Friday, September 22, 2023

ዳግም ምዝገባ ያላደረጉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ ደንብ ሲፀድቅ እንደሚሰረዙ ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በ2011 ዓ.ም. መፅደቁን ተከትሎ ዳግም ያልተመዘገቡ ከ1,500 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት የቀረበው የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ሲፀድቅ እንደሚሰረዙ ተገለጸ፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የደንቡን መፅደቅ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ ደንቡ ሲፀድቅ ድርጅቶቹን ሰርዞ ንብረታቸውን እንደሚወርስ አስታውቋል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ከ3,500 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የነበሩ ሲሆን፣ አዋጁ በፀደቀ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነባሮቹ ድርጅቶች እንደ አዲስ መመዝገብ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡

ባለሥልጣኑ በአዋጁ መሠረት የዳግም ምዝገባ ሥርዓት ዘርግቶ ጥሪ ማድረጉን ያስታወሱት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፣ አንድ ዓመቱ ሲጠናቀቅ መመዝገብ ከነበረባቸው ከ3,500 በላይ ድርጅቶች ውስጥ በድጋሚ የተመዘገቡት 1,832 እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ 

አቶ ፋሲካው፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ዳግም ምዝገባ ያልፈጸመ ድርጅት ሕጋዊ ሰውነት እንደሌለው እንደሚቆጠር ገልጸው፣ ከ1,700 በላይ የሚሆኑት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቀነ ገደቡ እንዳለፋቸው አስረድተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እነዚህን ድርጅቶች ፈቃድ ለመሰረዝ እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ 147 የሲቪል ማኅበሰረብ ድርጅቶች ለዳግም ምዝገባ ማመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ነገር ግን የተቀመጠው የአንድ ዓመት ቀነ ገደብ በመጠናቀቁ የሚስተናገዱበት ሕግ አልነበረም፤›› በማለት የነበረውን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ፋሲካው ገለጻ ባለሥልጣኑ ድርጅቶቹን ከመሰረዝ ይልቅ ለጊዜውም ቢሆን የሚመዘገቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ‹‹የዘገየ የዳግም ምዝገባ ክፍያ››ን ያካተተ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ደንብ መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኒስቴሮች ምክር ቤት አፅድቋል፡፡

በደንቡ ላይ ዳግም ምዝገባ ያላከናወኑ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የአገር ውስጥ ከሆኑ 3,000 ብር የውጭ ከሆኑ ደግሞ 1,000 ዶላር ክፍያ በመፈጸም መመዝገብ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡

በዚህም መሠረት ጊዜው ካለፈ በኋላ ካመለከቱት 147 ድርጅቶች ውስጥ 29 የሚሆኑት ምዝገባውን እንዳጠናቀቁና 94 የሚሆኑት በሒደት ላይ እንደሆኑ አቶ ፋሲካው ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ባለሥልጣኑ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት አዘጋጅቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የላከው የአዋጁ ማስፈጻሚያ ደንብ፣ ቀድሞ የነበሩ አሠራሮችን ሽሮ አዲስ አሠራሮችን የሚዘረጋ በመሆኑ ከደንቡ መፅደቅ በኋላ የዳግም ምዝገባ እንደማይከናወን ተናግረዋል፡፡

‹‹ይሄ ደንብ ሲወጣ ወዲያውኑ የዳግም ምዝገባ ጉዳይ ይቆማል፡፡ ደንብ ደግሞ የሚኒቴሮች ምክር ቤት በቅርቡ አጀንዳ ያደርገዋል ብለን እየጠበቅን ነው፤›› ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ደንቡ እስካሁን ያልፀደቀው ምክር ቤቱ ለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ደንቡን ስለምንፈልገው በአፋጣኝ እንዲፀድቅ እየገፋን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ፍትሕ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ አጀንዳ አድርጎ መወያየት ብቻ ነው የሚቀረው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ዳግም ምዝገባ ስላልፈጸሙት ድርጅቶች ሙሉ መረጃ አጣርቶ እንደያዘና የሀብት መጠናቸው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች እንዳሉት አቶ ፋሲካው ገልጸዋል፡፡

‹‹በቅርቡ ያልተመዘገቡትን ድርጅቶች ስም ዝርዝር በጋዜጣና በሶሻል ሚድያ እናወጣለን፡፡ ጎን ለጎን ሀብታቸውን የማጥራት ሥራ እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡

ከድርጅቶቹ የሚወረሰው ሀብት ባለሥልጣኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በፋይናንስ ለመደገደፍ ወደአቋቋመው የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በወጣው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ላይ በባለሥልጣኑ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ከሚፈርሱ ድርጅቶች የሚገኝ ንብረት ከፈንዱ ገንዘብ ምንጮች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት 587 አዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ያገኙ ሲሆን፣ 76 ድርጅቶች ደግሞ በምዝገባ ሒደት ላይ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -