ውስጥ በጣም የሚያማርሩኝ ልጆች ነበሩ…›› በማለት የጥንቱን እያስታወሰ ይስቅ ጀመር፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ለምንድነው የሚያማርሩህ? አታነክታቸውም እንዴ?›› አለው፡፡ እሱም፣ ‹‹ያላነከትኩት ሰው የለም፡፡ ግን ትችታቸውን አያቆሙም፡፡ አንዴ ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ?›› አለው፡፡  ሾፌሩም ምን ብለው እንደተቹት ለመስማት እየጓጓ፣ ‹‹ደግሞ ምን አሉህ?›› አለው፡፡ ወያላው ከመናገሩ በፊት ሒሳብ መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ይኼኔ ቅድም የተጀመረውን ወሬ ለመስማት ፋታ አገኘን፡፡ የመጀመሪያው ወጣት አንድ ነገር ሲናገር ጆሯችን ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡ ደግሞ ለወሬ!

‹‹በአንድ አገር ውስጥ የሕዝብ ንዴት በየትኛው ቅጽበት እንደሚነሳ ማወቅ አይቻልም…›› በማለት የተወሰኑ ሰዎችን ጆሮዎች ሰበሰበ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እነዚህ ወያኔዎች የትግራይ ሕዝብ ተራበ ብለው እዬዬ ሲሉ ከርመው ከየት አምጥተው ነው ጦርነትን የሚያህል ነገር የሚቀሰቅሱት አይባልም እንዴ… ጦርነት ለማስነሳት እኮ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ከእነ ጥይቶቻቸውና ተተኳሾቻቸው፣ ሠራዊት ለማሠልጠን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ፣ ነዳጅ፣ የሕክምና ቁሳቁሶችና የተለያዩ ሎጂስቲክሶች ያስፈልጋሉ… እነዚህ ሰዎች ሕዝብ ተራበ እያሉ እየጮሁ በምን አቅማቸው ነው ጦርነት ማስነሳት የቻሉት…?›› ብሎ ዱብ ዕዳ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ወጣቱን አሁንም በከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹አገር አጥፊ ወንበዴ ጦርነት ሲቀሰቅስ ውኃ ቀጠነ ብለን በመንግሥት ላይ መማረር የለብንም፡፡ ከመንግሥት ጎን ቆመን እነዚህን ወንበዴዎች ልክ ማስገባት አለብን፡፡ ለዚህም ለመንግሥታችን ተገቢውን ድጋፍና ማበረታቻ ማበርከት አለብን…›› ሲል ብዙዎች ድጋፋቸውን ገለጹለት፡፡ አንዳንዱ እኮ ይናገረዋል!

የልጁ እንደዚያ መናገር ያስገረማቸው አንድ አባት፣ ‹‹ልጄ አንተ ገና አንድ ፍሬ ብትሆንም ያነሳኸው ሐሳብ ግን ብስለት ያለው ነው…›› ብለው አሁንም በሰከነ አንደበት፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች ሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ወጣቱ በሰላም መኖር አይችልም ነበር፡፡ በልማት ስም ዝርፊያውን የቤተሰብና የዘመዳሞች ነበር ያደረጉት፡፡ ዴሞክራሲንም ቢሆን ስሙን እንጂ ግብሩን አያውቁትም፡፡ ያ ጨቋኝ ሥርዓት በማለፉ ፈጣሪን እያመሠገንን ደግሞ እንዳይመለስ መተባበር የእኛ ፋንታ ነው…›› ብለው ንግግራቸውን ገቱ፡፡ በዚህ መሀል ሾፌሩ ወያላውን፣ ‹‹እስቲ የፖለቲካ ጨዋታውን እዚህ ላይ እንግታና ታሪክህን ቀጥልልኝ፡፡ ምን እያሉ ነበር የሚተቹህ?›› አለው፡፡ ወያላውም ምንም ሳያቅማማ፣ ‹‹እንዳልኩህ ጫማ የሚባል ነገር አልወድም፡፡ እናም ሁልጊዜ በባዶ እግሬ ስሄድ ነበር ሰላም የሚሰማኝ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ቤተሰቦቼና እኔ የተጋበዝንበት አንድ የቅርብ ዘመድ ሠርግ ነበር፡፡ እዚያ ሠርግ ላይ ባዶ እግሬን መገኘት ለእኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ ውርደት ነበር፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦቼም እንደምንም ተጣጥረው አንድ አዲስ ጫማ ገዙልኝ፡፡ ያንን ጫማ አድርጌ ትንሽ ‹ወክ› ለማድረግ ከቤት ወጣ ስል እነዚህ እርጉም የሆኑ የሠፈራችን ልጆች አጋጠሙኝ…›› ብሎ ወሬውን አቋረጠው፡፡ ይኼኔ ልቡ የተሰቀለው ሾፌር፣ ‹‹ታዲያ ሲያዩህ አትዘንጥባቸውም ነበር? ግን ምን አሉህ?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹አካሄድ ጠፍቶብኝ ስሸነካከል ዓይተው ወደ እግሬ እየጠቆሙ፣ ‹ለማጅ› አይሉኝ መሰለህ?›› ሲል፣ ሾፌሩ ራሱን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ታክሲዋን ወደ ዳር እንኳን አስጠግቶ ማቆም አቃተው፡፡ መሀል ላይ አቁሞ በሳቅ ተንከተከተ፡፡ ወይ ጉድ!

ሌሎች መኪኖች ማለፊያ ስላጡ በጥሩምባቸው አካባቢውን ድብልቅልቁን አወጡት፡፡ ሾፌሩ ግን መኪናዋን ማሽከርከር እስከሚያቅተው ድረስ ሳቀ፡፡ አንዳንድ መንገድ የተዘጋባቸው አሽከርካሪዎች በመስኮታቸው ብቅ እያሉ፣ ‹‹ለማጅ ነህ እንዴ? ሰው እንዳትጨርስ አውርዳቸው…›› በማለት ተጯጯሁ፡፡ ሾፌሩን ‹ለማጅ› ሲሉት የባሰ እያሳቀው እንደምንም ብሎ ታክሲዋን አስነሳት፡፡ አንዲት ተሳፋሪ ወያላውን፣ ‹‹ሾፌሩ ለማጅ ነው?›› ብላ ስትጠይቀው እሱም እየሳቀ፣ ‹‹አዎ! ልምድ የለውም…›› ሲል ታክሲዋ በጩኸት ታመሰች፡፡ ወያላው እንደገና በከፍተኛ ድምፅ፣ ‹‹ተሳፋሪዎች እባካችሁ ተረጋጉ፡፡ የሾፌሩ ልምድ ከማንም ጋር ሳይነጋገር መንዳት እንጂ፣ እየሳቁ መንዳት አይደለም…›› ሲል ነፍሳችን ተመለሰች፡፡ ‹ለማጅ› የሚለውን ቃል አግዝፈው የሰሙት ግን ቆፈን እንደያዘው ሰው ይንዘፈዘፉ ነበር፡፡ አጠገቤ የተቀመጠች አስተዋይ ቆንጆ፣ ‹‹እየሠጋሁ ያለሁት አገሬም የለማጆች መጫወቻ እንዳትሆን ነው…›› ስትለኝ ወያላችን፣ ‹መጨረሻ› ብሎ አሰናበተን፡፡ ‹‹ወያኔም ዘወትር ለማጅ እየሆነ ነው እኮ ያስቸገረን…›› የሚል ድምፅ ደግሞ ከሩቅ ይሰማ ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት