- በስድስት ኩባንያዎች ላይ ክስ መሥርቷል
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ትርፍ ያስመዘገበው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ በፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ ባለሀብቶች መሰብሰብ የነበረበትን 12 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ መቸገሩን አስታወቀ፡፡
ያልተሰበሰበው የገንዘብ መጠን አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ 629.64 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን፣ ይህም ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት ካተረፈው 340.3 ሚሊዮን ብር በ289.54 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ክፍያ ያልፈጸሙ ኢንቨስተሮችን ከፓርኮቹ ውስጥ ከማስወጣት ይልቅ ክፍያ እንዲፈጽሙ የማግባባት ሥራ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለመንቀሳቀስ ውል ከገቡ በኋላ ሥራ ሳይጀምሩ ክፍያም ያልፈጸሙ ስድስት ኩባንያዎች ላይ ደግሞ ክስ መመሥረቱን አስታውቋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ 12 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አለመሰብሰቡን የገለጹት ሐሙስ ሐምሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የኮርፖሬሽኑን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድን ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በሂልተን ሆቴል ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጻ ያልተሰበሰበው ገቢ ክምችት በዚህ ደረጃ የደረሰበት ዋነኛ ምክንያት፣ በ2012 ዓ.ም. የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ በቅድሚያ ለሦስት ወር በኋላም ለተጨማሪ ሦስት ወር በተሰጠው ዕፎይታ ሳቢያ ነው፡፡ ‹‹ይህ ተሰብሳቢ ገቢ ባለፈው ሦስትና አራት ዓመት የተጠራቀመ ነው›› ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ ያልተሰበሰበ ገቢ ክምችቱ ኮርፖሬሽኑ ጉዳዩን “ሲያስታምም” በመቆየቱ የተጠራቀመ መሆኑን በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በተመራው የግምገማ መድረክ ላይ አስረድተዋል፡፡
ኢንቨስተሮቹ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል የገቡት በየወሩ የኪራይና የአገልግሎት ክፍያ እንዲፈጽሙ፣ ይህ ካልሆነም በሦስተኛው ወር የሚሰጣቸው አገልግሎት እንደሚቋረጥ ስምምነት ተፈጽሞ መሆኑን አቶ ሳንዶካን ገልጸዋል፡፡
‹‹ኢንቨስተሮቹ ክፍያ ሳይፈጽሙ አምስትና ስድስት ወር ሲጠራቀም ማድረግ የምንችለው የመጀመሪያ ነገር የምናቀርበውን አገልግሎት ማቆም ቢሆንም፣ ግን ይህ ፕሮፌሽናል ውሳኔ አይደለም፣ ሥራውንም አያስቀጥልም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በፓርኮቹ ውስጥ የተሰማሩት እነዚህ ኩባንያዎች “ትላልቅ ብራንዶች” እንደሆኑ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽኑ የኩባንያዎቹ “ስም እንዳይበላሽ” በማሰብ ዕርምጃ ከመውሰድ መቆጠቡን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ኩባንያዎቹ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹ከሦስት ወር በላይ ሳይከፍሉ የቆዩ ኩባንያዎችን ሁሉ ካስወጣን፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚቆይ ኢንቨስተር አይኖርም›› በማለት ጉዳዩን አብራርተዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ ጉዳዩን “ለማስታመም” በማሰቡ ገቢው አለመሰብሰቡ የኮርፖሬሽኑ ድክመት ተደርጎ እንዳይቆጠር ጠይቀዋል፡፡
ካልተሰበሰበው 12 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ 30 በመቶ ገደማው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር የሚያያዝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በመቀሌ ከተማ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ 15 ሼዶችን ከተከራዩ ኢንቨስተሮች ሒሳብ አለመሰብሰቡ የተሰብሳቢ ሒሳቡን ክምችት ከፍ እንዳደረገው አቶ ሳንዶካን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ሥራ ቆሞ የነበረ ቢሆንም ገቢው ከኮርፖሬሽኑ የሒሳብ መግለጫ (Financial Statement) ላይ እስካልተነሳ ድረስ መገኘት የነበረበት የኪራይና የአገልግሎት ክፍያ እንደተሰብሳቢ ሒሳብ እንደሚቆጠር አስረድተዋል፡፡
ተሰብሳቢ ገቢው ከመግለጫው ላይ መሰረዝ የሚችለው በገንዘብ ሚኒስቴርና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሲታመንበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኮርፖሬሽኑ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ይህንን የማስፈጸም ዕቅድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ክስ የመሠረተባቸው ስድስት ኩባንያዎች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ ስማቸውን ከመጥቀስ ተቆጥበው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ፍርድ ቤት የወሰድናቸው ምርት ላይ ያልሆኑ፣ ስምምነቱን ያላፈረሱ፣ ለመክፈልም ፈቃደኛ ያልሆኑ ኢንቨስተሮችን ነው›› ብለዋል፡፡
ቀሪዎቹን ኢንቨስተሮች በተመለከተም፣ ‹‹የማስታመም ሥራዎችን እየሠራን ነው የምንቀጥለው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑን ዋጋ በሚያስከፍል ሁኔታ መሆን የለበትም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
13 የመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ከሰመራና ከመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ የሚያስተዳድራቸው 11 ፓርኮች በሥራ ላይ ናቸው፡፡ በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ ካሉት 177 ሼዶች ውስጥ 98 ያህሉ ተከራይተው በማምረት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ ከሼዶች ኪራይ፣ ከለማ መሬት ሊዝ፣ ከምክርና ሥልጠና፣ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች 340.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ካገኘው 1.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ 639 ሚሊዮን ብር የሆነውን ትልቁን ገቢ ያገኘው ለኩባንያዎች ካከራያቸው ሼዶች ነው፡፡ ከሼዶች ኪራይ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት በ126 በመቶ ያደገ ነው፡፡