Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አገራችን ለሦስተኛ ጊዜ ተገዳ ወደ ጦርነት እየገባች መሆኑ በጣም ያንገበግበኛል፡፡ በቀን አንዴ ምግብ ለማግኘት ጣር በሆነባት አገር ውስጥ ምስኪኖችን የሚፈጀውና የሚያፈናቅለው ጦርነት እንደገና ተጀመረ ሲባል ያስደነግጣል፡፡ ይህ አውዳሚ ጦርነት በፍጥነት እንዲቆም ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት መከፈል አለበት እላለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያት አለኝ፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች ከአማራና ከአፋር አካባቢዎች ተመተው ወደ ትግራይ ሸሽተው ከሄዱ በኋላ፣ ሁለቱንም ክልሎች ተዘዋውሬ ጎብኝቼ ነበር፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች በየደረሱባቸው ሥፍራዎች ያደረሱት ዕልቂትና ውድመት እንደገና ሊደገም መሆኑን ሳስታውስ፣ ያኔ በአካል ተገኝቼ ያየሁት ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ፊቴ ድቅን ይላል፡፡

በመጀመሪያ በአማራ ክልል የደቡብ ወሎና የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ገጠር ድረስ ገብቼ የተመለከትኩዋቸው የጥፋት ድርጊቶች፣ በሕይወቴ ፈፅሞ የማልረሳቸው አሳዛኝና ቅስም ሰባሪ ነበሩ፡፡ እነዚያ ምስኪን ወገኖቼ ከአንድ ቤት እስከ ሰባትና ስምንት የቤተሰብ አባሎቻቸው የተገደሉባቸው፣ ጎጆዎቻቸው የተቃጠሉባቸው፣ እርሻዎቻቸው የወደሙባቸው፣ ከብቶቻቸው ከመታረድ አልፈው በጥይት ተደብድበው የተገደሉባቸውና በአጠቃላይ ከሰብዓዊ ፍጡራን የማይጠበቁ ወንጀሎች የተፈጸሙባቸው ነበሩ፡፡ እነዚህን ምስኪን ወገኖቼን ሳይ ራሴን መቆጣጠር እንዳቃተኝ መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡ በአፋር ክልል በነበረኝ ቆይታም ተመሳሳይ ሰቆቃና ምስቅልቅል ነበር ያየሁት፡፡ ሕፃናት ያለ ወላጅ፣ አረጋውያን ያለ ጧሪና ቀባሪ ከመቅረታቸውም በላይ፣ በእንስሳቶቻቸው ላይ የተፈጸመው ፍጅት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ እነዚህ ወገኖቼ ያሳለፉት ሥቃይ ቃላት ከሚገልጹት በላይ ነበር፡፡

የፌዴራል መንግሥት ትግራይ ገብቶ ይህንን ሁሉ ዕልቂትና ውድመት ያደረሱ የወያኔ ጉዶችን ይፋረዳል ብለን ስንጠብቅ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ወሰኖች ላይ የመልሶ ማጥቃቱን ዘመቻ መግታቱ ብዙዎችን እንዳበሳጨ አይዘነጋም፡፡ መንግሥት በዚያን ጊዜ መልሶ ማጥቃቱን ወደ ትግራይ ክልል አስፋፍቶ ላለመቀጠሉ ራሱን የቻለ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያት እንዳለው ብረዳም፣ ይህ ኃይል እንደገና ራሱን አጠናክሮ ቆቦ ድረስ መጥቶ መውረር የሚችል አቅም ሲገነባ ዝም ብሎ ማየቱ በጣም ድንቅ ይለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከወጣቶች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ትግራይ ውስጥ እየተሽሎኮለኩ እየገቡ የጦር መሣሪያ የሚያራግፉ አውሮፕላኖችን በተመለከተ የተናገሩትን ሳስብ ግራ መጋባቴ በጣም ይጨምራል፡፡ አገር ሊያጠፋ የተነሳ ወንበዴ ራሱን ሲያጠናክር ዝም ብሎ ሲታይ ነበር፣ ወይስ እኔም ሆንኩ ሌሎች ወገኖቼ የማናውቀው ነገር ይኖር ይሆን ብዬ ከራሴ ጋር እወዛገባለሁ፡፡ ለማንኛውም ይህንን ጉዳይ ጊዜ ይፍታው ብዬ ባልፍ ይሻለኛል፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት ይህንን አስከፊ ጦርነት በእንጭጩ መቅጨት አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው ሰላማዊ መንገድ ረግጦ እሳት ጨብጦ የመጣውን የሕወሓት ጉጅሌ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጉልበት በማንበርከክ ነው፡፡ መንግሥት ሰላም ሊገባው ከማይችለው ጦረኛ የአዛውንቶች ቡድን ጋር የጀመረውን የማይሳካ አጉል ወሬ ትቶ፣ ጀግናውን ሕዝባችንንና የመከላከያ ሠራዊታችንን ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በማቀናጀት የመጨረሻውን ማጥቃት መጀመር አለበት፡፡ ቆቦ ድረስ የመጣው የሕወሓት ጀሌ ወደ ወልዲያና ላሊበላ እንደገና እንዲገባ መፍቀድ ማለት፣ ከዚህ በፊት ከደረሰው ቀውስ የበለጠ እንደሚፈጠር መጠራጠር አይገባም፡፡ ያለፈው ጠባሳ ባልሻረበት በዚህ ጊዜ መልሶ ሕዝቡን ለዚህ አጥፊ ቡድን ማጋለጥ የአደጋውን አድማስ እንደሚያሰፋው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ በፊት የተሠሩ ስህተቶችን እንደገና እንዲደገሙ መፍቀድ ማለት፣ በአገራችንና በሕዝባችን ህልውና ላይ ከመቆመር አይተናነስም፡፡ በቀደም ዕለት ይህንን ጉዳይ አንስተን ከወዳጆቼ ጋር ስንነጋገር ነበር፡፡ እኛ ተምረናል የምንባል ኢትዮጵያን የመሰለች በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች አገር ምንም ስላልሠራንባት ብቻ ሕዝባችንን ለምግብ ተመፅዋችነት እንዳደረግነው፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ገበያ በምግብ አቅርቦት ብቻ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እየቻልን፣ እኛ ከዓለም ገበያ ስኳርና ዘይት እንዲሁም የተለያዩ ምግቦች ጠባቂ መሆናችን፣ ፖለቲካችንን በሠለጠነ መንገድ መምራት ተስኖን እርስ በርስ የምንጋደልና የምንሳደድ ገልቱ ሆነን መቅረታችንና በዚህ ዘመን ደግሞ ወሬ ላይ ተጥደን የአሉባልታ ተዋንያን በመሆናችን የደረሰብንን ክስረት በሰፊው አንስተን ተወያየን፡፡ ይህ አልበቃ ብሎን ችግራችንን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ስለማንችል ጦርነት አስነስተን ንፁኃንን ለአደጋ እናጋልጣለን፡፡

አንዱ በዕድሜ ታናሻችን የሆነ ወጣት ወዳጃችን አንድ የተከበረ ሰው በቅርቡ በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሠፈረውን በሞባይል ስልኩ ስክሪን ላይ አሳየን፡፡ እስኪ ጽሑፉን በአንክሮ አንብቡት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ብቻዋን በመጠን ከዩክሬን ሁለት እጥፍ የምትበልጥ አገር ናት! በሕዝብ ብዛትም እንደዚያው! በወጣት ቁጥርማ ኢትዮጵያ አጠገብ አትደርስም! ዩክሬን ከዓመት እስከ ዓመት በከፍተኛ በረዶ የቀላቀለ ቅዝቃዜና በከፍተኛ ሙቀት የምትጨነቅ አገር ስትሆን፣ ኢትዮጵያ ከዓመት እስከ ዓመት ለኑሮም ይሁን ለእርሻ እጅግ ምቹ የአየር ንብረት አላት! ይሁንና ዩክሬን ከዓለማችን ከፍተኛ የእህልና ወዘተ ምርት አምራች አገሮች አንዷ ዋናዋም ናት! እንግዲህ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ድፍን የአፍሪካ ባለሥልጣን አንገቱን በከረቫት አንቆ እንደ ዝንጀሮ ፀሐይ ሲሞቅ ስለኑክሌርና ምናምን ሲዘባርቅ ይከርምና ከዚህች ከአፍሪካ ጋር ስትነፃፀር በአጉሊ መነፅር እንኳ ከማትታይ አገር ስንዴና ዘይት ይማፀናል! ሰሞኑን ከሩሲያ ጋር በተፈጠረው ጦርነት አፍሪካ ከዳር እዳር በኑሮ ውድነት የሚናጥበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው! ወጉን ሲያሳምሩት ታዲያ “ምዕራባዊያኑ ራሳችንን እንዳንችል የሸረቡብን ሴራ” ይሉሃል! ድህነት ምርጫ ነው! መሠልጠን ወይም ሞት ብሎ የተነሳ አገር በማንም ሴራ ተገቶ አያውቅም! የአሥራ ሦስት ወራት ፀሐይ ላይ ተሰጥተን በድህነት ሙቀጫ የምንወቀጥ ስጦች ነን? ምንድን ነን?›› ነበር ያለው፡፡ ጎበዝ ከዚህ በላይ ምንም ማለት አልችልም፡፡

(ዘነበ ጉቱ፣ ከአፍንጮ በር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...