Friday, December 8, 2023

ኮርፖሬሽኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርጥ ዘር ማባዣ አካባቢዎችን ቀየረ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርጥ ዘር ማባዛት ባለመቻሉ፣ በሌሎች አካባቢዎች አዳዲስ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻዎችን ወደ ሥራ በማስገባት ዘር የማባዛት ሥራ እየሠራ መሆን ገለጸ፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፀጥታ ችግር ምክንያት በቤንሻንጉል ክልልና በኦሮሚያ ክልል ሆሮ አለልቱ መሰብሰብ የነበረበት ምርጥ ዘር አለመብሰቡን፣ የግብርና ሚኒስቴር በቅርቡ የገለጸ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የግብርና የፀረ ተባይና ፀረ አረም መድኃኒቶችን በማምረት የሚታወቀው ዓለም አቀፉ ኮርቴቫ አግሪሳይንስ ኩባንያ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እርሻ ላይ መሰብሰብ የነበረበትን ምርጥ ዘር በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ምንም ዓይነት ምርት ሳይሰበስብ መቅረቱን ገልጾ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም እንደተናገሩት፣ በፀጥታ ምክንያት ለተፈጠረው እጥረትና የአቅርቦት መጠንን ለማሳዳግ የምርጥ ዘር ማባዣ ልማት ጣቢያዎችን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልና በጋምቤላ ክልሎች ለማቋቋም ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል፣ አሥር ሺሕ ሔከታር መሬት ላይ ምርጥ ዘርና ወደ ውጪ የሚላኩ የጥራጥሬ ምርቶችን ለማምረት የሚያሰችለው የኢንቨስትመንት ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶ፣ በክልሉ እየታየ ስለመሆኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የዘር ብዜቱ 68 በመቶ የሚሆነውን ዘር በሰፋፊ የመንግሥትና የባለሀብት እርሻዎችና በአርሶ አደር ማሳ ላይ፣ ቀሪውን 32 በመቶ ደግሞ በራሱ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማቶች ላይ በማባዛት፣ በአገር ደረጃ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የምርጥ ዘር ፍላጎት እየሸፈነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አክለውም በ2014 በጀት ዓመት 139,217 ኩንታል ዘር 703.4 ሚሊዮን ብር መሸጡን ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ አሁን ያለውን 2.4 ቢሊዮን ብር የማቋቋሚያ ካፒታል ወደ 9.7 ቢሊዮን ብር ሊያሳድግ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው ኮርፖሬሽኑ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ ለውጥ እንዲሁም ከጊዜ ጊዜ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት መስፋት ምክንያት፣ የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችንና የእርሻ መሣሪያዎችን ለማቅረብ እንዲሁም የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት በመቸገሩ ነው፡፡

በመሆኑም የኮርፖሬሽኑን ማቋቋሚያ ካፒታል አቅም ማሳደጊያ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶና በኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ይሁንታ አግኝቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያገኝ፣ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ለአጭር ጊዜ መፍትሔ በመንግሥት ዋስትና ብድር በመውሰድ የግብርና ግብዓቶችን አቅርቦ በመሸጥ ብድሩን የመክፈል ዕቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ሥር ሲተዳደር የነበረ ሲሆን፣ ከግንቦት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል፡፡

ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉና ለዘመናዊ እርሻና አግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት የሚሆኑ፣ ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርብ የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ፣ በመላው አገሪቱ 25 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና አምስት የእርሻ ጣቢያዎች እንዳሉትና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 62 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የማዳበሪያ ግዥዎችን መፈጸሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -