Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ መንግሥታት የሠሩትና መሥራት የሚገባቸው ‹‹ሲገመገም››

የኢትዮጵያ መንግሥታት የሠሩትና መሥራት የሚገባቸው ‹‹ሲገመገም››

ቀን:

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት

ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ እስከ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያሉ መሪዎች ከነበራቸው የሥልጣን ቆይታ አኳያ የሠሩትን ሥራ ስንገመግም እጅግ አናሳ ሆኖ አናገኘዋለን፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በርካታ ቢሆኑም፣ ዋናው ምክንያት ግን ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉና በውጭ የሚኖሩ ብቃት ያላቸውን ሰዎች አፈላልገው መሾም ባለመቻላቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ሀብትና አገሪቱን ሊያበለፅጉ ከሚችሉ ዘርፈ ብዙ የሀብት ምንጮች አኳያ (ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የውጭ ዕዳና በድህነት ሳይሆን መኖር የነበረባት፣ መሪዎቻችን መሥራት የሚገባቸውን ሠርተው ቢሆን ኖሮ) አገራችን ድህነት ወጥታ፣ ከውጭ ዕዳ ነፃ ሆና፣ እንዲያውም ሌሎች አገሮችን አበዳሪና ዕርዳታ ሰጪ መሆን ነበረባት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ዓመታዊ በጀቷን ጭምር ለማሟላት ዕርዳታ የምትጠብቅ አገር ስትሆን፣ ካላት አቅም አኳያ ይህ በፍፁም መሆን አልነበረበትም፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየን መሪዎቻችን በሥልጣን ዘመናቸው ሁሌም መሥራት ከሚገባቸው በታች እንደሠሩ በግልጽ ያሳብቃል፡፡  

እኔ ሁሌ የሚገርመኝ አንድ አገር እንደ ኮምፒዩተርና ሌሎች የተራቀቁ ምርቶችን አምርታ ሀብት መፍጠር በተወሰነ ደረጃ ውስብስብ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን መኖራቸው የታወቀን እንደ ብረት፣ የድንጋይ ከሰል፣ እምነ በረድና የመሳሰሉ የተፈጥሮ ማዕድናትን በጊዜ አልምቶ አገርን ተጠቃሚ ማድረግ መሪዎቻችን ለምን እንደተሳናቸው ሳስብ ከፍተኛ ቁጭት ይፈጥርብኛል፡፡

ከአፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ ዓብይ (ዶ/ር) በነበሩ አመራሮች የተሻለ ቦታ ለባለሀብቶች ይሰጥ የነበረው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ነው፡፡ ነገር ግን በንጉሡ ዘመን የነበሩ ባለሀብቶች ከገጠር የእርሻ ልማት የሚያገኙትን ሀብት የግል የተንደላቀቀ ሕይወታቸውን ለመምራት ይጠቀሙበት ነበር እንጂ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲያድግና መሠረት እንዲጣል ጥረት አድርገው አያውቁም፡፡

ንጉሡም፣ ‹‹እኔ ብቻዬን አገር ላለማ አልችልም፡፡ እናንተም በእጃችሁ ላይ ያለን ገንዘብ ለወጣቱ ሥራ ዕድል ለመፍጠርና ቴክኖሎጂ እንዲያድግ የበኩላችሁን አድርጉ፤›› እያሉ ጥሩ ሥራ የሠራውን እያበረታቱ፣ እየሸለሙ በአገራችን የልማት መሠረት እንዲጣል አድርገው ቢሆን ኖሮ አገራችንም ታድግ ነበር፣ ንጉሡም ተዋርደው ከሥልጣን አይወርዱም ነበር፡፡

አንድ መሪ ሊጠበቅ የሚችለው በታጠቁ ጠባቂዎቹ ሳይሆን፣ ሕይወታቸውን የተሻለ ባደረገላቸው ወይም ሕይወታቸውን በለወጠላቸው ዜጎች ነው፡፡ ለአገራቸው የረባ ያልሠሩ መሪዎች ሕዝባዊ አመፅ ሲመጣ ጠባቂዎቻቸው አድነዋቸው አያውቁም፡፡ ሁሉም መሪዎቻችን ሥልጣን ለመያዝና ሥልጣኑን ለማፅናት ብዙ ሠርተዋል፡፡ ነገር ግን ሁሌም ሥልጣን ለመያዝም ሆነ ለማፅናት፣ ሕዝብን ተጠቃሚ በማድረግ መሥራት ከተቻለ ጤነኛ የሆነ ተግባር ተፈጸመ ማለት ነው፡፡

በሸር ወደ ሥልጣን መምጣትና በሸር ሥልጣንን ለማፅናት መሥራት ለማንም አይጠቅምም፡፡ በሸር የተወሰኑ ገደሎችን ማለፍ ይቻላል፡፡ ሁሉንም ገደሎች ማለፍ ግን አይቻልም፡፡ ሸረኛ ሰው ሁሌም መጨረሻው አያምርም፡፡ ሸረኛ መሪዎች በሥልጣን ዘመናቸው ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል ተግተው ይሠራሉ እንጂ፣ ‹‹እስኪ በታሪክ የሚዘከር ቁም ነገር ሠርቼና ዜጎች ሊመሰክሩት የሚችሉት ሥራ ሠርቼ የሥልጣን ዘመኔን ላጠናቅቅ›› የሚል ህልም ኖሯቸው አያውቅም፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ የተሳተፉበት የማይጨው ጦርነትን ታሪክ የሚዘግብ መጽሐፍ በእነ ኮሎኔል ዴል ባዬ ተጽፎ በዶ/ር ተስፋዬ መኮንን የተተረጎመው ‹‹ቀይ አንበሳ›› የሚባለው መጽሐፍ ገጽ 211 ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…ንጉሡም ከዚያ በኋላ በራሳቸው ዋሻ ውስጥ ድንኳናቸውን እንድጋራ ጠየቁኝ፡፡ ንግሥቲቱ እዚህ አዲስ አበባ ቀርተዋል፡፡ ሆኖም ግን ኃይለ ሥላሴ የጦርነት ዘመቻቸው እንዳይመራቸውና እንዳይከብዳቸው፣ በጣም ቆንጆ የሆኑ ሴት ባሮቻቸውን አስከትለው መጥተዋል፡፡ እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት ድንክዬ ውሻዎች ቤተ መንግሥታቸው ከሚገኙት ብዛት ካላቸው ውሾቻቸው ጋር ተመርጠው አብረዋቸው መጥተዋል፡፡ በጣም የሚወዷቸውና የተለየ እንክብካቤ የሚያደርጉላቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወደፊት ሠራዊታቸው የሚጠጣውን በጣም አስፈላጊ የሆነውን ውኃ እነዚህን እንስሳት በማጠብ ንጉሠ ነገሥቱ ያባክኑት ነበር፤›› ይላል፡፡

እዚህ ላይ የምንረዳው ቁምነገር መሪዎቻችን እንኳን ቤተ መንግሥት ሆነው የግድ ጦር ሜዳ መሄድ እንኳን ቢኖርባቸው፣ ምን ያህል ለግል ስሜታቸው እንደሚጨነቁና የአገር ጉዳይና የዜጎች ጉዳይን እግረ መንገዳቸውን ብቻ እንደሚያሳስባቸው ነው፡፡

በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 189 ላይ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የጦር ሚኒስትር የነበሩት ራስ ሙሉጌታ ጦር ሜዳ ከኮሎኔል ዴል ባዬ ጋር በነበሩበት ወቅት ከጣሊያኖች በተተኮሰ ጥይት ተመተው ሲያጣጥሩ እጅግ የሚገርም መረጃ ለኮሎኔሉ ሰጥተውት ነበር፡፡ ይህም መረጃ አፄ ምኒልክ የኃይለ ሥላሴ የጦር ጄኔራል በሆኑት በራሳቸው በራስ ሙሉጌታ በመርዝ እንደተገደሉና መርዙን አንድ ግሪካዊ ዶ/ር እንደሰጣቸው፣ ሕይወታቸው ከማለፉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሚስጥሩን አካፍለውት ኮሎኔል ዴል ባዬ ከማይጨው ጦርነት ተመልሶ ወደ አገሩ ከገባ በኋላ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ አስፍሮት ይገኛል፡፡

ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶ/ር)፣ ይህንን መጽሐፍ ኩባ ተማሪ በነበሩበት ወቅት አግኝተው ወደ አማርኛ ተርጉመው ስላስነበቡን፣ እኔ በግሌ ያለኝን ታላቅ አክብሮት እየገለጽኩ መጽሐፉን ማንኛውም ዜጋ እንዲያነበው እመክራለሁ፡፡

ወደ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን ደግሞ ስንመጣ በመንግሥቱና በአጠቃላይ የደርግ አባላት በግልጽ የሚታየው ባህርይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የመናቅ ሲሆን፣ ሁሉንም ችግሮች በጠመንጃ አፈሙዝ ለማስወገድ የሚደረገው አካሄድ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡

በደርግ ዘመን አገራችን ከፍተኛ የሚባል ዕርዳታ ከሶሻሊስት አገሮች ታገኝ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ በፀጥታ ችግር ተወጥራ ነበረች፡፡ አብዛኛው ወታደራዊ ዕርዳታ ነበር፡፡ የደርግን ዘመን የልማት ዘመን ከምንለው የጦርነት ዘመን ብንለው ይሻላል፡፡

በደርግ ዘመን በስፋት የሚታየው ሁኔታ ልክ አሁንና በሕወሓት ዘመን እንደነበረው ‹‹ምሁር ጠል›› የነበረ ሥርዓት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሁሉም ውጤት የራቃቸው፡፡ አሁን በዓብይ (ዶ/ር) ዘመን እንደምንመለከተው የተፈጠሩ መቅሰፍቶችን  ሁሉ በቃላት ሽወዳ ለማለፍ፣ ከዚያም አለፍ ሲል ኃይል በመጠቀም አንድን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት ሁሌም የታወቀ ነው፡፡  

ችግሮች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ በመዘጋጀት፣ በተቻለ መጠን በሳይንሳዊ ጥናት ባደረግ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የማድረግ ባህል በአገራችን መሪዎች ዘንድ መቼም ያልታየ ባህርይ ነው፡፡ ሁሌም ትኩረት የተነፈጋቸው ሁኔታዎች አብጠው አደገኛ መሆን ሲጀምሩ ነው ዕርምጃ መውሰድ የሚጀመረው፡፡

በደርግ ዘመን ከተወሰኑ ውሳኔዎች እኔ በግሌ በጣም የሚያሳዝነኝ የፈረንሣይ መንግሥት ጂቡቲን ያስተዳደረበት መቶኛ ዓመት ሲሞላ ፈረንሣዮች ለመንግሥት ደብዳቤ ጽፈው፣ ‹‹ጂቡቲን የምናስተዳድርበት መቶ ዓመት ስለሞላ ኑና ጂቡቲን ተረከቡን፤›› ብለው ደርግን ሲጠይቁ፣ ደርጎች ማንንም ሳያማክሩ ጂቡቲን ለመረከብ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በመግጻቸው ዛሬ ጂቡቲን አጥተን ወደብ አልባ ሆነን በመቸገር ላይ ነን፡፡ በደርግ የአመራር ብቃት ማነስ ኤርትራ ተገነጠለች፡፡ እንደገና ደግሞ በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀል የምትችለዋን ጂቡቲን አጣን፡፡ ይህ የተሳሳተ የደርግ ውሳኔ አሁን በድህነት ለመኖራችን የአንበሳውን ድርሻ ይዟል ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ የምንገነዘበው ነገር የደርግ ሰዎች ኑና ጂቡቲን ተረከቡ ሲባሉ (ሊመጣ የሚችል ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሳይኖር) ጂቡቲን የኢትዮጵያ አካል ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ደርጎች ኤርትራ ልትገነጠል እንደምትችል እንኳን መገመት የተሳናቸው ስብስቦች እንደነበሩ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ከደርግ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው የሕወሓት ስብሰብ ሥልጣንን የራስን አጀንዳ ለማስፈጸም ብቻ ተጠቅሞበት እስከ ምርጫ 97 ድረስ የቆየ ሲሆን፣ በምርጫው ወቅት ሕወሓት እጅግ አስደንጋጭ ሕዝባዊ ሠልፍ ካየ በኋላ በተወሰነ ደረጃ የልማት ሥራ ማከናወን ተጀመረ፡፡ እዚህ ላይ የግድ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ በእነ ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) የሚመራው የቅንጅት ስብሰብ መስቀል አደባባይ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለሠልፍ እንዲወጣ ማድረግ ቢችልም፣ ይህንን ሕዝባዊ ማዕበል በመጠቀም መፈንቅለ መንግሥት ማድረግ እየቻለ ሕዝብ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ነው ያደረጉት፡፡ እውነቱን ለመናገር ያቺ ቀን ይህንን ያህል ሕዝብ በሕዝባዊ ማዕበል መንግሥት ለመለወጥ ቢሞክር ሊያስቆመው የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል አልነበረም፡፡ በወቅቱ መለስ ዜናዊ ሽሽት ጀምሮ ደብረ ዘይት አየር ኃይል ግቢ አውሮፕላን አዘጋጅቶ ወደ መቀሌ ለመብረር ዝግጅቱን አጠናቆ ነበር፡፡

በሕወሓት የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት በሥልጣን ዘመኑ ብዙ ነገሮች የተሠሩ ቢሆንም፣ መሥራት ከሚገባው አኳያ ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ የሕወሓት ሥርዓት የግሉን ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አካል ማድረግ አለመቻሉ፣ መሬት በባለቤትነት (በተለይ የገጠር መሬት) መያዝ አለመቻሉ፣ ኢኮኖሚው በተፈለገው ፍጥነት እንዳያድግ ዋናው እንቅፋት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

የታሪክ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያ መንግሥታት የትኛውም መንግሥት ምን ሠራ ብለው ታሪክ ሲዘግቡ በኢሕአዴግ ዘመን የተሠሩ ግድቦችን፣ አገር አቋራጭ መንገዶችን፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ ኮንዶሚኒም ሕንፃዎችንና ከሰላሳ በላይ ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ ጥሩ ተግባር አድርገው መዘገባቸው አይቀርም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የገነባችበት የውጭ ዕዳ በብድር የመጣው ገንዘብ ያላግባብ መባከኑ ደግሞ፣ አሁን አገራችን ያገኘችውን ማንኛውንም የውጭ ምንዛሪ በዋናነት ለዕዳ ክፍያ የምታውል በመሆኑ፣ ከላይ የተጠቀሱት ግንባታዎች የዜጎችን ሕይወት በመለወጥ በኩል ያላቸው አበርክቶ ከዜሮ በታች ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ዓባይ ተገድቦ ሲያልቅ ሕይወታችን ይለወጣል ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ አተያይ በፍፁም የተሳሳተ ነው፡፡ ዓባይ ተገድቦ ካለቀ በኋላ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በቀጥታ የውጭ ዕዳ ለመክፈል ይውላል እንጂ፣ የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል አቅም በቅርብ ጊዜ አይፈጠርም፡፡

እርግጥ ነው የዓባይ ግድብና ሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ሲጠናቀቁ የሚገኘው የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ስለሚጨምር፣ የሥራ ዕድል የመፈጠሩ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምል፡፡ ይህንን እንደ አንድ ጥሩ ነገር መውሰድ ይቻላል፡፡

ወደ ዓብይ (ዶ/ር) የሥልጣን ዘመን ስንመጣ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ስለኢኮኖሚ በተገቢው መጠን ማሰብ እንኳን እንዳይችሉ እጅግ የተወሳሰቡ ነገሮች እንደተወረሱ መካድ አይቻልም፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን እንደ ሜቴክ ያሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመዝረፍ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች የሠሩትን ለመስማት የሚቀፍ ዘረፋና ብልሹ አሠራር ማስተካከልና ማረም የዓብይ (ዶ/ር) የቤት ሥራ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ሥራ የሠሩት በተፋጠነና ድፍረት በተሞላው መንገድ ሳይሆን በፈራ ተባ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑ የሕወሓት ሰዎች እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ሥልጣኖች ላይ ስለነበሩ፣ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. (ዓብይ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ) እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. በሕወሓቶች ምክንያት በአገሪቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ በመከላከያ ውስጥ ብቻ እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ድረስ 67 ከፍተኛ የሕወሓት የጦር አዛዦች ነበሩ፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) በመለሳለሳቸው ብዙ መውሰድ የሚገባቸውን ዕርምጃዎች በጊዜ ባለመውሰዳቸው፣ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ ከባድ መከራና ሥቃይ ደርሷል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ዓብይ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ ይልቅ እንቅልፍ አጥተው የሚሠሩት ስላስጀመሯቸው ፓርኮች መሆኑ በታሪክ መዝገብ ላይ በጉልህ የሚዘከር ጉዳይ ይሆናል፡፡

በተጨማሪ በዓብይ (ዶ/ር) የሥልጣን ዘመን ወደፊት ፍሬ ሊያፈራ የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት መጀመሩን የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በሕወሓት ዘመን ተጀምረው በተለያዩ ምክንያት ተስተጓጉለው የነበሩ ፕሮጀክቶች በዓብይ ዘመን ችግሮቻቸው ተቀርፈው በመገንባት ላይ መሆናቸው፣ በከፍተኛ ደረጀ በጥሩ ጎን የሚገመገሙ ናቸው፡፡

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል (ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥት ከተወገደ በኋላ) የሕወሓት የበላይነት እንዲቀጥል መደረጉ ሌላው የዓብይ (ዶ/ር) በስህተት የተሞላ አካሄድ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል አብዲ ኢሌ እጅግ የሚዘገንን ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ተወግዶ በሙስጠፌ መሐመድ መተካቱ ማንም ሊመሰክረው በሚችለው መንገድ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ ለውጥ እንደተፈጠረ ሁሉ፣ የሕወሓትንም አደገኛነትን በጊዜ ተገንዝቦ አስፈላጊው መስዋዕትነት ተከፍሎ በጊዜ ሕወሐትን ማስወገድ ቢቻል ኖሮ፣ ላለፉት በርካታ ወራት ሕወሓት የፈጸማቸው ወንጀሎች ባልተፈጸሙ ነበር፡፡

ከአንድ የአገር መሪ ከሚጠበቁ ተግባሮች አንዱ፣ ‹‹ወደፊት በዚህ በዚህ ምክንያት እንዲህ ዓይነት ችግር ሊፈጠር ይችላል›› ብሎ የመገመት ብቃት ነው፡፡ ይህንን ተግባር ለመፈጸም በሙያተኞች የተዋቀረ ቡድን በማዋቀር ጉዳዮችን በጊዜ በመተንተን በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) እንኳን ይህንን ሊያደርጉ ይቅርና ሕወሓት ወታደራዊ ሥልጠና እያካሄደች መቀሌ ስታዲዮም ስታስመርቅ ችግኝ ትከሉ ይሉን ነበር፡፡

በየትኛውም አገር ከማዕከላዊ መንግሥት ወታደራዊ ብቃት ጋር የሚገዳደር ወታደራዊ አደረጃጀት እንደ ኢትዮጵያ ያለበት አገር የለም፡፡ እጅግ የሚገርመው ደግሞ ከትግራይ ክልል ማዕከላዊ መንግሥት ምንም ዓይነት ግብር ሳይሰበስብ፣ ሕወሓት አሁንም ለሦስተኛ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ወደ መቀሌ መላኩ በእርግጠኝነት ሕወሓት ይህንን ገንዘብ ለጦርነት ያውለዋል እንጂ፣ ለትግራይ ሕዝብ ምንም የሚደርሰው ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከሱዳን ተነስተው በሑመራ አየር ላይ በረው መቀሌና አክሱም ኤርፖርቶች ያረፉት አውሮፕላኖች እንደነበሩ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን በሦስተኛ ዙር ጦርነት በሕወሓት ወረራ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በሌሎች ተዋጊ ኃይሎች ላይ መድረስ የማይገባው ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል መገመት ሞኝነት አይመስለኝም፡፡

በአጠቃላይ በዓብይ (ዶ/ር) ዘመን መሠራት ያለበት ተግባርና እየተሠራ ያለው ሥራ፣ በቅርቡ ሕዝባዊ እርካታ ያመጣል ብሎ በፍፁም መናገር አይቻልም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጽሑፍ ያነበባችሁ ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ይዘው መሥራት የሚገባቸውን ወይም መሥራት ከሚገባቸው በላይ ለአገራቸው የሠሩ መሪዎች ካሉ እስኪ አስተያየታችሁን ስጡ፡፡ የጋዜጣው ክፍል በእርግጠኝነት በአግባቡ ያስተናግዳችኋል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ ዓብይ (ዶ/ር) ድረስ ያሉ መሪዎችን በራሴ ምልከታ መሥራት ከሚችሉት በታች እንደሠሩ ነው የገመገምኩት፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን ሳይንስ በተራቀቀበት፣ አገርን ለማልማት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከበቂ በላይ ተሟልተው ባሉበት ቤተ መንግሥት ተቀምጦ አገርን ሊለውጥ የሚችል ተግባር መሥራት አለመቻል የሚያመላክተን፣ የአመራሩ ስብስብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የብቃት ማነስ መኖሩን ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ለተሰጠው ሥልጣን የሚመጥን የትምህርት፣ የሥራ ልምድ፣ የዕድሜና የተጠራቀመ ዕውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ውጤት ሊያመጣ የሚችል ተግባር መፈጸም የሚቻለው፡፡

አገር ችሎታ ባለው መሪ (የተፈጥሮ ሀብት ባይኖራትም) ትለወጣለች፡፡ አገር ችሎታ በሌለው መሪ ለውድቀት ትዳረጋለች፡፡ በብዙ በሠለጠኑ አገሮች ውስጥ ያሉ ሕዝቦች አንድ ግዙፍ ፕሮጀክት ሊጀመር ሲል ይህ ፕሮጀክት ሕይወታችንን ውስብስብ ያደርገዋል፣ እኛ የምንፈልገው አረንጓዴ ልማት ነው እያሉ ሰላማዊ ሠልፍ ይወጣሉ፡፡ እኛ ግን ገና የረባ የኢኮኖሚ ለውጥ ሳናመጣ አገራችን በውጭ ዕዳ ተተብትባ፣ መሠረታዊ የዜጎችን ፍላጎት እንኳን ማሟላት ሳንችል ቀኑን ሙሉ ስለአረንጓዴ ልማት እያወራን ነው፡፡    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...