Friday, September 22, 2023

ውጥረት የነገሠበት የወልቃይት ግንባር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የወልቃይት ግንባር አሁን ዋናው የዓውደ ውጊያ ሜዳ ሆኗል፡፡ በሰሜን ኤርትራን፣ በምዕራብ ደግሞ ሱዳንን የሚያዋስነው ይህ ቀጣና በሁለቱ የአማራና የትግራይ ክልሎች ከፍተኛ የይገባኛል ጥያቄና ውዝግብ የሚነሳበት ነው፡፡ በዚህ ቀጣና ወደ 360 ሺሕ ሔክታር የሚገመት ለም መሬትን የሱዳን ጦር በኃይል መቆጣጠሩም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በራያ ቆቦ ግንባር የጀመረው ሦስተኛው ዙር ጦርነት በቀናት ልዩነት ወደ ወልቃይት ግንባር አምርቷል፡፡ በራያ ግንባር ቆቦን እስከ መቆጣጠር ደርሶ የነበረው የሕወሓት ኃይል በጥምር ጦሩ በደረሰበት ምት ጠንካራ ምሽግ ሠርቶበት የቆየውን ከመቀሌ በ95 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝውን የአበርገሌ አካባቢ ጭምር ለቆ እንዲያፈገፍግ መገደዱ ተረጋግጧል፡፡ በአፋር ግንባር በኩል ጥምር ጦሩ ማጥቃት ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑ እየተነገረ ሲሆን፣ የአፋር ክልል ወሰን ከመቀሌ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደመገኘቱ ለጥምር ጦሩ የወደፊት ግስጋሴ ወሳኝ መንደርደሪያ እንደሚሆነው ተገምቷል፡፡

ከሁሉ በተለየ ሁኔታ ተፋፍሞ በቀጠለው የወልቃይት ግንባር ውጊያ ጥምር ጦሩ በሕወሓት ኃይሎች ላይ ጠንካራ ምት ማድረሱ ታውቋል፡፡ የትግራይ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ ታደሰ ወረደ (ጄኔራል)፣ እንዲሁም የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በተለያዩ ቀናት በሰጧቸው መግለጫዎች፣ ‹‹በወልቃይት ግንባር ጠንካራ መረባረብ ተደርጎብናል፤›› የሚል ይዘት ያለው መረጃ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡

በወልቃት ግንባር በተለይ ከሑመራ በ25 ኪሎ ሜትር የምትርቀው ሉግዲ  የተካሄደው ውጊያ ጠንካራ መሆኑን የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በወልይቃት ግንባር እየተካሄደ ያለው ውጊያ ሁለት መልክ እንዳለው የገለጹት የአካባቢው ምንጮች፣ በአንድ ወገን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስበር ዕርምጃ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከተከዜ ባሻገር የተሠለፉ የትግራይ ኃይሎችን ከማፅዳት ጎን ለጎን በሱዳን ድንበር በኩል መሠለፉ የሚነገረውን ሳምሪ የተባለውን የሕወሓት ኃይልም የማፅዳት ተልዕኮ ጥምር ጦሩ እንዳለው ነው ምንጮች ያረጋገጡት፡፡

በዚህ የወልቃይት ግንባር ውጊያም የጥምር ጦሩ በወሰዳቸው ጠንካራ ዕርምጃዎች ወደ አምስት ምሽጎች መሰበራቸውን ነው እነዚሁ ምንጮች ያረጋገጡት፡፡ በእነዚህ ከባድ የውጊያ ቀናት ደግሞ በየዕለቱ ከሚሰሙ የግንባር ዜናዎች ጎን ለጎን፣ ‹‹ወልቃይት ለምን የደም መሬት ሆነ?›› የሚለው ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ አጨቃጫቂ ጉዳይ ዳግም በመነሳት ላይ ነው፡፡

የዛሬ 20 ዓመታት በአሜሪካን አገር የተቋቋመው የልሳነ ግፉአን ድርጅት በወልቃይት ተወላጆች የተመሠረተና የወልቃይትን የማንነት ጥያቄ ለማስመለስ የሚሠራ ድርጅት መሆኑ ይነገራል፡፡ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ኪዳኔ ማሙሻ ድርጅቱ ሲመሠረት በወቅቱ ለነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደብዳቤ በመጻፍ የአካባቢው ሕዝብ ጥያቄ በሰላም እንዲመለስ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመታት አቶ ኪዳኔ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መረጃ፣ ለአቶ ዳዊት ዮሐንስ፣ አቶ መለስ ዜናዊና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በደብዳቤ ጥያቄዎቻቸውን ቢያቀርቡም መልስ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ የተነሳ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር የነበረውን የወልቃት አካባቢ ‹‹ግፍን በራሳችን መንገገድ ለዓለም ማጋለጥ ጀመርን፤›› ይላሉ አቶ ኪዳኔ በማብራሪያቸው፡፡ 

‹‹ሕወሓት ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምትን የራሱ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ ይህንን ለም አካባቢ ለመጠቀም፣ እንዲሁም ወደ ሱዳን የመውጫ በር ለማድረግ በ1972 ዓ.ም. ተከዜን አቋርጦ ወልቃይት ገባ፡፡ ሕዝቡ ቢታገለውም ነገር ግን ተደጋጋሚ ጦርነቶችን በመክፈት በቁጥጥር ሥር አውለውታል፡፡ በቃብቲያ በተደረገው የመጀመርያ ውጊያ ተመተው ቢመለሱም፣ ነገር ግን ተደራጅተው በመምጣት ብዙ ሰዎች ገድለው ቦታውን ይዘውታል፡፡ ሕዝቡ ‹ከፋኝ› የሚል የአመፅ እንቅስቃሴ በማድረግ ሲታገላቸው ቆይቷል፡፡ በኋላም የአርበኞች ግንባር ኃይልን በመቀላቀል በኤርትራ ሸምቆ ሲዋጋ ቆየ፡፡ በእነዚህ የትግል ጊዜያት እንደ ‹‹ባዶ ስድስት›› የሚባል አስከፊ እስር ቤቶችን በመሥራት የሚታገላቸውን ሕዝብ አሰቃይተዋል፡፡ ወልቃይት የኢሕአዴግ መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት በዚህ መሰሉ የኃይል ዕርምጃ የተወሰደ ቦታ ነው፤›› በማለት ነበር አካባቢው ከመቼ ጊዜ ጀምሮ የውዝግብና የደም መሬት መሆን እንደጀመረ ያስረዱት፡፡

በተለይ ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ ጥያቄው እየገፋ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ኪዳኔ፣ ‹‹የወልቃት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ›› ተቋቁሞ ጥያቄ ማንሳት ሲጀምርና በጎንደር የእነ ደመቀ መኮንን (ኮሎኔል) እስር ጉዳይ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተከትሎ፣ የወልቃይት ጥያቄ በሚዲያዎች ጎልቶ መውጣቱንና የአማራ ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ወደመሆን መሸጋገሩን አቶ ኪዳኔ ያስረዳሉ፡፡

ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የዛሬ ሁለት ዓመታት ጦርነቱ ሲከፈት የአማራና የአፋር ኃይሎችን በማስተባበር የመከላከያ ጥምር ጦር በከፈተው ማጥቃት የወልቃይት ቀጣና ከሕወሓት ቁጥጥር ነፃ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

የወልቃይት አካባቢ ሕዝብ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የራሱን ጊዜያዊ አስተዳደር የመሠረተ ሲሆን፣ ነገር ግን የአካባቢው ሁኔታ ሥጋት እንዳጠላበት መቆየቱ ነው የሚነገረው፡፡

የልሳነ ግፉአን ድርጅት ሊቀመንበር አቶ አብዩ በለው መጋቢት 2014 ዓ.ም. ላይ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ‹‹የወልቃይት ጉዳይ ባለህበት እርገጥ ሁኔታ ላይ ይገኛል፤›› ብለው ነበር፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ መነሻ ምክንያት ቢሆንም፣ እስካሁን አለመመለሱና መፍትሔ አለማገኘቱ እንዳሳሰባቸው ነው አቶ አብዩ የተናገሩት፡፡

‹‹የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ ይመለስ›› ከሚሉ ወገኖች በተቃራኒ የቆሙ ሕወሓትን ጨምሮ ሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎች በበኩላቸው፣ ምዕራብ ትግራይ የሚሉት ቀጣና ደግሞ ወደ ትግራይ እንዲመለስ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡

የትግራይ ኃይሎች በዋናነት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን በማጣቀስ ወልቃይት የትግራይ ግዛት ሆኖ መቆየቱን ለማሳመን ሲጥሩ ይታያል፡፡ በተለይ ሕወሓት ምዕራብ ትግራይ ወደ ትግራይ ካልተመለሰ የሚል ጠንካራ አቋም የያዘ ሲሆን፣ ከሰሞኑ መፍረሱ የታወጀውና ሊጀመር ነው ተብሎ ሲጠበቅ ለቆየው ድርድር እንደ አንዱ ቅድመ ሁኔታ በማድረግ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዳግም የጦር ግንባር መሆኑ እንደማይቀር እንደሆነ ሲገመት የቆየው የወልቃይት አካባቢ፣ ከሰሞኑ ከባድ ውጊያ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በርካታ የታሪክ፣ የሰነድና የሰው ማስረጃ ለይገባኛል ጥያቄዎች በማሳመኛነት የሚቀርብበት የወልቃይት አካባቢ፣ በአንዳንዶች እምነት ለመዳኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ለአካባቢው ፖለቲካዊ መፍትሔ ማፈላለግ ካልተቻለ የሚያስከትለው ዕልቂት ከዚህ እንደሚከፋ ነው የሚገመተው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ እንደሚመለስ መንግሥት አስታውቋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያም፣ ወልቃይት ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ያገኛል የሚለውን ጉዳይ ደግመውታል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ የተወሰደብን እያንዳንዷ ኢንች መሬት ወደ ትግራይ ትመለሳለች፤›› ሲል የቆየው ሕወሓት፣ በዚህ ሐሳብ ሲስማማ አልታየም፡፡ ከምዕራብ ትግራይ መከላከያን ጨምሮ ሁሉም ኃይሎች ያለ ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ካልወጡ የሚል ቅድመ ሁኔታን የሕወሓት ባለሥልጣናት ሲያስቀምጡ ይታያል፡፡ ይህንን ደግሞ ሕወሓትን ደጋፊ የሆኑ ምዕራባውያን ኃይሎች ጭምር በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ይታያል፡፡

‹‹ከተከዜ ማዶ ሆነው ሁልጊዜ በአቦ ሰጥ ይተኩሳሉ፣ ነገር ግን የወገን ጦር ጠንካራ መከላከል አበጅቶ እየጠበቀ ነው፡፡ የወልቃይትን ጉዳይ ሕወሓቶች በጦርነት እንፈታዋለን ቢሉም፣ ነገር ግን የአካባቢው ሁኔታም አመቺ ባለመሆኑ አይሳካላቸውም፡፡ ምድሩ በተፋሰስ የተከፈለ ገደላማና ተራራማ በመሆኑ ራሱን በራሱ ይጠብቃል፤›› በማለት ነው የአካባቢውን ሁኔታ በጥልቀት የሚያውቁት አቶ ተስፋ የሺወንድም የሚናገሩት፡፡

ከሰሞኑ ሕወሓቶች ጠንካራ ጥቃት በወልቃይት ግንባር ቢከፍቱም፣ ጠንካራ የመከላከል ምት እንደገጠማቸው አቶ ተስፋ አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለ30 ዓመታት የሕወሓትን ግፍ ሲቀምስ የኖረው የወልቃይት ሕዝብ ራሱን ለመከላከል ዝግጁ አድርጎ ከወገን  ጦር ጋር ለጋራ መከላከል ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ይናገራሉ፡፡

‹‹የሕወሓት ኃይሎች ከከፈቱት የመሣሪያ ጦርነት ጎን ለጎን ወልቃይትን በፕሮፓጋንዳ ጦርነት ከእጃቸው ለማስገባት ይፍጨረጨራሉ፡፡ በፌዴራል መንግሥቱና በአማራ ኃይሎች መካከል መከፋፈል ለመፍጠር ያልተጨበጠ ወሬ ያስወራሉ፡፡ ‹ወልቃይት ለትግራይ ሊሰጥ ነው› ከሚል ውሸት ጀምሮ፣ በወልቃይት ሰላም አስከባሪ ይሠፍራል› እስከሚሉ ውሸቶች ያስነግራል፡፡ ይህ ደግሞ የወገን ኃይልን በመበታተን ወልቃትን በግርግር የራሳቸው ለማድረግ አስበው የሚያደርጉት ነው፤›› በማለት አቶ ተስፋ የወልቃይትን ጉዳይ ያብራራሉ፡፡

የሕወሓት ፖለቲከኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወልቃይት ጉዳይ የሚያራምዱት ፖለቲካ ከአማራ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ወደ ድርድር ለመግባት እንቅፋት እንደሚሆንባቸው የሚገምቱ በርካታ ናቸው፡፡

የሕወሓት ቀንደኛ ደጋፊ በመሆናቸው የሚጠቀሱት የኖርዌዩ ምሁር ሼትል ትሮምቦል (ፕሮፌሰር) ከሰሞኑ በትግራይ ቴሌቪዥን ባደረጉት ቆይታ ይህንኑ ጉዳይ ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹የትግራይ ኃይሎች በሰብዓዊ ረድዔት፣ በመሠረተ ልማት አገልግሎትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መደራደር ቢችሉም፣ ነገር ግን በአጨቃጫቂው የወልቃይት ጉዳይ ላይ ለመደራደር ጊዜው አይመስለኝም፤›› በማለት ትሮምቦል ተናግረዋል፡፡ በእርሳቸው አስተያየት ወልቃይት ወይም ምዕራብ ትግራይ በሒደት በሚካሄድ ድርድር ካልሆነ፣ አሁን ካልተለቀቀልን፤›› የሚል ቅድመ ግዴታ በማስቀመጥ አይፈታም፡፡

በሕወሓት ባለሥልጣናት በኩል ግን ይህንን ዓይነቱ ፍላጎት ያለ አይመስለኝም፡፡ የሕወሓት ባለሥልጣናት ወደ ድርድር ከመገባቱ በፊት፣ ‹‹ሁሉም የመንግሥት ኃይል ከወልቃይት እንዲወጣ›› የሚል ግዴታ አስቀምጠዋል፡፡ የሕወሓት ኃይሎች የኢፌዴሬ መከላከያ ጭምር ሥፍራውን እንዲለቅ ሲያሳስቡ ነው የቆዩት፡፡፡ ይህ ካልሆነ ወደ ድርድሩ እንደማይገቡ የገለጹት ሕወሓቶች፣ በስተመጨረሻ ‹‹ትግራይን ነፃ እናወጣለን፤›› በሚል የሰሞኑን ጦርነት ማወጃቸው ተነግሯል፡፡

ሆኖም መንግሥት የሕወሓቶችን ቅድመ ግዴታ ተቀብሎ ምዕራብ ትግራይን (ወልቃይትን) ለሕወሓቶች ቢሰጣቸው፣ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ከመምጣት ይልቅ ሕወሓቶች ትግራይን ከኢትዮጵያ ወደ መገንጠል ይገባሉ የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

‹‹የሕወሓቶች በወልቃይት በኩል የከፈቱት ጦርነት ሁሌም እንደነበረ ነው፣ አሁንም ሙከራው አለ፡፡ ጦርነቱ ካዋጣቸው ይግፉበት፡፡ እኔ እስከማውቀው ግን አመፅ እየሆኑ ነው ያለው፤›› ሲል ይናገራል የፖለቲካ ተንታኙ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን፡፡ ጦርነቱን አሁን ላይ በወልቃይት ግንባር አፋፍመው የጀመሩበትን ምክንያት ያብራራው ሙሉዓለም፣ ‹‹አንደኛ ክረምቱ እንዳያመልጣቸው ካላቸው ፍላጎት ወይም የጊዜ ሩጫ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ጦርነቱን ቀጣናዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ በማሰብ ነው፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

በወሎ ወይም በሰቆጣ ግንባሮች የሚያደርጉት ወረራ የመደራደር አቅማቸውን ለማስፋት እንደሆነ ያመለከተው ሙሉዓለም፣ በሁሉም አቅጣጫ ያውም በአንዴ ጦርነት ማወጁ ለሕወሓቶች የከፋ ኪሳራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ሕወሓት በወልቃት በኩል ጥቃት መክፈቱን ተናግሯል፡፡ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ሕወሓት በዋግ፣ በወልቃት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ ከፍቷል ብሏል፡፡ ‹ሕወሓትን ያለ ጦርነት መኖር የማይችል› ሲል የሚጠራው የመንግሥት መግለጫ፣ ‹‹የሕወሓት እብሪት ለሰላም የተዘረጉ እጆች እንዲታጠፉ እያስገደደ ነው፤›› በማለት ነው ጠበቅ ያለ ማሳሰቢያ የሰጠው፡፡

በቅርቡ የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹‹ምዕራብ ትግራይ ተወሮ ለምን ትደራደራላችሁ? የሚል ግፊት ቢኖርብንም፣ ለሰላም ባለን ቁርጠኝነት ወደ ድርድር ለመግባት ዝግጁ ነበርን፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ይህን ከማለታቸው ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ ግን፣ ‹‹ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙ ፈርሷል፤›› የሚል መረጃ ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ብዙዎች እንደሚገምቱት መንግሥት የወልቃት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ ይፈታል ብሎ የገባውን ቃል ሕወሓቶች ለመጠቀም ትዕግሥት አለማሳየታቸው ፖለቲካዊ ኪሳራ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚገምቱት ከሆነ ደግሞ ሕወሓቶች የወልቃይት ጥያቄ አሁኑኑ ካልተመለሰ ብለው በወልቃይት ግንባር ጦርነት ማወጃቸው እብሪት የታከለበት ዕርምጃ ነው፡፡

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሕወሓቶችን የወልቃይት ግንባር ጦርነት፣ ‹‹የውጭ ኃይሎች ፍላጎትን ለማስፈጸም የታለመ ዘመቻ፤›› ሲሉም ይጠሩታል፡፡ ሕወሓቶች እንዳሰቡት ‹‹ትግራይን ነፃ ማውጣት›› ባሉት በዚህ ጦርነት ወልቃይትን ጨምሮ ሌሎች ተይዞብናል የሚሉትን መሬቶች ለማስመለስ ይሳካላቸው ይሆን ወይ? የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ቀናት የሚመለስ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -