Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አንፃር ‹‹ያልተረጋጋ›› መሆኑን ምሁራን ተናገሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት፣ መንግሥት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ቢወሰድም፣ ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አንፃር ‹‹ያልተረጋጋ›› መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ነሐሴ 27 እና 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ባዘጋጀው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የዳሰሰ የፖሊሲ ውይይት፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ የመሬት ፖሊሲ፣ ግጭትና የድህረ ግጭት ኢኮኖሚ ማገገሚያ መንገዶች እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአሶሼሽኑ አባል የሆኑትና በኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር የፖሊሲ ተመራማሪ ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ የማክሮ ‹‹ኢኮኖሚ መረጋጋት በኢትዮጵያ›› የሚል ጥናት አቅርበዋል፡፡

‹‹የአንድ አገር ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ነው የሚባለው ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው?›› የሚለው ዝርዝር ወጥቶ፣ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ጥናት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ተገማችና የማይዋዥቅ ግሽበት፣ ትክክለኛ የወለድ ምጣኔ፣ የተረጋጋ የፊስካል ፖሊሲ፣ የተሻለ የክፍያ ሚዛን፣ ተወዳዳሪና ተገማች የምንዛሪ ተመን ምን ይመስላል? በሚሉት መመዘኛዎች ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት በተለይም አገሪቱ ከዓለም አቀፍና አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትሉ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋ አይደለም ተብሎ የሚገለጽበት ድምዳሜ ላይ መደረሱን ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ተብለው በመንግሥት የተተገበሩ ሥራዎች ምን ዓይነት ውጤት አምጥተዋል የሚለው ጥናት እንደተደረገበት የተናገሩት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ገበያ ተፅዕኖ (ፋይናንሺያል ሪፕሪዥን)፣ የመንግሥት የክፍያ ሚዛን (ባላንስ ኦፍ ፔይመንት)፣ የመንግሥት በጀት አጠቃላይ ይዘቱ ምን ይመስላል የሚሉት ጉዳዮች በተደረገው ጥናት ተዳሷል ብለዋል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለማንሳት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመፍታት መንግሥት ላለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የአገር በቀል ሪፎርም ሥራዎች የተወሰነ ውጤት ማምጣቱን ያነሱት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን በአገሪቱ የተከሰተው ጦርነት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንቅስቃሴውን አደናቅፎታል ብለዋል፡፡

እንደ ፖሊሲ ተመራማሪው በአገሪቱ የተከሰተው ጦርነት ካደረሳቸው ጉዳቶች ውስጥ የዋጋ ንረትን በማባባስ ትልቅ ተፅዕኖ ማድረጉ ሲሆን፣ ይህም አምራች የሆኑ አካባቢዎች የሚያመርቱትን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረብ ባለመቻላቸው ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በምርትና ምርታማነት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በአገር የክፍያ ሚዛን ባሳደረው ተፅዕኖ ምክንያት የውጭ ኢንቨስትመንት መቀነሱ ተመላክቶ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከሁለት እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከዚህ ቀደም የሚያድጉ የነበሩ ዘርፎች የመቀነስ ዝንባሌ ከማሳየታቸው ጋር የሚያያዝ መሆኑን ቴዎድሮስ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ጥናት አቅራቢው እንዳስረዱት ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ አገሮች እንደሚጋጥማቸው፣ የኢኮኖሚ ቀውስ (ሾክ) ሁለት ዓይነት ጉዳዮች መኖራቸውን የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ውስጣዊና ውጫዊ (ኤግዞጅነስና ኢንዶጅነስ ሾክስ) የሚባሉት ናቸው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ላይ ነው፡፡ ያንን መለዋወጥ ይቻላል? ወይስ ከኢኮኖሚው ውጪ ያሉ ነገሮች ናቸው? አሊያም ኢኮኖሚው ሊቆጣጠር ከሚችላቸው ውጪ ነው? የሚሉት ሊታዩ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወይም ፖሊሲ አውጪዎች ሊቆጣጠሯቸው ከሚችሏቸው ውጪ ያሉ ነገሮች፣ ማለትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የፖለቲካ ግጭት (ከኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጪዎች የማያመጡት)፣ የዩክሬይን ሩሲያ ጦርነት ውጭ መሆናቸውን የተናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ በእነዚህ ጉዳዮች የተነሳ ተፅዕኖውን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻል ሊያመጣቸው የሚችላቸውን ውጤቶች እንዳይመጡ (የመቋቋም አቅም ለማሳደግ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ አንዱ ሲሆን ይህንን የገቢ ምርት አጠቃቀምን (ኢምፖርት) በመለዋወጥና በማስተካከል፣ የአስቸኳይ (ኤመርጀንሲ) ጊዜ ሕጎችን በማውጣት መሠረታዊ ወይም ግዴታ የሆኑ ነገሮችን በማስመጣት የመጣውን የዋጋ መጨመር መቋቋም የሚቻል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሌሎች አገሮች አንፃር አነስ ያለ ቢሆን በሌሎች አገሮች ላይ የተነሳው ችግር ተፅዕኖ የሚፈጥርባት አገር እንደመሆኗ ከላይ የተገለጹት ዓይነት ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ተብሏል፡፡

ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በዋነኛት የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሰው የገንዘብ ልቀት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ መንግሥት የገንዘብ ልቀትን መቆጣጠር ቢችልም፣ ያጋጠሙት ቀውሶች ማለትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ አገራዊ ግጭቱ፣ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት እንደልቡ መቆጣጠር እንዳይችልና በአገራዊ ግጭቱ ሳቢያ ለሚደርሰው ውድመት መልሶ ማልማት ግንባታ ገንዘብ እንዲፈልግ ያስገደደው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች