Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፌዴሬሽኑ ምርጫ በፖለቲካዊ ጫናና ማስፈራሪያ የተከናወነ እንደነበር ተገለጸ

የፌዴሬሽኑ ምርጫ በፖለቲካዊ ጫናና ማስፈራሪያ የተከናወነ እንደነበር ተገለጸ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ በውድድር መሆኑ ቀርቶ ፖለቲካዊ ውሳኔ የተላለፈበት እንደነበር፣ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበው የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ ተናገሩ፡፡

ባለፈው እሑድ በተደረገው የፌዴሬሽኑ ምርጫ ላይ በሆነው ነገር ሁሉ ሳይታለሉና ሳይፈሩ ለመረጧቸው 27 ሰዎች ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ባለፈው እሑድ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ፣ ፌዴሬሽኑን ለቀጣይ አራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነትና በሥራ አስፈጻሚነት የሚያስተዳድሩ አመራሮች ምርጫ ማከናወኑ አይዘነጋም፡፡

ከአማራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ዕጩ ተወዳዳሪ በመሆን የቀረቡት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ‹‹የፌዴሬሽኑ ምርጫ የተከናወነበትን ሒደት የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በሰጡት በዚሁ መግለጫ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት እግር ኳስን የሚያስተዳድሩ አመራሮችን ለመምረጥ የምንሄድበት መንገድ ፍፁም ዘመኑን የማይመጥን ከመሆኑም ባሻገር፣ በከፍተኛ ሁኔታ ስፖርቱን የሚጎዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ መላኩ የምርጫውን ሒደት አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ‹‹ምርጫው በፖለቲካ ተፅዕኖም ይሁን በገንዘብ እንዲፈጸም ማድረግ ለጊዜው እግር ኳሱን ሳይሆን ተመራጩን አካል ቢጠቅም፣ አዋጪ ግን አይደለም፡፡ አክሳሪ ነው፤›› ብለው፣ ምርጫው ከመከናወኑ አንድ ቀን በፊት ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየሄዱ ስለመሆኑ ጭምር የተረዱበት ሁኔታ እንደነበርም አልሸሸጉም፡፡

‹‹አንዳንድ መራጮች ከምርጫው በኋላ በአካል ተገናኝተን እንደነገሩኝ፣ በነበረው ሁኔታ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ፣ ከፍተኛ በሆነ ፖለቲካዊ ማስፈራሪያና ጫና ሳይወዱ በግድ ድምፅ እንዲሰጡ መደረጋቸውን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ምርጫው ነፃና ገለልተኛ ቢደረግ ኖሮ፣ መራጩ ለእግር ኳሱ የሚበጀውን ዓይቶና መዝኖ በምክንያት መምረጥ እንደሚችል ለኅብረተሰቡ መግለጽ የሚያስፈልግ ከመሆኑም ባሻገር፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የማይበጅ በመሆኑ ለቀጣይ ዕርምት እንዲደረግበት በማሰብ ጭምር መግለጫውን መስጠት እንደፈለጉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከረቡዕ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የነበሩ ዕፀፆችና ተግዳሮቶች ገልጸን መታረም እንዳለበት ተናግረናል፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ በነበረው አካሄድ ሁኔታ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ጭምር እንዲታወቅ የሆነበትን አጋጣሚ ነው ያስረዱት፡፡

‹‹በዋናነት ዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ምሽቶች፣ ትልልቅ ሆቴሎች፣ የአንዳንድ ትልልቅ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ሳይቀር የድርድር ቦታዎች፣ ክፍያ መፈጸሚያዎች፣ እንዲሁም የቢሮ ስልኮች ፖለቲካዊ ትዕዛዞች የሚሰጥባቸው፣ በተለይም ለመራጮች ፖለቲካዊ ማስፈራሪያና መመርያ የሚተላለፍባው መሆናቸው የተሟላ መረጃ በእጃችን ገብቷል፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ያውም በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገልና ለመምራት ይህ ሁሉ ግርግርና ውጣ ውረድ ለምን? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ለችግሩ መፍትሔ ሲሉ ያስቀመጡት አቶ መላኩ፣ አሁን ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ መዋቅራዊ አደረጃጀት ተፈትሾ፣ ጉባዔው የእግር ኳሱን ትክክለኛ ባለሙያ የሚጋብዝ ሆኖ ሊዋቀር እንደሚገባ አልሸሸጉም፡፡

እግር ኳሱ የሚመለከታቸው አካላት በዋናነት ክለቦች፣ ከከተማ ከንቲባና ከዞን አስተዳዳሪ ነፃ ሆነው በገቢ ራሳቸውን የሚያጠናክሩበት መዋቅር ሊኖር እንደሚገባ የገለጹት አቶ መላኩ፣ ‹‹በተለይ የከተማ ክለቦች የሚያስተዳድሯቸውና በጀትም የሚመደብላቸው በከተማ አስተዳደር በመሆኑ፣ ለችግሩ መሪ ተዋንያን ማለትም ለፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ቅርብ በመሆናቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የክለቦችን ሚናና ድርሻ ታሳቢ በማድረግ፣ የተጠቀሱት የፖለቲካ አመራሮች በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሊኖራቸውን የሚችለውን ድርሻ በመለየት አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ እንዲሁም ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ክለቦችን ወክለው የሚመጡ የከተማ ከንቲባ፣ የዞን አስተዳደሪ ድርሻና ተፅዕኖ መቀነስ የሚቻልበትን አሠራር መቀየስ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን ወደ ክልሎች በማውረድ፣ የክልል ፌዴሬሽኖች የራሳቸውን ውድድር እንዲመሩና ምርጫን የሚመለከት ጠቅላላ ጉባዔ ሲመጣ፣ እዚያው በማን ሊወከሉ እንደሚገባ የሚወስኑበትን አሠራር ማበጀትና ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ክለቦችን በፋይናስ አቅማቸውን በማጠናከር ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ማውጣት የሚቻልበትን መዋቅራዊ ሥርዓት መዘርጋት ግድ ስለመሆኑ ጭምር አቶ መላኩ ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...