Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የውትድርና አልባሳትን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ውጥን ደብተርና እስኪብርቶንም አይዘንጋ!

የአገራችን የዋጋ ንረት ያልነካካው ነገር የለም፡፡ በየትኛውም የገበያ ሥፍራ ሸማችን እያማረረ ከዘለቀ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የትኛውም ሸቀጥ ዋጋው ጨመረ እንጂ ቀነሰ ሲባል አይሰማም፡፡ የአንዳንድ ምርቶች የዋጋ ዕድገት ደግሞ አስደንጋጭ የሚባል ነው፡፡ በሰዓታት ልዩነት ሳይቀር ዋጋቸው ሽቅብ የሚወጡ፣ ከወጡም በኋላ የማይመለሱ ምርቶችም ቁጥር እየበረከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ልጓም ባጣው የዋጋ ንረት ሸማቾች እየተማረሩ ነው፡፡ ይህ ሳያንስ ዓውድ ዓመትን አስታከው የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች ሲታከሉ ደግሞ የዋጋ ንረቱን ሥጋት የበለጠ ያደርገዋል፡፡ አዲሱ ዓመት ዋዜማ ገበያም ይህንን ይነግረናል፡፡ በዓሉንና ለአዲስ ዓመት አስፈላጊ የሚባሉ ዕቃዎች ከወዲሁ ዋጋቸው ወደላይ እየወጣ ነው፡፡ ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉ ዕቃዎችን ትተን መስከረም በጠባ ቁጥር ገበያው የሚደራውን ትምህርት መሣሪያዎችን ዋጋ ብቻ እንመልከት፡፡ 

መጪው አዲስ ዓመት ሲታሰብ በየቤቱ በፍጹም ሊቀር የማይችል ነገር ቢኖር ይኸው የትምህርት መሣሪያዎች ግብዓት ነው፡፡ የትምህርት ዘመኑ አንድ ተብሎ የሚጀመረው ከመስከረም ወር በመሆኑ ከወዲሁ ከፍተኛ ግብይት ከሚፈጸምባቸው ምርቶች ውስጥ የትምህርት ግብዓቶች በቀዳሚነት ይጠቀማሉ፡፡ ከጀማሪ ትምህርት ቤት (KG) እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከ35 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እንዳሉ በሚታመንበት አገር ለትምህርት ዘመኑ የሚያስፈልገው የጽሕፈት መሣሪያዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስበት መገመት አያዳግትም፡፡ 

በመሆኑም ለእነዚህ ሁሉ ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት መሣሪያዎች ግብዓት ከወዲሁ ገበያውን ይዞታል፡፡ ሸመታው ተጀምሯል፡፡ ዋጋው ግን ለብዙዎች ሸማቾች ያስደነግጣል፡፡ እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ የትምህርት መሣሪያዎችም ዋጋ ከታሰበው በላይ ሆኖ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ 

እነዚህ የጽሕፈት መሣሪያዎች ዋጋ አስደንጋጭ የሚባል ሲሆን በተለይ የደብተር ዋጋ ከቀደመው ዓመት በእጥፍ በሚባል ደረጃ ማሻቀቡ ለብዙዎች ሸማቾችና ወላጆች ዱብ ዕዳ ሆኗል፡፡ የአዲስ ዓመት ወጪ የሚጠብቀው የቤተሰብ አስተዳዳሪ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ለሚያስፈልጉት የትምህርት ግብዓቶች የሚወጣው ወጪ ከዚህ በፊት በየትምህርት ዘመኑ ሲያወጣ ከነበረው በእጅጉ የሚልቅ ሆኖ የመገኘቱ ነገር ቢያሳስብ አይገርም፡፡ ምክንያቱም በሌሎች ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ የተማረረ ሸማች ሊያስቀረው የሚችለው ደብተር ዋጋው እንዲህ ሲሰቀል ኑሮውን ቢያማርር ምን ይፈረድበታል፡፡ 

አንድ ባለመቶ ቅጠል ደብተር እንደየ ደብተሩ ዓይነት የችርቻሮ ዋጋው እስከ 80 ብር ደርሷል፡፡ ባለሃምሳ ቅጠል ደብተር ደግሞ እስከ 50 ብርና ከዚያም በላይ እየተሸጠ ነው፡፡ 

በጣም አስገራሚው ደግሞ ይህ ከሰሞኑ እየሸጠበት ያለው የደብተር ዋጋ በየዕለቱ ጭማሪ እየታየበት በመሆኑ ከዚህ በኋላም ይጨምራል የሚል ሥጋት መኖሩ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ለ2014 የትምህርት ዘመን ገብተው የተረፉና በየመደብሩ የነበሩ ደብተሮች ወጥተው አዲስ በተለጠፈላቸው ዋጋ እየተሸጡ ነው፡፡ 

የደብተር ዋጋ በዚህን ያህል ደረጃ የመጨመሩ ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ በእርግጥ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችና እየታየ ካለው አጠቃላይ የዋጋ ንረት አንፃር እንደ ሌላው ምርትና ሸቀጥ ሁሉ የተወሰነ ጥሪ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል፡፡ ነገር ግን አሁን በሚታየው ደረጃ ይጨምራል ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡ ነገር ግን ሆኖ እያየነው ነው፡፡ 

ሁለትና ከሁለት በላይ ልጆች የሚያስተምሩ ወላጆች ለደብተር ለእስክሪብቶና ለሌሎች የትምህርት ግብዓቶች የሚያወጡት ወጪ ሲታሰብ ብዙዎች ለዓውድ ዓመት ብለው የቋጠሯትን ለደብተር፣ እስክሪብቶ፣ ለቦርሳና ለመሳሰሉት አውለው ዓውድ ዓመቱን አስበው የሚሉ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የወላጆች ወጪ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ግዴታ ነውና ዩኒፎርም ማሰፋት አለባቸው፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ወላጆች ደግሞ ከሰሞኑ የሚጠበቀው የትምህርት ቤት ክፍያ ሲታከል የመስከረም ወጪ ከዋጋ ንረቱ ጋር ተደምሮ ጫናውን ያበረታባቸዋል፡፡  

ለምሳሌ ሦስት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ልጆች ያሉት ወላጅ በአነስተኛ ግምት ለሦስቱ ልጆች እስከ 50 የሚደርስ ደብተር ያስፈልገዋል ቢባልና ለአንዱ ተማሪ ለዓመቱ የሚፈልገው ከ15 እስከ 17 የማደርስ ባለ መቶ ቅጠል ደብተር ከሆነ ለእነዚህ ሦስት ልጆች እስከ 4000 ሺሕ ብር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ 

ቦርሳ የሚያስፈልግ ከሆነ ተራ የተባለ ቦርሳ ከ700 ብር ካልሆነ አሁን ባለው ዋጋ እስከ 2000 ሺሕ ብር ያወጣል፡፡ በአማካይ 1,200 ብር ብንል ለቦርሳዎቹ ግዥ ተጨማሪ 3,600 ብር ይጠይቃል፡፡ ዩኒፎርምና መጫሚያ ሲታከል ደግሞ ሦስት ልጆች የሚያስተምር ወላጅ ከሰሞኑ በትንሹ አሥር ሺሕ ብር ወጪ ይጠብቀዋል ማለት ነው፡፡ ይህንን ያህል ወጪ የሚያወጣው አቅም ካለነው፡፡ በሚሊዮን የማቆጠሩ ወላጆች ግን አሁን ባለው የዋጋ ንረት የልጆቻቸውን የትምህርት ግብዓት የሚሆኑ መሣሪያዎችን አሟልተው ወደ ትምህርት ይልካሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የትምህርት ግብዓቶች ዋጋ በዚህን ያህል ደረጃ ማሻቀባቸው አስደንጋጭ ነው ቢባል ማጋነን ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን እጅግ አሳሳቢ የሆነ ችግር እንደ ዋዛ ማለፍም አይቻልም፡፡ 

ስለዚህ ለዋጋ ጭማሪው የሚሰጠው ሰበብ ምንም ይሁን ምን በዚህ ዋጋ የትምህርት ግብዓቶች ገዝቶ ሊጠቀም የሚችለውን ዜጎች ምን ያህል ነው? የሚለው ታሳቢ በማድረግ አንድ መፍትሔ መቀመጥ እንደሚኖርበት ያመለክታል፡፡ 

የትምህርት ግብዓት በተለይ ደብተርና እስክሪብቶ እንደ ሌላው ሸቀጥ በዘፈቀደ ዋጋ የሚጨመርበት እንዲሆን መፍቀድ ይገባል ተብሎም አይታሰብም፡፡ ደብተር እስክሪብቶና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶች መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች ሰንጠረዥ ውስጥ መካተት የሚኖርባቸው ቢሆንም ይህንን ታሳቢ ያደረገ አሠራር አልተዘረጋም፡፡ 

ተማሪ ያለ ደብተርና እስክሪብቶ ወደ ተማሪ ቤት አይሄድም፡፡ መልካም ዜጋ ለመቅረጽ የትምህርት አስፈላጊነት የማያከራክር ከሆነም የትምህርት ግብዓቶችም እንደ ማንኛውም ሸቀጥ በዘፈቀደ ዋጋው የሚቆለልባቸው መሆን የለበትም፡፡ ከሰሞኑ በገበያ ውስጥ ያለው የደብተርና እስክሪብቶ ዋጋ የብዙዎችን ሸማቾች አቅም ያገናዘበ አይደለም፡፡ በትክክልስ ይህ ዋጋ ኢኮኖሚያዊ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ 

ነጋዴውም ቢሆን ተማሪ ልጅና ቤተሰብ አለውና ችግሩ የእርሱም በመሆኑ የትርፍ ህዳጉን መጥኖ መሸጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለማንኛውም ያው እንደለመድነው ችግሮቻችንን ወደ መንግሥት መውሰዳችን አይቀርምና መንግሥትም ጉዳዩን መፈተሽና መፍትሔ ካለ እንዲያስተካክል ይጠበቃል፡፡

በተለይ የደብተር ዋጋው በእርግጥ አሁን እየተሸጠበት ያለው ዋጋ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ያለው ወይም የሌለው መሆኑን ማጥራት ይችላል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረተውም ሆነ ከውጪ የሚመጣው ደብተር አጠቃላይ ወጪው ይታወቃልና እየተሸጠበት ካለው ዋጋ ጋር በማገናዘብ የችርቻሮው ዋጋ የሚመጠንበትን መንገድ ቢያፈላልግ ብዙዎችን መታደግ የሚችልበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለዘለቄታው ግን እንዲህ ያሉ ምርቶች የትርፍ ህዳጋቸው እንዲመጠን የማድረግ ዋጋቸውን መቆጣጠር የግድ  ሊል ይችላል፡፡ ነጋዴዎችም ቢሆኑ በሁሉ ምርቶች ላይ ስንጥቅ እያተረፉ መዝለቅ አይችሉም፡፡ ለህሊና መገዛትንም ይጠይቃል፡፡ እስቲ እንተሳሰብ፡፡ እንረዳዳ!! ከዚህ ማሳሰቢያ ባሻገር ግን የትምህርት ግብዓቶች በተለይ እንደ ደብተርና እስክሪብቶ ያሉ ምርቶች ሁሌም የሚያስፈልጉ ጠቀሜታቸውም እጅግ ከፍ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዋጋቸው የሚመጠንበትን ፖሊሲ ማመቻቸት ተገቢ ይሆናል፡፡ 

አሁን ገበያ ላይ ያሉ አብዛኞቹ የደብተርና የእስክሪብቶ ምርቶች ደግሞ ከውጪ የሚገቡ በመሆናቸው ዋጋቸው እንዲሰቀል ምክንያት ሊሆን መቻሉን በማሰብ በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማበረታታት አንድ መፍትሔ ይሆናል፡፡ እነዚህ ምርቶች የሚያመርቱ ጥቂት ፋብሪካዎች ያሉ ቢሆንም እንዲሰፋና ምርት እንዲያበዙ የሚጋብዝ ዕድል ያልተመቻቸላቸው መሆኑ አዳዲስ ፋብሪካዎች እንዳይፈጠሩ ማድረጉ እየተነገረ በመሆኑ ይህንን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ነገም የሚጠብቀን ከዚህ የባሰ ስለሚሆን መንግሥት እነዚህን ምርቶች መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች አንዱ በማድረግ ገበያውን ቢቆጣጠር ምርቱም በአገር ውስጥ እንዲስፋፋ ዕገዛ ቢያደርግ ብዙ ነገሮችን ማስተካከል ይችላል፡፡ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ወላጆችና ተማሪዎች በደብተርና እስክሪብቶ ዋጋ መጨነቅ የለባቸውም፡፡ ደብተርና እስክሪብቶ ለማቅረብ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልግ ከሆነ ኢኮኖሚው ላይ ችግር አለ ማለት ነው። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያስተዳደሩና በዓመት በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እያስተማሩ በቂ ደብተርና እስክሪብቶ በአገር ውስጥ አለመመረቱ የኢኮኖሚ ልማት አስተዳደር ላይ ያለውን ችግር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም የፀጥታ አካላት ወይም የውትድርና አልባሳትን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለማምረት ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ ለደብተርና እስክሪብቶም ትኩረት ያሻል። 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት