የኢትዮጵያ ወጣቶች ታሪካዊ አደራ አለባቸው፡፡ ይህ አደራ ከአያቶቻቸውና ከቅድመ አያቶቻቸው የተረከቧትን ጥንታዊት ኢትዮጵያ፣ ለመጪው ትውልድ በክብር የማስረከብ ኃላፊነት ነው፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን ተስፋፊዎችንና ወራሪዎችን አንበርክከው አገራቸውን ለሌላው ትውልድ ያስረከቡት፣ ከምንም ነገር በፊት ለአገራቸው በነበራቸው ከፍተኛ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያለ ምንም ግዴታ ሕይወታቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ አድርጓቸዋል፡፡ ከዓድዋ በፊትም ሆነ በኋላ በተደረጉ በርካታ ጦርነቶች ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው፣ አገራቸውን በዓለም አደባባይ የነፃነት ተምሳሌት ያደረጓት ከእሷ በፊት ምንም የሚቀድምባቸው ነገር ስላልነበረ ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን ወጣቶችም ይህንን ተምሳሌታዊ አርዓያነት በማንገብ አገራቸው ኢትዮጵያን ከግጭት የነፃች፣ ከድህነት የተገላገለችና በኩራት የምትረማመድ ለማድረግ ጠንክረው መነሳት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ጠልፎ የጣለውን ብልሹ አሠራር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ፣ ምስኪን ሕዝባቸውን ከዘመናት መከራ የሚገላግል መልካም ተግባር የመፈጸም ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከግጭትና ከድህነት ማጥ ውስጥ የምትወጣው ወጣቶቿ በኅብረት ሲነሱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለታሪካዊ አደራ ዝግጁ ይሁኑ፡፡
በከፋ ድህነት ውስጥ የምትኖር አገር በርካታ ሚሊዮኖች በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በመቸገራቸው የዕርዳታ እህል ይለመንላቸዋል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ከሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ አብዛኛው በአስከፊ ድህነት ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ በልቶ ለማደር ካለው ትግል በተጨማሪ በመኖሪያ ቤት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ችግር ምክንያት የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከከፋ ድህነት ውስጥ ለመውጣት እንዲቻል ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ሆነው ቢጀመሩም፣ በአገሪቱ ውስጥ በተንሰራፋው የፖለቲካ ችግር ሳቢያ በሚፈጠሩ ግጭቶችና የለየለት ጦርነት የብዙዎች ሕይወት ተመሰቃቅሏል፡፡ ውድ ሕይወታቸውን ካጡ በርካታ ንፁኃን ጀምሮ ንብረቶቻቸው ወድመው ቀዬአቸውን ለቀው እንዲሰደዱ የተገደዱ ወገኖች በሚሊዮኖች ይቆጠራሉ፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት መዋል የሚገባው የሰው ኃይል፣ ዕውቀት፣ ገንዘብና ጊዜ በከንቱ እየባከነ ነው፡፡ የሚሊዮኖችን ሕይወት መለወጥ የሚገባው የአገር አንጡራ ሀብት ለጦርነት እየዋለ፣ መጪው ጊዜ ከተስፋ ይልቅ ሥጋት እያጠላበት ስለሆነ ወጣቶች ይነሱ፡፡
የኢትዮጵያን ለዘመናት ከተጣባው የጦርነት ታሪክ አላቆ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የሚያስችለው ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም ግን የጦረኝነት አስተሳሰብ የተፀናወታቸው ኃይሎች ከፖለቲካው መገለል ይኖርባቸዋል፡፡ መጪው ጊዜ የወጣቶች መሆን የሚችለው ከጦርነት ጋር ተጣብቀው የኖሩ ጀብደኞች ገለል ሲደረጉ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር አዲሱ ትውልድ መረከብ ይኖርበታል፡፡ በተበላሸው የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የቆዩ ሰዎች፣ አሁንም ከስህተታቸው ለመማር ስለማይፈልጉ ከተቻለ በክብር ካልሆነ ግን በግድ በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የቅራኔ ማምረቻ ከመሆን ወጥቶ ለብሔራዊ ጉዳዮች መተባበሪያ እንዲሆን፣ የዘመኑ ወጣቶች በአዲስ አስተሳሰብ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛ ፖለቲካ ማራመድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም ሳይጎድላት ለዘመናት በድህነት ውስጥ የምትዳክር አገርን የጦርነት ዓውድማ ማድረግ ወንጀል መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በቅንነትና በትብብር መንፈስ ሊሠሩ የሚችሉ ዘመናዊ ፖለቲከኞች እንጂ፣ ዕድሜያቸውን በሙሉ ከሴረኝነት የማይላቀቁ ኋላቀር ፖለቲከኞች መፈንጫ መሆን የለባትም፡፡
አዲሱ ትውልድ ራሱን በትምህርት እያበለፀገ አገሩን ለማሳደግ በቁርጠኝነት መነሳት አለበት፡፡ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ እንደሆነ የሚገመተው ይህ ትውልድ፣ ዕድሜ ለዘመኑ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች አገሩን በአጭር ጊዜ አልምቶ የሀብት ሰገነት ላይ ማውጣት አያቅተውም፡፡ በብሔር፣ በእምነት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በፖለቲካ አቋም ወይም በሌሎች ምክንያቶች የሚያጋጥሙትን ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ አስተናግዶ ለመፎካከር ምንም የሚያግደው ነገር የለም፡፡ አገሩን ከራሱና ከሚያራምደው ዓላማ በላይ በማክበር በቅንነት ለማገልገል ችግር የለበትም፡፡ ከመሀሉ በሴራ ፖለቲካ ተጠልፈው ያልሆነ ጎዳና ውስጥ የገቡትን በማረም፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሥልጡኖች መፎካከሪያ እንዲሆን የማድረግ ተልዕኮን መቀበልም ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ልዩነት ሲኖር በተሻለ ሐሳብ በልጦ መገኘት ሲቻል፣ ጠመንጃ አንግቦ ይዋጣልን ከሚል የግብዞች አስተሳሰብ መላቀቅ የትውልዱ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም በነፃ አውጪነት ስም ሲያጭበረብሩ የነበሩ ማንን ሲጠቅሙና ለማን ሲሠሩ እንደነበር ስለሚታወቅ፣ በሕዝብ ስም መቆመርም ሆነ ማጭበርበር ሊበቃው ይገባል፡፡ በሕዝብ ስም የግልና የቡድን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት በወጣቶች ስም መነገድም ማብቃት አለበት፡፡
ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ያላት አገር ማድረግ የሚቻለው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ በብዛት ገብተው በዘመናዊ አስተሳሰብ ሲፎካከሩ ነው፡፡ ይህ ፉክክር የፖለቲካ የጨዋታ ሕጎችን ያከበረ፣ በጠላትነት የማያስተያይ፣ ለግጭት በር የማይከፍት፣ ሌብነትንና ዝርፊያን የሚፀየፍ፣ ኢፍትሐዊነትን የሚያስወግድ፣ ሰብዓዊነትን የሚያስቀድምና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች የተገዛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ ክፋት፣ ሴራ፣ ደመኝነትና ውሸትን የሚያስወግድ ነው፡፡ ወጣቶች ለዘመናት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታወቀው ብልሹ የፖለቲካ ባህል ሲላቀቁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከራ ጊዜ በሚገርም ፍጥነት ያጥራል፡፡ ምግብ በልቶ ማደር ብርቅ የሆነበት አብዛኛው ሕዝባችን፣ ከራሱ ተርፎ ለሌሎች የሚተርፍበት ዕድል ይፈጠርለታል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ገጽታዋ ይለወጣል፡፡ በተመፅዋችነት፣ በጦርነት፣ በእርስ በርስ ክፍፍልና በትርምስ የሚታወቀው አስከፊ ገጽታ ሲለወጥ ኢትዮጵያ ተደማጭ ትሆናለች፡፡ የልመና ስልቻ ይዞ ክብር የለም፡፡ እርስ በርስ እየተፋጁ ፈላጊ አይኖርም፡፡ ይልቁንም ያደፉ ታሪካዊ ጠላቶች የባሰ ዕልቂትና ውድመት እንዲደርስ መልካም አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ሁኔታ ውስጥ መውጣት አለባት፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶ ከአሁን በኋላ ለግጭትና ለእርስ በርስ ጥላቻ የሚዳርጉ አጉል ድርጊቶችን መታገስ የለባቸውም፡፡ በዓለም ፊት ኃፍረት ውስጥ የሚከቱ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዘረፋዎችና የንብረት ውድመቶች አያስፈልጉንም ማለት አለባቸው፡፡ የገዛ ወገንን በአገር ውስጥ በማፈናቀል በጦርነት ከወደሙት ሶሪያና የመን በላይ በመሆን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ መፈረጇ፣ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን እንደ እግር እሳት ማንገብገብ አለበት፡፡ ስንትና ስንት ገድሎችን መፈጸም የሚችሉ ኩሩና አስተዋይ ኢትዮጵያውያን እያሉ፣ ለአገር ምንም ደንታ የሌላቸው ትርምስ እንዲፈጥሩ ዕድል መሰጠት የለበትም፡፡ ይልቁንም ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሐሳብ ከየትም ይምጣ በነፃነት እንዲደመጥ መታገል ተገቢ ነው፡፡ ወጣቶች ከጉልበተኝነት ይልቅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር፣ መከራከርና መደራደር መልመድ አለባቸው፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ መተማመን እንዲኖር የውይይት ባህል ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሴራ ፖለቲከኞች አገር የሚያጠፉት የውይይት ባህልና መተማመን እንዳይኖር በማድረግ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ማምጣት የሚቻለው በመተባበር ስለሆነ ለሥልጡን ውይይት መዳበር ወጣቶች ይታገሉ፡፡ መጨው ጊዜ ብሩህ የሚሆነው ወጣቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ግጭትና ድህነትን ለማስወገድ ዝግጁ ይሁኑ!