በአገር ደረጃ ያለውን የፈሳሽና የደረቅ ጭነት የማጓጓዣ ችግር ለመቅረፍ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር በ2013 ዓ.ም. በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎትና አቅሙ ላላቸው 168 ድርጅቶች/ግለሰቦች፣ ደረቅና ፈሳሽ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲገዙ በፈቀደው የሁለት ዓመታት የዱቤ ግዥ ሥርዓት መሠረት፣ የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (የአፍሪ ኤግዚም ባንክ) ዋስትና ያገኙ የተወሰኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች የገዟቸው 745 ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር አስተባባሪነት በዱቤ ግዢ ለመግዛት የታቀዱት 2600 የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች ነበሩ፡፡
ዓለም አቀፍ የጭነት መኪኖች አምራች ከሆነው ሲኖትራክ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ከሚላኩት 745 የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 28ቱን እንደሚልክ አስታውቋል፡፡
አከፋፈሉን በሚመለከትም መቀመጫውን ዱባይ ያደረገውና ለኢትዮጵያውያን ኤጀንት የሆነው ጃምፑር ኢንተርናሽናል ኩባንያ የመጀመሪያውን የ28 ተሽከርካሪዎች ዋጋ ለሲኖትራክ ኩባንያ ከፈጸመ በኋላ፣ ኢትዮጵያውያኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለጃምፑር እንደሚከፍሉና ቀሪዎቹን 717ቱን ደግሞ እንደሚልክ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት ዓመታት የዱቤ ግዢ ከሚገዙት 2600 የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 63 ሚሊዮን ዶላር ድረስ የሚያወጡ 745 የሚሆኑት የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በሁለት ዓመት መክፈል እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ዋስትና ስለተሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መታቀዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የግዢ ሒደቱን በአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በኩል የጨረሱ መኪኖች 745 ቢሆኑም፣ ዓለም አቀፍ የጭነት መኪና አምራች የሆነው ሲኖትራክ የሚልከውን መኪኖች ክፍያ የሚከፍለው የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን፣ በገዢዎቹ የተመረጠው ጃምፑር መሆኑን ለማረጋገጥ፣ በቅደሚያ 28 ብቻ ለመላክ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሲኖትራክ አምራች ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
መኪኖቹን የሚገጣጥመው ሲኖትራክ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙት ገዢዎች በሽያጭ የሚያቀርበው ጃንፑር ነው። ጃንፑር ሲኖትራክን የሚወክል ኤጀንት ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙት ገዢዎች የሁለት ዓመት የዱቤ ግዢ የፈጸሙት ከጃንፑር ጋር ሲሆን፣ ሲኖትራክ አምርቶ ለሚልካቸው መኪኖች ክፍያውን ከጃንፑር ወዲያውኑ ይቀበላል፡፡
ሲኖትራክ የሚያመርታቸውን የደረቅና የፈሳሽ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ገዢዎች ጃንፑር ኢንተርናሽናል ለሚባል ድርጅት ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈታቸውን፣ የገዢዎች ኮሚቴ አባልና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ገደፋው ባዬ ተናግረዋል።
ለግዥው ሒደት መዘግየት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በዋናነት ግን በአቅራቢው ድርጅት በኩል የተጠየቀው የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ማረጋገጫ መሆኑን ገደፋው ተናግሯል።
ለዚሁ ግዥ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ የመክፈያው ጊዜ ሲደርስ ገዢዎች በኢትዮጵያ ብር ያስቀመጡትን ተቀማጭ ገንዘብ መንግሥት ወደ ዶላር በመቀየር ክፍያው የሚፈጸም መሆኑን የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ይሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እንደ አገር የረዥም ዓመት የዱቤ ግዢ የተካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ፣ የዓለም አቀፍ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ገዢዎች ላይ በተደረገ የዋጋ ማስተካከያና አምራቹ በኢትዮጵያ ባንኮች እምነት ስለሌለው በአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት የአሠራር ሒደት መኪኖቹ በወቅቱ እንዳይላኩ ካደረጉት ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ ገዚዎች ገልጸዋል፡፡
ተሽከርካሪዎቹ በወቅቱ እንዳይገቡ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ የሆነው የዋጋ ማስተካከያ በ2022 በአቅራቢው ድርጅት በኩል በዓለም ላይ በሸቀጦችና በባህር ጉዞ ላይ በታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሲሆን የዋጋ ማስተካከያ ሒደቱ ሁለት ዓይነት ነበር፡፡
በቅድሚያ ማለትም ከ2022 በፊት የባንክ ሒደት ላጠናቀቁና ሌተር ኦፍ ክሬዲት በከፈቱ ገዥዎች ላይ የስምንት በመቶና በተቀሩት ላይ ደግሞ የአሥር በመቶ ጭማሪ ተደርጓል።
ጥቁር ዓባይ ትራንስፖርት ማኅበር መጀመሪያ 251 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በዋጋ ማስተካከያው ምክንያት ወደ 231 ዝቅ በማድረግ አምራቹ የጠየቀውን የባንክ ሒደት ያጠናቀቀ ድርጅቶች ውስጥ ይካተታል፡፡
በጥቁር ዓባይ ትራንስፖርት የታዘዙት ተሽከርካሪዎች ከአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የሁለት ዓመት ዋስትና ያለው ሌተር ኦፍ ክሬዲት ከ15 ቀን በፊት ለጃምፑር ማስተላለፋቸውን የጥቁር ዓባይ ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መላኩ ተናግረዋል፡፡
ለድርጅቱ በአዋሽ ባንክ 18 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መከፈቱን ያረጋገጡት አቶ ሥዩም ከተሽከርካሪዎቹ አጠቃላይ ዋጋ ውስጥ 30 በመቶውን ለባንኩ ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡