Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትጦርነቱ ብቻ ሳይሆን የጦርነቱ ምክንያት ያብቃ!

ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን የጦርነቱ ምክንያት ያብቃ!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ስለሰላም፣ ስለሰላም ስምምነት፣ ወደ ስምምነትና ወደ ሰላም ስለሚወስደው ስለንግግርና ድርድር በመነጋገር ላይ ሳለን፣ ድንገትና ወደ ድርድሩ በሚወስደው መንገድ ብዙም ሳንገፋ በፌዴራሉ መንግሥት በገዛ ራሱ ብቸኛ አነሳሽነትና ውሳኔ የተወሰደው የተኩስ አቁም ዕርምጃ ውሳኔ ረቡዕ ዕለትና ከዚያው ቀን ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተናግቷል፡፡ እንደገና አዲስ ጦርነት ተከፍቶ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ጦርነት የሚያመጣው መናጋት፣ ጥፋትና ውድመት እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም›› (Humanitarian Truce) የወሰደውን ዕርምጃ ተከትሎ ከመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የቆየውን ይህንን አንፃራዊ ሰላምና የተኩስ ማቆም ማን አፈረሰው? ጦርነቱን ማን ጀመረው? ይህም ራሱ ጦርነት፣ የጦርነቱ አካል የሆነ ፍልሚያ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ራሱ የሚያሳየው ሰላም ለመፍጠር፣ ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት የፈረሰውን የተኩስ ማቆም ዕርምጃ እንደገና ወደ ነበረበት ለመመለስም ሆነ፣ ይህንን ጦርነት ራሱን ለማስቆም የጦርነቱ መነሻ ጉዳዮች ሁሉ ፈልፍሎ ማውጣትና እነሱንም ዓይቶ የማያዳግም መፍትሔ መስጠት ይጠይቃል፡፡

በጊዜው የነበረንና ነፍስ የምናውቅ ሰዎች ትዝ እንደሚለንና የቅርብ ታሪካችንም እንደሚያሳየው የኢትዮጵያና የኤርትራ ድኅረ ነፃነት ግጭት መነሻ (መነሻ የተባለው) ባድመ የኢትዮጵያ ነው? የኤርትራ? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ በአልጀርሱ ስምምነት በተወሰነው ሕግና በተቋቋመው የዳኝነት አካል አማካይነት ውሳኔ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ እስከተወሰነ የማይናቅ ጊዜ ደግሞ ፀቡና ክርክሩ ባድመ የማነው? የኢትዮጵያ ወይስ የኤርትራ? መሆኑ ቀርቶ የድንበር ኮሚሽኑ ባድመን ለማን ወሰነ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለኤርትራ ማለት ኢትዮጵያውያንን የረበሸ ሆን ብሎና ድክመትን ለመሸፈን፣ ኃላፊነትን ለማድበስበስ፣ ሳይጠይቁ መቅረትን (መጠየቅ የሚባል ነገር ከእነ መኖሩም ለመሻር) ለማድበስበስ የተፈጠረ ችግር እንደነበር አልረሳነውም፡፡ ‹‹Sound Familiar?›› ይላል ፈረንጅ እንዲህ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥመው፡፡ ኢትዮጵያን ፈጠርን፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መሠረትን፣ ዴሞክራቶች ነን፣ ለዚያውም አብዮታዊ ዴሞክራቶች የሚሉን ሰዎች እንኳን ከእኛ ጋር፣ ከሚጨቁኑን ጥቁሮች ጋር አልጀርስም ላይ፣ እኩዮች አድርገው አልጀርስ ላይ ከተዋዋሏቸው ጋርም ቢሆን በመረጃ፣ በማስረጃና በዕውቀት መከራከርን፣ ከተቻለም አስቀድሞ አለመግባባትን በውይይት መፍታትን በጭራሽ እንደሚያውቁበት በዓለም አቀፍ መድረክ ራቁታቸውን ቆመው ያስመዘከሩበት አጋጣሚ ነበር፡፡

ከመጋቢት 15 ቀን ጀምሮ ፋታ መስጠት የጀመረውንና የተቋቋመውን፣ የአንድ ወገን (ዩኒላተራል) ፈቃድና ዕርምጃ ያመጣውን (በዜና ላይ ተደጋግሞ እንደሚሰማውና የተኩስ አቁም ስምምነት እየተባለ በስህተት እንደሚጠራው)፣ በስምምነት ላይ ያልተመሠረተውን ጊዜያዊ ሁኔታ ማን አፈረሰው? ቀደም ሲል ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ራሱ ‹‹ጦርነት›› ነው፣ ‹‹ጦርነት›› ከፍቷል፡፡ ሕወሓት ጦርነት የጀመረው የፌዴራሉ መንግሥት ነው የሚለው በ‹‹መሃላ ቃል›› ጭምር ነው፡፡ እንዲያውም አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚሉት የዚህን ጉዳይ ዋና መግለጫ እስከሰጡበት ቀን ድረስ ለሦስት ቀናት የቆዩት እስኪያጣሩ ድረስ፣ የተፈጸመው ድርጊት የአንድ ‹‹የነሸጠው ሰው››፣ ‹‹በሞቅታ መካከል›› የመጣ ነገር አለመሆኑን እስክናጣራና እስክናረጋግጥ ድረስ እንጂ ነገሩ የጀመረው ‹‹ስምምነቱ›› ፈረሰ ተብሎ ከተነገረበት ከሦስት ቀናት በፊት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለጊዜው በዚህ የክርክር ጭብጥ ላይ ‹‹ግራ ቀኙን›› መከራከሪያና ማስረጃ መርምሬ እውነቱ ይህ ነው ማለት የምችበት እውቀት የለኝም፡፡ የሚገርመው ግን ስለሰላምና ስለዘላቂ ሰላም ስናወራ በጦርነት ውስጥ ለጊዜው ቆም ባለ (ፖዝ በተደረገ) ጦርነት ውስጥ ስለተጀመረ ማን አፈረሰው ሌላ ጦርነት ስናወራ ከዚህ በላይ ደባ የተሠራበትን፣ ‹‹ዓለም አቀፍ›› ሚዲያው የጉልበተኞችን፣ የአድራጊ ፈጣሪዎችን፣ የግለኞችን ጠንጋራ መነጽር አጥልቆ ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ ‹‹እየፈረደ›› የግፍ ግፍ የሚፈጽምበትን የጦርነቱን የሥር የመሠረት ተኳሽ ጉዳይ በጭራሽ መርሳት የለብንም፡፡

እና ሚዲያው በሚያስተጋባው ጉልበተኞች ቀርፀውና ደርሰው በሰጡት ትርክት መሠረት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ትግራይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሰሜን ዕዝ ተጠቃ ብሎ ዕርምጃ እንዲወስድ በማዘዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ የገባቸው ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. (ሃያ ሦስተኛው ወር ውስጥ ገብተናል) መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይህ ግን ሁሉንም እውነት ሆነ እውነቱን ሁሉ አይገልጽም፡፡ ምክንያቱም እስከዚያው ድረስ ጦርነት ተብሎ አይጠራ እንጂ ሕወሓት ዓብይ አህመድ በሚመራው ለውጥና ሽግግር ላይ ተኩስ የከፈተው ትናንት እሱ በአፋኝና አርድ አንቀጥቅጦ ገዥነቱ ላይ በነበረበት ወቅት የሰቀዛቸውን መብቶችና ነፃነቶች በለውጡ ጊዜ በሽግግሩ ምጥ ውስጥ ግፋ በለው ላይ ሆኖ ግጭት ማራባት በጀመረበት ሰዓት ነው፡፡ ከዚያም፣ ከዚያም ሁሉ በፊት በእሱ ቁጥጥር ሥር ሆኖ የኖረውን መንግሥታዊ አውታር በሙሉ በራሱ አምሳል ሲቀርፅ ነው፡፡ ኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይ ተሠልፎ የኖረውን የሰሜን ዕዝ በ‹‹ቦታ›› ብቻ ሳይሆን፣ በአመራር ክምችትም፣ በዶክትሪንም አገርን የምርኮ ሲሳይ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀምም ረገድ የገዛ ራሱ ‹‹ጦር›› አድርጎ ‹‹ቤት›› ሲሠራ ነው፡፡

ዕለቱን ወደሚመለከተው የጥቅምት 23 ጉዳይ እንመለስ፡፡ ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ? የጉልበተኞቹ የፍርደ ገምድሎቹ መልስ ብቻ ሳይሆን ‹‹ፍርድ›› ዓብይ አህመድ (የሰሜን ዕዝ ተጠቃ ብለው) ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲያዙ ነው የሚል ነው፡፡ ሚዲያውም የሚያስተጋባውና የሚዘምረው ይህንኑ ነው፡፡ ጦርነቱን የጀመረው ድርጊት የሰሜን ዕዝ መጠቃቱ ነው? ወይስ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ? ሚዲያውና ጉልበተኛው ዓለም እነዚህ ጥያቄዎች እኩዮች ሆነው እንዲቀርቡ እንኳን አይፈቅዱም፡፡ ‹‹የሰሜን ዕዝ መጠቃቱ›› እንኳ አይሉም፡፡ የሰሜን ዕዝ ተጠቃ በመባሉ ነው የሚሉት፡፡ ይህንን የመሰለ ፍርደ ገምድልነት ይኼውና ለ22 ወር ያህል የጦርነቱ ‹‹ምክንያት›› በተነሳ ቁጥር የምንሰማው የማይጠየቅ፣ ራሱንም ከማስረጃና ከእውነት ‹‹ነፃ›› ያወጣ አድሏዊነትና ቅጥፈት ነው፡፡ አሁን ጦርነቱ እንደገና ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጊዜው ከቆመበት ሲጀምርና ከዚያ ወዲህ በምንሰማው ያው የተለመደ ‹‹የተሰበረ ሸክላ›› መሠረት የቪኦኤው የአማርኛ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ፋይል ባደረገው ዘገባው፣ ጦርነቱ የተነሳው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል በሚል/ተብሎ ዓብይ ትዕዛዝ ሲሰጡ መሆኑ ይታወሳል ሲል ሰምተናል፡፡ ይህን የመሰለውን የእኛውን አገር ጉድና ጋዜጠኛነት እንኳን ከ‹‹ቅጥረኝነት›› ከታማኝ አገልጋይነት ይልቅ ሲከፋ ድንቁርና ውስጥ አለዚያም ማሰብና ማሰላሰልን ትቶ ዝም ብሎ በደፈጣ ጸሐፊና ጋዜጠኛ መሆን ውስጥ ማፈላለግ ሳይሻል አይቀርም (በነገራችን ላይ የአገሬ ጋዜጠኞችና የፌስቡክ ከታቢዎች ጭምር በዳግምና በእንደገና መካከል ያለውን ተመሳሳይነትና ልዩነት ለምን በተግባር አያሳዩንም?)፡፡

በዚህ አጋጣሚ እውነቱን ለሚሹ ቢያንስ ቢያንስ የተለያየ ሐሳብን የሁሉንም ወገኖች መከራከሪያ ከልብ መስማት ለሚልጉ ለአገራችን ጋዜጠኞችና ጸሐፍት እግረ መንገዴን ማስታወስ የምፈልገው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የዩኢንዲፒ አስተዳዳሪ የካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የጻፉትን ደብዳቤ እንዲያዩና በእሱም ላይ ተጨማሪ ሥራ፣ ተጨማሪ እሴት እንዲጨምሩ ነው፡፡ ይህንን የዩኤንዲፒ ሜሞ (ማስታወሻ) ለመጀመርያ ጊዜና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. (ማርች 9) ያወጣውን ፎሬን ፖሊሲንም እንዲያነቡት እጋብዛለሁ፡፡ በጋዜጠኛነት ሙያ እንዴት እንደሚቆመር ጭምር አሉታዊና ክፉ ተግባሩ ያስተምራል፡፡ ይህ ፎሬን ፖሊሲ ለመጀመርያ ጊዜ ወሬውን ያወጣውና አንጋዶ፣ ቆራርጦ ለጌቶቹ እያረገደ መራርጦ ያወጣው ጽሑፍ ራሱ ብዙ ይመሰክራል፡፡ ዋናው ችግር ‹‹…በኢትዮጵያ የፖለቲካ የሠራ አካል ላይ በቅሎ የተንሠራፋው ሁለት ዓመት የሞላው ነቀርሳ ነው፣ ማለትም ትግራዋይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው›› ይላል፡፡ ዓለም አቀፋዊው ማኅበረሰብ ይህንን ከሥር ከመሠረቱ ለመከላከል በጊዜውና (ሳይረፍድ በጠዋቱ) ዕርምጃ አለመውሰዱን በተለያዩ ቁናዎች መሥፈሩን እያነሳ ይከሳል፡፡ ተጠያቂ ነውም ይላል፡፡

ይህንን የዩኤንዲፒ/የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ድርጅት ዋና ኃላፊ ደብዳቤና የመጀመርያ ምስክርነት የምጠቅሰውና በምስክርት የምቆጥረው፣ ኢትዮጵያ እጅ በለውጡና በሽግግሩ ወገን በኩል ብቸኛው ምስክር/ማስረጃ ይህ ብቻ ነው ብዬ አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ የሚሰማ ነው የጠፋው፡፡ የሚናገር መጥፋቱም የሚሰማ መጥፋት ችግራችንን አባብሶታል፡፡ የሚናገር መጥፋቱ፣ የኢትዮጵያን ሕመም የኢትዮጵያን ችግር በዳኝነትም ሆነ በሕዝብ አስተያየት መድረክ የሚናገር መጥፋቱ ለውጡና ሽግግሩ ራሱ የተነሳበት፣ ገለልተኛና በምርጥ ባለሙያዎች የተገነባ ተቋም የማደላደል በሽታችን አንዱ አካል ነው፡፡ ትናንት ኢትዮጵያና ኤርትራ የባድመ ጉዳይ ሰበብ ሆኖ ለዚያ ሁሉ ዓይነት ችግር በተዳረግንበት ወቅት፣ እውነታችንን በመናገርና በማስረዳት ረገድ ምን ያህል ሥቃይና መከራ ውስጥ ገብተን እንዳለፍን ገና እማማ ኢትዮጵያ ተናግራ፣ አልቅሳ፣ አውግታ የጨረሰችው ጉዳይ አይደለም፡፡ ገና ከኢትዮጵያ አገር ውስጥ ወጥቶ አዲስ ጎጆ የወጣ አገርና መንግሥት እንዴት አድርጎ በአደባባይ ክርክር ሊበልጠን እንደቻለ ዛሬም፣ እስካሁንም ድረስ በኃላፊነት ተጠይቆ ሒሳቡን ያወራረደና የከፈለ የለም፡፡ አልጀርስ ላይ በገባውና ፓርላማውም ባፀደቀው/አፀደቀው በተባለው ስምምነት መሠረት ባድመ የእኛ ነች እያልን የምንከራከረው፣ ለካስ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት የተሰመረው የድንበር መስመር ባድመን የማን ያደርጋል? የኢትዮጵያ ወይስ የጣሊያን ነው እንጂ በቅርብ ጊዜም ከዚያ በፊትም ለረዥም ጊዜ ባድመን ማን ሲያስተዳድር ኖረ? ባድመ የማን ይዞታ ነች የሚል አልነበረም፡፡ ‹‹ሞኙ›› የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ባድመ የእኔ ነች ብሎ ባድመ ላይ ምርጫ የተካሄደበትን ማስረጃ ሁሉ እያቀረበ ተከራከረ፣ ተዋጋ፡፡ እዚያ ክርክር ላይ ጉድ የሠሩትን ሰዎች፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ብሔራዊ ጥቅምን የማያስጠብቅ ሽርክና ውስጥ ከመግባት አንስቶ፣ ጦርነት ውስጥ እስከ መግባት፣ ጦርነት ውስጥ ከተገባም በኋላ ከአጨራረስ ጀምሮ በቅኝ ግዛት የወሰን ውል እረታለሁ ብሎ በዓለም አቀፍ የፍርድ መድረክ ሙትቻ ክርክር እስከ ማድረግና የተሰጠውን ውሳኔ አለመረዳትን ጨምሮ እሱንም እስካለመቀበል ድረስ በተግተለተሉ ጥፋቶች፣ አገሪቱ ላይ ከፍ ያለ በደል ያደረሱ ሰዎች ዛሬ ኢትዮጵያን በልጠው የሚሰሙ ሆነው አረፉት፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያት ምንድነው? ይህን ሁሉ የሚናገር ሰውና ወኪል እንዴት ኢትዮጵያ ትጣ?

የሚገርመው ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያና የትግራይ ጭምር ደመኛ ጠላት የሆነው የሕወሓት ቡድን ዛሬም በዚህ በጦርነቱ ምክንያት ክርክር በሚያደርጉበት ወቅት በልጠው፣ በልጠን እንታይ ብለው መቅረባቸው አለመቅረቱ ነው፡፡ ከአምስት ወራት ጊዜያዊ የግጭት ማቆም ሁኔታ በኋላ ነሐሴ 18 ቀን ግጭቱ/ጦርነቱ እንደገና በተጀመረበት ሳምንት ውስጥ፣ አልጀዚራ ኢንሳይድ ስቶሪ ኢትዮጵያ ላይ የቀረበው ማርቲን ፕላውት ዓይነት ሰው የሚጫወተውን ሚና፣ የሚፈጽመውን ተልዕኮ መመልከት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሕወሓት በኢሕአዴግና በኢትዮጵያ መንግሥትነት ስም ኢትዮጵያን የምርኮ ሲሳይና የዝርፊያ ማሳ (ከዚያም በፊት በትጥቅ ትግሉ ወቅት) አድርጎ በገዛበት፣ ባዘዘበትና በናዘዘበት ወቅት መላሻ እያቀመሰ ፍርፋሪ እየሰጠ ያላመዳቸው የማደጎ ውሾች ናቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች የማይጮሁት ‹‹ጩኸት›› የለምና ለምሳሌ የተጠቀሰውን የአልጀዚራን የኢንሳይድ ስቶሪ የማርቲን ፕላውት የኢትዮጵያን ጥፋት የሚያስረዳ ማስረጃ እንመልከት፡፡ ይህ ሰው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የጥቅምት 23/24 ዕርምጃ ሕወሓት የሰሜን ዕዝን መጀመርያ በማጥቃቱ ምክንያት የተወሰደ ምላሽ መሆኑንም እስከ ማመን ድረስ ጭምር ‹‹አብሮን መጓዝ›› የሚችል ነው፡፡ ታዲያ ምን ይጠበስ!? ምን ‹‹አባታችሁስ›› ትሆናላችሁ? ይለናል ማርቲን ፕላውት፡፡ ሕወሓት ይህንን ያደረገው አሁንም የዓብይ መንግሥት ከኤርትራው የኢሳያስና ከሶማሌው የፎርማጆ መንግሥት ጋር አብሮና ተባብሮ ትግራይ ሕዝብ ላይ የህልውና አደጋ ሊጥል ሲል ለመከላከል፣ አስቀድሞ ለመከላከል የተወሰደ ዕርምጃ ነው ባይ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ጋዜጠኞች/ተንታኞች ‹‹ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት አደረሰ በሚል›› የሚል ‹‹መደዴ›› መከራከሪያ ላይ አልቆረበም፡፡ ይህንን ጭብጥ ለማስረዳትና ክርክሩንም ለማጠናከር (ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን በአልጀዚራ እንደሰማነው) የአልጀዚራን ተመልካቾች ይማፀናል፣ ጉግል አድርጉና የሦትዮሽ የኢትዮጵያን፣ የኤርትራንና የሶማሊያን ስምምነት ልብ አድርጉልኝ ይላል፡፡ ማርቲን ፕላውት ‹‹ስሞት አፈር ስሆን!›› ብሎ ዊኪፒዲያ ውስጥ ፈልጋችሁ አንብቡና ፍረዱኝ የሚለው ጉዳይ አስመራ ላይ ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. (5 ሴፕቴምበር 2018) ዓብይ፣ ፎርማጆና ኢሱ የተፈራረሙት የትራፓርታይት ስምምነት (የአፍሪካ ቀንድ) የሚባለው ሰነድ ዜና ነው፡፡ በይፋ ስሙ ‹‹Joint Decclaration on Comprehensive Cooperation Between Ethiopia, Somalia and Erittria›› ይባላል፡፡

 ሰውየው እንደ እርግጠኛነቱ፣ እንደ ‹‹ውስጥ አዋቂ››ነቱና እንደ ፉከራው ዳግም እዩልኝ፣ ስሙልኝ የሚለው የስምምነቱን ዜና እንጂ ስምምነቱን ራሱን አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የዚህ ዜና (ሰነዱ ራሱ አይደለም) የዊኪፒዲያ የዚህ መረጃ የግርጌ ማስታወሻዎች እንደሚያሳዩት ከአራቱ ማጣቀሻዎች ውስጥ ሁለቱ የራሱ የማርቲን ፕላውት፣ የተቀሩ ሁለቱ ደግሞ የፋናና የአዲስ ስታንዳርድ ናቸው፡፡ ይህንን ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የተፈራረሙትን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው፣ እንዲያውም ምናልባትም ለ2019 የኖቬል የሰላም ሽልማት አሸናፊነት ያገለገለውን ጥረት ነው የኢትዮጵያ ጥፋትና ማስረጃ አድርጎ ተጋዳላይ ፕላውት እግዜር ያሳያችሁ ክርስቶስ ያመልክታችሁ ብቻ ሳይሆን ያዙኝ ልቀቁን የሚለው፡፡ የ2019 የኖቬል የሰላም ሽልማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተሰጠው መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. (ኦክቶበር 11 ቀን 2019) ነው፡፡ የየትኛውም የዚህ ሽልማት ዕጩ የማቅረብ የጊዜ ገደብ ደግሞ በዚያው ዓመት (2019) ጃንዋሪ 31 ላይ ያልቃል፡፡ ከፌብሩዋሪ 1 በፊት (ከጥር 24 ቀን 2011 በፊት) ያልቃል፡፡ ዓብይ ስምምነቱን ያደረጉት ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ነው፡፡ ደግሞ እኮ ራሳቸው ደብረ ጽዮን፣ ዓብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ያለንን ግንኙነት በሚመለከተው ዘርፍ ያመጡትንና ያስመዘገቡትን ለውጥ ‹‹ፕሮፋውንድ›› ነው ብለው በአደባባይ፣ በጉባዔ የመሰከሩለት ሥራ ነበር፡፡   

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ማርቲን ፕላውት ቅጥርና የኪራይ ጋዜጠኛና ተንታኝ ሆኖ በሚያቀርበው መከራከሪያ ይህ ጦርነት የእርስ በርስ ጦርነት (ሲቪል ዋር) አይደለም፡፡ ከዚያ የባሰ ሪጅናል ጦርነት ነው እያለ የሚያቀርበው ክርክር ነው፡፡ ይህ መከራከሪያ ዓብይ አህመድና ሕወሓት ሳይቀድመን የቀደምነው የአስመራው ስምምነት ይዞት የመጣውን እርግጠኛና አይቀሬ አደጋ ለመመከት ነው የሚልና ያለፈ ነገር ላይ መተማመኛና ማረጋገጫ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በጦርነቱ ጊዜና ሒደት ውስጥ የሕወሓት ተቀዳሚ ፍላጎት ሆኖ የመጣውን ግብ ለማሳካት ነው፡፡ ይህም የትግራይን ሕዝብ ማስራብ የጦርነት ሥልት ሆነ፣ የሰላምና የድርድሩን ሒደት መንግሥት ዕንቢ አለ እያለ ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ወታደራዊ ኃይል መትከል ነው፡፡ እነ ማርቲን ፕላውት በእርስ በርስ ጦርነት በላይ የአካባቢ (ሪጅናል) ጦርነት ነው፣ ኤርትራ ጦርነቱ ውስጥ አለች፣ ኤርትራ ወታደር/መከላከያ ውስጥ የሶማሊያ ወታደሮች አሉ፣ ከዚያም በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ጦርነቶች/ግጭቶችም መፍታት ያስፈልጋል ይልና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የትግራይ ብቻ ተደርጎ መታየቱን ውሸት ይልና የትግራይ ጦርነት በዓለም ላይ አሁን ከሚካሄዱ ጦርነቶች መካከል ደመኛ መሆኑ እውነት ነው ይልና፣ ግን ከዚህ ከትግራይ ጋር በጭራሽ ምንም ግንኙነት የላቸው ሌሎች ጦርነቶችም አሉ፣ ይህችን ባለ 80 እና 90 ‹‹ቡድን›› ኢምፓየር ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ነገሩ ወዲህ ነው፣ ጦርነቱ አካባቢያዊ ሪጅናል ጦርነት ነው፡፡ መፍትሔውም የሚገኘው ይህንን ከማወቅ ላይ ነው ብሎ የ‹‹መፋረጃ ሐሳቡን›› ያቀርባል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት ግን ማርቲን ፕላውት ከሚገኝበት የኪራይና የቅጥር ጋዜጠኞችና ተንታኞች ውጪ ያሉት ሌሎቹ እንደሚሉትም የእርስ በርስ ጦርነት አይደለም፡፡ ዓለም አቀፋዊው የጦርነት ሕግ (ኢንተርናሽናል ሒዩማንቴሪያን ሎው የሚባለው) ሲቪል ዋርን ማለትም የእርስ በርስ ጦርነት ከቁጥር የሚያስገባው በአገሮች/በመንግሥታቱ መካከል ከሚደረጉ ጦርቶች ውጪ ያሉትን ጦርነቶች ለማመልከት ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ያልሆኑ ግጭቶች ለማለት ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ግጭቱ ምንም ዓይነት ባህርይ ይኑረው (በአገሮች መካከል የሚካሄድ ጦርነት ሆነ በአንድ አገር ውስጥ) ጦርነት ሁሉ በጦርነት ሕግ ውስጥ ይሸፈናል ለማለት ነው፡፡ ጉዳዩ አሁን በቀረበበት መልክ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አሁን እንደገና የተነሳውን ጦርነት ሲቪል ዋር (የእርስ በርስ ጦርነት) ማለት ያልተለመደ አይደለም፡፡ እንዲያውም ፖለቲካዊ መከራከሪያም ነው፡፡ ሲቪል ዋር ወይም የእርስ በርስ ጦርነት ማለት ሕዝብ የሁለት ተዋጊ ወገኖች ተስቦ የሚተጫጨድበት ማለት ከሆነ በኢትዮጵያችን ውስጥ በእኛ ዕድሜ (ባለፉት 60 እና 70 ዓመታት ውስጥ) ሕዝቦች ወዶ ገባ የሆኑበት የእርስ በርስ ጦርነት ዓይተን አናውቅም፡፡ በኤርትራም ሆነ በትግራይ ውስጥ የነበሩት ጦርነቶች ሕዝብን የማገዱ ቢሆኑም (ሕዝብን ማግደዋ) በመንግሥትና በሽምቅ ተዋጊዎች መካከል የተካሄዱ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ ‹‹ቀይ ሽብር›› እና ‹‹ነጭ ሽብር››ም የእርስ በርስ ውጊዎች አልነበሩም፡፡ ሕዝብ/ሕዝቦች ወገን ለይተው አልተፈሳፈሱም፡፡ የእርስ በርስ ውጊያ ጅምር የተከሰተበት ወቅት ቢኖር ኦነግና ቢጤዎቹ ፀረ ነፍጠኛ ግብግብ ባነሳሱበት የ1983 የአፍላ ወቅት ነበር፡፡ ‹‹ዕድሜ›› ለሕወሓት ከለውጡ ወዲህ እዚህም እዚያም ብልጭ ድርግም እያሉ የሚያስፈራሩን ብሔር ነክ ግጭቶች በቶሎና ትክክለኛ መፍትሔ ካላገኙ ዓይተነው የማናውቀው መሰያየፍ ሊያጥለቀልቀን ይችላል፡፡ ለውጡና ሽግግሩ የሚለፋው ይህንን ለማስቀረት ነው፡፡ ሕወሓት የሚማስነው የእኔ ልዩ ጥቅም የ(Privilege) እና (Prerogative) የእኔ አግላይነትና አንጓላይነት የተቋረጠበት ኢትዮጵያ፣ የእኔ የምርኮ ሲሳይ፣ የእኔ የዘረፋ ማሳ ያልሆነች ኢትዮጵያን አፈርሳታለሁ፣ አተራምሳታለሁ፣ ለሕዝም ፍጅትና መጨራረስ እደግስለታለሁ ብሎ ነው፡፡

የኢትዮጵያ፣ ‹‹ጦርነት›› ሪጅናል ጦርትም አይደለም፡፡ የዚህ ‹‹መከራከሪያ›› ባለቤቶች አሁን የዚህ የአልጀዚራ የኢንሳይድ ስቶሪ መድረክ ለማርቲን ፕላውት ሲያደርገውና ሲያደራርገው እንዳየነው የኢትዮጵያ መንግሥት የዚያን ወቅት ‹‹ውሸት›› ወይም የኤርትራ ጦር አገሬ ውስጥ የለም ማስተባበሪያ ከኩራት፣ ከእብሪት ያለፈ ጥጋብ ሲያጎናፅፈው አይተናል፡፡ የእኛ የመናገር፣ የመከራከር ችሎታ በትንንሽ ነገሮችም ቢሆን እንዲህ እንደሚያጎድለን መገንዘብ አለብን፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ በመብቷ ውስጥ ናት፡፡ ከዩክሬን የበለጠ፣ ዩክሬን አገር ምድሩን ከጋበዘችበት የበለጠ ኤርትራን ድረሽልን የማለት መብት አላት፡፡ የአገር ክህደቱ የውጭ ወታደራዊ ኃይል እንዲመጣ የሚጠራው፣ ይህንን የሚያግዘው ዋናው የውስጥ ጠላት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ መከራከሪዎች፣ መከራከሪያ መስለው የሚደረደሩ ስያሜዎችና ውሸቶች የሚያሳስቡን አሁን በምንገኝበት ‹‹ዓለም አቀፋዊው ኅብረተሰብ›› አያያዝና ባህርይ ይህን በመሰለ ሰበብና ማመካኛ ከፍተኛ ትንቃቄ ልናደርግበት የሚገባ የከፋ ጥቃት ሊደገስብን እንደሚችል ከወዲሁ በማወቅ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነትና በእሱ ስም የተቋቋመው የዓለም የመተዳደሪያ ሥርዓት የሚሠራው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው ዓለም የፈረመው፣ ይበጅ ያለውና የተቀበለው ሕጉ ትርጉም የሚኖረው ትልልቆቹ ኃያላን ያለን አገሮች ባበጁት መቃንና ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሥርዓቱ ታልልቆቹ ጉልበተኛ አገሮች በተለይም አሜሪካ እንወደዋለን እንፈቅደዋለን ከሚሉት ወሰንና ሜዳ ውጪ አይላወስም፡፡ ይህንን በመሰለ የተወሳሰበ ዓለም ውስጥ አሁን ያጋጠመን ችግር መጋፈጥና መፍታት የምንችለው፣ አገርን ከማዳን ግዳጅ ጋር እንድ ላይ የገጠመውን ዴሞክራሲን የመገንባት አደራ የምንወጣው፣ እውነትና ሀቅን ፍትሐዊ ዓላማን ከመጨበጥ ጋር አንድነታችንንም ንፋስ የማይገባው ስናደርግ፣ በዚህም ላይ በዕውቀትና በጥበብ ስንረባረብ ጭምር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...