የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከሁለት ዓመታት በፊት ለተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለሌሎች የአየር ትራንስፖርት (የአቪዬሺን) ዘርፍ የመድን ሽፋኖች የከፈለው ከፍተኛ የጉዳት ካሳ በ2014 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የካሳ ክፍያ ወጪውን በ327 በመቶ እንዳናረበት አስታወቀ።
ድርጅቱ የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ በ2014 ዓ.ም. ለካሳ ክፍያ ያዋለው አጠቃላይ ወጪ 5.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በድርጅቱ ታሪክ ለጉዳት ካሳ የተከፈለ ከፍተኛ ወጪ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ድርጅቱ በ2014 የሒሳብ ዓመት በደንበኞቹ ንብረትና ሕይወት ላይ ለደረሰ አደጋ፣ እንዲሁም ከሕጋዊ ኃላፊነት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የከፈለው ክፍያ ከቀዳሚው ዓመት በ327 በመቶ ለመጨመሩ ዋናው ምክንያት ደግሞ ከአቪዬሽን መድን ሽፋን ጋር በተያያዘ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ካሳ በመክፈሉ ነው፡፡ በተለይ ከሁለት ዓመታት በፊት ለተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለሰጠው የመድን ሽፋንና ለሌሎች የአቪዬሸን ሽፋኖች በሒሳብ ዓመቱ ከ3.8 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለተከሰከሰው አውሮፕላን የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያው ከሚከፍለው ካሳ ወጪ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለዚህ ዋስትና ሽፋን አውሮፕላኑ ከተከሰከሰበት ጊዜ ጀምሮ ለዚህ ክፍያ የሚውል ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ መጠባበቂያ ሲይዝ ቆይቶ እንደነበር ታውቋል፡፡
ዘንድሮ ግን መክፈል ያለበት ትክክኛ ሒሳብ የቀረበለት በመሆኑ ከተከሰከሰው የኢትዮጵያ አውሮፕላን ጋር በተያያዘ ለሰጠው የመድን ሽፋን ለተገዛው በ2014 የሒሳብ ዓመት 3.8 ቢሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ሊከፍል መቻሉ ታውቋል፡፡ ይህም ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ለጉዳት ካሳ ክፍያ ያዋለውን የገንዘብ መጠን በእጅጉ እንዳናረው የሚያመለክተው የድርጅቱ መረጃ፣ በሒሳብ ዓመቱ ለአቪዬሽን የመድን ሽፋን ከከፈለው ካሳ በተጨማሪ ለሌሎች የመድን ሽፋኖች 1.6 ቢሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መክፈሉንም ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2013 የሒሳብ ዓመት ለአጠቃላይ የጉዳት ካሳ የከፈለው 1.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከድርጅቱ የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባለፈው ሐሙስ በተካሄደው የድርጅቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንደጠቀሱትም፣ ድርጅቱ በ2014 የሒሳብ ዓመት የከፈለው ካሳ መጠን ከዕቅዱ የ33.7 በመቶ ቅናሽ ያለው ቢሆንም፣ ለካሳ ክፍያው የዋለው የገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ327 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ከዚህ ከተከፈለው የካሳ ክፍያ ውስጥ የጠቅላላ መድን ድርሻ ብር 5.3 ቢሊዮን ብር ወይም 98.4 በመቶ ድርሻ ሲይዝ፣ የረዥም ጊዜ መድን (ሕይወት ኢንሹራንስ) ዘርፍ የተከፈለው የካሳ ክፍያ 86 ሚሊዮን ብር ወይም 1.62 በመቶ ድርሻ ነበረው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የድርጅቱ የጉዳት ካሳ ምጣኔ 47.6 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱም ሆነ ከኢንዱስትሪ የጉዳት ካሳ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛና አበረታች እንደሆነም አቶ ነፃነት ጠቅሰዋል፡፡
የድርጅቱን ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርታቸው፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እስከ 2014 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት ማጠቃለያ ድረስ ለደንበኞች የሰጠው የዋስትና ሽፋን ከአራት ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱን ነው፡፡ ይህም ከቀዳማዊ ዓመት የ25.4 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው ተብሏል፡፡ ድርጅቱ በ2013 የሒሳብ ዓመት ለደንበኞቹ የሰጠው የመድን ሽፋን መጠን 3.2 ትሪሊዮን ብር ነበር፡፡ በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ የ166,571 የመድን ውሎች ሽያጭና እድሳት መከናወኑን የገለጹት አቶ ነፃነት፣ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ የ2.3 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6.5 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማስመዝገቡን የሚያመለክተው የአቶ ነፃነት ሪፖርት፣ ይህ አፈጻጸሙ የዕቅዱን 99.6 በመቶ ያሳካ ሲሆን፣ የተመዘገበው የዓረቦን መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ7.3 በመቶ ወይም በ446 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡
ከተመዘገበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 6.3 ቢሊዮን ብር ወይም 96.9 በመቶ ከጠቅላላ መድን ዘርፍ፣ ቀሪው 206 ሚሊዮን ብር ወይም 3.1 በመቶ ደግሞ የረዥም ጊዜ የመድን ሽፋን ከሆነው የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበ ነው፡፡ ድርጅቱ ያስመዘገበው ዓረቦን ከኢንዱትሪው ጠቅላላ ዓረቦን ያለው ድርሻ 39.3 በመቶ እንደሆነ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ምንም እንኳን የተመዘገበው የዓረቦን ገቢ ከድርጅቱ ዕቅድም ሆነ ካለፈው በጀት ዓመት አንፃር አፈጻጸሙ አንፃር ሲገመገም መልካም ቢሆንም፣ የድርጅቱ የዓረቦን ገቢ ከዚህ በላይ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች ዋነኛው ከአቪዬሽን ዋስትና ዘርፍ የሚሰበሰበው ዓረቦን ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱ ነው። በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከአቪዬሽን የዋስትና ዘርፍ የተሰበሰበው ዓረቦን ካለፈው ዓመት የ416 ሚሊዮን ብር ቅናሽ፣ እንዲሁም ከ2014 የሒሳብ ዓመት ዕቅድ በ562 ሚሊዮን ብር ቅናሽ እንደታየበት ገልጸዋል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከተሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዙ ነው። በመሆኑም ለአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ይሰጥ የነበረው የመድን ሽፋን በዚያው ልክ እንደተቀዛቀዘ፣ ነገር ግን ወረርሽኙ የፈጠረው ሥጋት ቢቀንስም አሁንም ድረስ ለአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የሚሰጠው የሕይወት መድን ሽፋን ተጠቃሚ ደንበኞች ውሎቻቸውን ለማደስ ፍላጎት ባለማሳየታቸው፣ ድርጅቱ ከዚህ ዘርፍ ይሰበስብ የነበረው የዓረቦን ገቢ መቀነሱን ገልጸዋል። በመሆኑም ከአቪዬሽን ዘርፍ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ መታጣቱን በዚሁ ሪፖርታቸው ላይ አመላክተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶች ባያጋጥማቸው ኖሮ ድርጅቱ የሚያድግበትን መጠንም ሆነ የገበያ ድርሻ ላቅ ያለ ሊሆን ይችል እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
የድርጅቱን የ2014 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት ከኢንቨስትመንትና ሌሎች ገቢዎች 528.3 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ሪፖርቱ ያመልክታል። ይህ ገቢ በባንኮች ከተቀመጠ ገንዘብ የወለድ ክፍያ፣ ከሕንፃ ኪራይና ከሌሎች ገቢዎች የተገኘ መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ይህ የገቢ መጠኑ ደግሞ ድርጅቱ ከኢንቨስትመንትና ከሌሎች ገቢዎች ያገኘው አጠቃላይ ገቢ ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ49.4 ሚሊዮን ብር ወይም የ10.3 በመቶ ዕድገት የታየበት ቢሆንም፣ ከዕቅዱ አንፃር ግን የ46.3 ሚሊዮን ብር ወይም 8.1 በመቶ ቅናሽ የታየበት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል፡፡
ድርጅቱ በሒሳብ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም በድርጅቱም ሆነ በኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ ያስመዘገበበት ሆኗል፡፡ ይህም ከታክስ በፊት ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር በ2.3 በመቶ፣ እንዲሁም ካለፈው ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ17.1 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ከታክስ በፊት አትርፎ የነበረው 1.12 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱ የተገለጸበት እንደሆነ አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በመካከለኛ ዘመን ዕቅዱ ከውጭ ሊመጡ ከሚችሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ሊያደርገው የሚያስችል አዲስ የስትራቴጂ ዕቅድ ዝግጅት ውስጥ መግባቱን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የ2014 የሒሳብ ዓመቱን የሥራ አፈጻጸምና የ2015 ዕቅዱን በተመለከተ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው፣ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቀየስና ግቦችን በመጣል ለተግባራዊነታቸው ሲንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በተለየ ስትራቴጂ ለመንቀሳቀስ ወስኗል። እስካሁን ከነበሩ ስትራቴጂዎቹ በተለየ መጓዝ ያስፈለገበትም ዋነኛ ምክንያትም መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ፣ ‹‹ባለፉት ዓመታት ያጠናቀቅናቸው የስትራቴጂካዊ ዕቅዶቻቸውን ለውጭ ገበያው ዝግ የነበረውን የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ አገር ውስጥ ገበያ ውድድር መነሻ አድርገው የነበሩ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ገበያ ክፍት ሊያደርግ የሚችልባቸው የሪፎርም ሥራዎች የሚጠበቁ በመሆናቸው እስከዛሬው በተለየ መጓዝ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣናዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚፈጥሩ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ ሥልታዊ ዕቅድ ማዘጋጀት የግድ እንደሚል አቶ ነፃነት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ለዚሁ የሚሆን ‹ቢጋር› የተዘጋጀና በየደረጃው ለሚሳተፉ አካላት በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ የሥልጠና፣ የልምድ ልውውጥና ሙያዊ ድጋፎችን ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር አካላት ጋር በማመቻቸት ወደ ሥራ እየተገባ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ነፃነት ገለጻ፣ በሒሳብ ዓመቱ ስኬታማ የሚባል አፈጻጸም የተመዘገበ ቢሆንም፣ በሥራ ሒደታቸው ውጤቱን ለማስመዝገብም ሆነ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ የተፈለገውን ያህል መጓዝ እንዳይቻል ያጋጠሙ ችግሮች በርካታ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
ካጋጠሟቸው ችግሮች መካከል በዋናነት የጠቀሱት በኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች፣ በዚህም ምክንያት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች፣ በተለይም ደግሞ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነቱ ቀጣና አካባቢ የሚገኙ ቅርንጫፎቻችን በበቂ ሁኔታ ሥራ ለመሥራት ያለመቻላቸው ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ከዩክሬንና ከሩሲያ ጦርነት ጋርና በዓለም አቀፉ ደረጃ ከታየው የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ የመለዋወጫ ዋጋና የጥገና ወጪ መናር፣ ከሕንፃ ፕሮጀክት ግንባታ ጋር በተያያዘ ያለው አፈጻጸም በልዩ ልዩ ተግዳሮች ምክንያት ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በግዥ ሒደትና በሪፎርም ትግበራ ላይ ያሉ ሥራዎች ከተጠበቀው በላይ ጊዜ መውሰዳቸው፣ እንዲሁም በገበያው ላይ እየተስተዋለ ያለው በዋጋ ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ ፉክክር ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በዚህ ሳምንት ለሁለት ቀናት በቆየው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የ2015 የሒሳብ ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል፡፡ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በ2015 የሒሳብ ዓመት የሚሰባሰበውን ጠቅላላ የዓረቦን መጠን 7.3 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የሚል ይገኝበታል፡፡ ይህ ዕቅድ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዲኖረው ታሳቢ ተደርጎ የተያዘ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን፣ ብቸኛው መንግሥታዊ የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው፡፡