የተበላሹ ብድሮች ጤናማ ሆነው እንዲመለሱ ከማድረግ ጎን ለጎን አዳዲስ ብድሮች በፍጥነትና በጥራት እንዲለቀቁ የማድረግ ሥራ እየሠራሁ ነው ያለው ልማት ባንክ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ከቀደሙት ሁለት ዓመታት ብልጫ ያለው ብድር ለማቅረብ መወጠኑን አስታውቋል፡፡
በ2015 የበጀት ዘመን ልማት ባንክ 30 ቢሊዮን ብር ብድር ለመልቀቅ ማቀዱን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) የገለጹ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 22 ቢሊዮን ብር አፅድቆ ለተበዳሪዎች አገልግሎት መስጠቱ ተገልጿል፡፡
ባለፈው ሳምንት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር በልማት ባንክ ላይ ባጠናቀረው የ2014 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ፣ የልማት ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 22.9 ቢሊዮን ብር ለማበደር አቅዶ የለቀቀው ብድር ግማሽ ያህሉ (50 በመቶ) መሆኑ ተጠቅሶ ይህ ለምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡
የፀደቀው ብድር 22 ቢሊዮን ደርሷል ሲባል የራሱ የሆነ የሥርጭት ጊዜ ወጥቶለት የሚሰጥ መሆኑን፣ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በግምገማው ወቅት ያብራሩ ሲሆን፣ ይህም በመጀመሪያ ያለው የኮንስትራክሽን ደረጃ ሲባል፣ ብድር በአነስተኛ የሚሠራጭበት መሆኑን አንስተው፣ ቀጥሎ የማሽነሪዎች ግዥ የሚደረግበትና ትልቅ ብድር የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ለዚህ የሚለቀቀው ብድር በዚያው ዓመት ካለመሠራጨቱ ጋር በተያያዘ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡ ብድር ማፅደቁና መልቀቁ ቀጥታዊ ግንኙነት ያላቸው አለመሆኑ ከግምት ሊያዝ እንደሚገባ የባንኩ ኃላፊዎች በግምገማ ወቅት ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት የበጀት ዓመታት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባንኩ እንዳሠለጠነ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ለጋዜጠኞች የተናገሩት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ወጣቶች ብዙኃኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ፕሮፖዛላቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝምም በርካታ ፕሮጀክቶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 4.2 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2014 የበጀት ዓመት 3.8 ቢሊዮን ብር ያተረፈው የፖሊሲ ባንኩ፣ የተበላሸ ብድር ከማስመለስ ባሻገር የተለያዩ ብድሮችን እየሰጠ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ዮሐንስ (ዶ/ር) ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ልማት ባንክ ባለፈው ሳምንት ዓመታዊ አፈጻጸሙን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ኃላፊዎች ባሉበት በሒልተን ሆቴል ባስገመገመበት ወቅት በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠሩበት ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ለአብነትም በትግራይ ብቻ የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር አሥር ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ልማት ባንክ 4.1 ቢሊዮን ብር መጠባበቂያ ከትርፉ ላይ ለመያዝ መገደዱን፣ ይህም ትርፉን ከ7.8 ቢሊዮን ብር ወደ 3.7 ቢሊዮን ብር እንዲወርድ ማድረጉ ታውቋል፡፡
ቅርንጫፎችን ከማስፋፋት ጋር በተገናኘ በሱማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉልና በመሳሰሉት ክልሎች የባንኩ የቅርንጫፍ ሥርጭት የሳሳ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በሌሎቹም ክልሎች ያሉት ቅርንጫፎች በቂ አይደለም የሚለውን በጥናት በመለየት ተጨማሪ 30 ቅርንጫፎችን በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ተብሏል፡፡ በዚህም 78 የሆኑትን ቅርንጫፎች በተያዘው ዓመት ወደ 108 ከፍ እንደሚል ተገልጿል፡፡
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር በልማት ባንክ ላይ ባጠናቀረው የ2014 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ፣ የባንኩ ታማሚ ብድር በአሁኑ ጊዜ 19.2 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ከእዚህም ውስጥ 48.5 በመቶ ሊሰበሰብ የማይችል (Loss)፣ 33.8 በመቶ ደግሞ አጠራጣሪና 18 በመቶው ከደረጃ በታች ብድሮች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡