Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ለ27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተገለጸ

ኢትዮጵያ ለ27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተገለጸ

ቀን:

በመጪው ኅዳር 2015 ዓ.ም. በግብፅ ሻርማልሼክ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የተባበሩት መንግሥታት የ27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ ከአስተናጋጇ ግብፅ በኩል ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጫናዎችን በበቂ ሁኔታ መልስ በሚሰጥ መልኩ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተገለጸ፡፡

በየዓመቱ በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አዘጋጅ አገሮች ከዋናው አጀንዳ ወጣ ያሉ የጎንዮሽ ፍላጎታቸውን ሊያንፀባርቁ የሚችሉ አጫጭር ስብሰባዎችን በማዘጋጀት፣ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አማካይነት መልዕክታቸውን እንደማስተላለፊያ መንገድ ይጠቀሙበታል፡፡

በእንግሊዝ አዘጋጅነት በስኮትላንድ ግላስጎው ከተማ የተካሄደው 26ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ወደ 40 ሺሕ የሚጠጉ ተሳታፊዎችና ወደ ከ3,800 በላይ የሚዲያ ተቋማት የተገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን በመወከል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ተሳትፈዋል፡፡

ቀጣዩን 27ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የምታዘጋጀው ግብፅ በርካታ የዓለም አገሮች መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የአየር ንብረት ተቆርቋሪ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ለጋሽ ድርጅች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የሚዲያ ተቋማት የሚኙበት ሲሆን፣ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እሰጣ አገባ የገባችበትን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት የተለመደ የተቃርኖ ሐሳቧን ለማንጸባረቅ ዝግጂት እያደረገች ስለመሆኑ የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን እየገለጹ ነው፡፡  

ለማሳያነት እንኳ የመካከለኛው ምሥራቅ የሚዲያ ተቋማት የግብፅ ባለሥልጣናትን ጠቅሰው፣ የግብፅ በታላቁ ህዳሴ ላይ ያነጣጠረ የጎንዮሽ ምክክርና የተሳታፊ አገሮችን ዕይታ ሊቀይር የሚችል ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጀችበት ስለመሆኑ ዘግበዋል፡፡

የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ በአፍሪካ ኅብረት እንዲፈታ ከወሰነ ወዲህ፣ የሦስቱ አገሮች ድርድር እስካሁን ባለበት መቆሙ ይታወቃል፡፡

በተለይም ከግድቡ ጋር ተያያይዞ ‹‹አሳሪ ስምምነት ሳይኖር ሙሌቱ መከናወን የለበትም›› በሚል ግብፅና የሱዳን የቆየ አቋም አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

የግብፁ አልሞኒቶር የዜና ምንጭ የቀድሞ ዲፕሎማትን ጠቅሶ እንደጻፈው፣ በኅዳር ወር 2015 የሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለግብፅ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውኃው ሙሌት ስምምነት ባለመደረሱ ምክንያት ግብፅና ሱዳን ላይ የሚያደርሰውን ጫና በማንጸባረቅ፣ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጫና የምታሳድርበት ዕድል እንደሚፈጥርላት ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የግብፅ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደጻፈው ግብፅ በጉባዔው ላይ በአዳጊ አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የሚነሱ አለመግባባቶችን ከአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታ ጋር እንደ ወሳኝ አጀንዳ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንደሆኑና  የአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥረውን ጫና በመጥቀስ፣ ግብፅ በየዓመቱ በህዳሴው ግድብ ምክንያት ውኃ ልታጣ እንደምትችል የምታንጸባርቅበት መድርክ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ የግብፅ መስኖ ሚኒስቴር መሐመድ አብደል አታይ፣ በኅዳር ወር በግብፅ አዘጋጅነት በሚካሄደው ጉባዔ፣ የውኃ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግበትና የውኃ መጠን መቀነስ፣ የበረሃማነት መስፋፋትና ድርቅ እንዲሁም የዝናብ አጥረት የጉባዔው ዋነኛ አጀንዳ ለማድረግ ሥራ ላይ መሆናቸውን ዘግቧል፡፡

በግብፅ ዝግጅት ላይ ስማቸው ሳይጠቀስ ሐሳባቸውን ለሪፖርተር የሰጡ አንድ ኢትዮጵያዊ የአየር ንብረት ተደራዳሪ ሲናገሩ፣ የአየር ንብረት አጀንዳው ምንም እንኳ ቀድሞ የተያዘ ቢሆንም፣ ግብፆች ያገኙትን ዕድል ሁሉ ተጠቅመው ስለህዳሴ ግድቡ የተለመደውን የጩኸት ዲፕሎማሲ ማሰማታቸው እንደማይቀር አስረድተዋል፡፡

የጉባዔው አዘጋጅ በመሆኗ የተለያዩ ዓይነቶች ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ድምጼ ይሰማ ለማለት ዕድል እንደሚሰጣት የገለጹት ተደራዳሪው በዚሁ ልክ የሚመጥን ዝግጅት በኢትዮጵያ በኩልም መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመሆኑም ከተደራዳሪ ኮሚቴውና ኢትዮጵያን ወክሎ በጉባዔው ከሚሳተፈው አካል ጋር የተመረጡ የሚዲያ ተቋማትን በመያዝ፣ የጉዳዩን ክብደት ማሳየትና ለሚነሱ ማናቸውም የተሳሳቱ ዕይታዎችና ዕሳቤዎች መልስ ሊሰጥ የሚችል ተመጣጣኝ የጎንዮሽ የሚዲያ መግለጫና ኮንፈረንስ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ባለሙያውና ስማቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ ስለጉዳዩ ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በኩል በየዓመቱ የሚደረጉ ተሳትፎዎች በጉባዔ ተሳትፎ ከመመለስ ባሻገር፣ በቅድመ ጉበዔ ወቅት የሚደረጉ ዝግጅቶች እምብዛም ለሚዲያ ያልተገለጹና ሕዝብም የማይሰማቸው ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ ለዚህኛው ፕሮግራም በመያዝ በየዓመቱ የተገኙ ውጤቶችን በመገምገም በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸውን ቅድመ ዝግጅቶች፣ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበትና ውይይት ሊካሄድበት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ግብፅ የ27ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማዘጋጀት ከምታደርገው ዝግጁነት ልክ፣ ግድቡ በግብፅ ላይ ሊያሳድር ይችላል የምትለውን ሁሉ እየፈጠረች በማሰማት የተሳታፊ አካላትን እይታ ሸውራራ እንደሚያደርግና በስተመጨረሻም ኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

አክለውም በግብፅ ግፊት ሊፈጠር የሚችል ጫናን ሲያብራሩ፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚለግሱትን የፋይናንስና ቴክኒካል ድጋፍ መቀነስ፣ መያዝ፣ ዕርዳታ ወይም አበዳሪ አካላት ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት የሚኖራቸው ፍላጎት ሊቀንስ እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ግብፅ ልታሰማው በምትችለው የሐሰት እሮሮ ልክ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሆነ መልስ ወይም ማስተባበያ ካልሰጠች፣ በግብፅ የተነገረው መረጃ ምንም እንኳን ከእውነታ የራቀ ቢሆንም፣ የመረጃ ተቀባዮቹ የተነገረውን እንደ እውነተኛ መረጃ መውሰዳቸው አይቀሬ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ተመርጠው ወደ ግብፅ የሚጓዙ ተሳተፊዎች በመድረኩ የሚነሱ ሐሳቦቸን የበሰለ ሐሳብ ማቅረብ የሚችሉና መልስ መስጠት እንዲችሉ ተደገርገው የተቀረጹ መሆን እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ግብፆች ስለ ህዳሴ ግድቡ ያላቸው አቋም ቅርፁን ሊቀያይር ይችላል እንጂ ይዘቱ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ግብፆች ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ያልተኙ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ  ወደ ፊትም ይህን አቋን በማስቀጠል በተገኘው መድረክ ሁሉ ሥልት በመቀያየር ፕሮፓጋንዳ ማንፀባረቀባቸው የማይቀር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ስምምነቶች ማስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ መንሱር ደሴ በበኩላቸው፣ ግብፅ የታለቁ ህዳሴ ግድብን አጀንዳ ልታንጸባርቅ እንደምትችል ቢጠቁሙም፣ ጉባዔው በአኅጉር ደረጃ አፍሪካን ወክሎ የመጣ በመሆኑ በዋና ኮንፈረንሱ ላይ የራሷን አቋም የምታንጸባርቅበት ዕድል እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በኩል ገና ግብፅ ስለግድቡ እንዲህ ታደርጋለች በሚል፣ ነገሩን የማጉላትና የማጮህ ፍላጎት እንደሌለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ መደረግ ያለበት ቅደመ ዝግጅት ግን እየተከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...