በነሲቡ ስብሐት
በቅድሚያ ሦስቱ የኪነት አበባዎች ብዬ የሰየምኳችሁ ቅድስት ይልማ፣ አዜብ ወርቁና ቤዛ ኃይሉ ደራሲነት የሁሉም ተዋንያን ድንቅ ችሎታና ብቃት ለታየበት “እረኛዬ” ተከታታይ ተውኔት ያለኝን አድናቆት ስገልጽ በምሥጋናዬ ውስጥ አገሬና ሕዝባችን እየታዩኝ ነው።
ስለአገራችን ኢትዮጵያና ስለሕዝቧ በርካታ ድምፃውያን፣ ደራሲያን፣ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች፣ ሠዓሊያን፣ ተዋንያን እንደየዘርፋቸው አዚመዋል፣ አንጎራጉረዋል። ከያኒያን አገሬን ብለው ገጥመዋል፣ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አርገዋል፣ ወንዞች ተራሮቿን ዳሰዋል፣ ዓባይን ከብዕራቸው አፍስሰው ስንኝ ቋጥረው አድንቀዋል፣ ኢትዮጵያችንን አንድ መጽሐፍ ከሚገልጸው በላይ በሥዕሎቻቸው ተናግረውላታል።
ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ወይም ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኝ ነን ብለው እንደ አሸን ከሞሉት ምሁራን በእጅጉ በሚያስንቅ ሁኔታ ድምፃውያን ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋታል። የአገር አንድነት እንዳይዛባ በድምፃቸው ጮኸዋል፣ መድረክ ላይ ወጥተው ጀግኖችን ቀስቅሰዋል፣ አወድሰዋል። ታሪክን አዚመዋል፣ ቅርስን አስተዋውቀዋል።
በዚህ ጽሑፌ በቅርቡ የተጠናቀቀው የ“እረኛዬ” ተከታታይ ተውኔት የዜማ ቅላፄ፣ የቅኔ ዘረፋ፣ የመቼት መረጣ፣ የአብሮነት ዜማ፣ የእናትነት አንጀት፣ የሃይማኖት ክብሩ፣ የዘራፊን ምግባሩ፣ ኢትዮጵያዊነት ክብሩ፣ ደግነቱ፣ አብሮነትን፣ ይቅር ባይነትን፣ የትውልድ፣ የታሪክ፣ የአገር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የሰው በሰው ሥራ ሌላም ሌላ እውነትን አፍክቶ፣ ማንነትን አውጥቶ፣ ስሜትን ገዝቶ ከመደነቅ አሻግሮ ዛሬም ትውልድ አለ፣ ዛሬም ነገም አገር አለች፣ ያስባለኝን ውስጤን በመጠኑም ቢሆን ለአንባቢያን ላጋራ ፈለግሁ።
“እረኛዬ” አሸንፏል! በዘርና በቋንቋ በተከለለች አገር ዘረኝነት ላይ ዘምቷል፣ በሙስና በተጨማለቀች አገር ሌብነትን አጋልጧል፣ አኩሪ ባህሉን እንዲዘነጋ በተደረገ ትውልድ ላይ “ባህሌን አገሬን” አዚሟል፡፡ በጥላቻ፣ በቂም ላይ ፍቅርን፣ ይቅር ባይነትን ሰብኳል፡፡ በትዳር ውስጥ የእናት ሆድ ዥንጉርጉርነትን ተንተርሶ የእናትነት መንሰፍሰፍን ዳሷል። ሌላም ሌላ፡፡ ከደራሲያኑ ብጀምር የሴቶችን ጠንካራ አመራር ሰጪነትና ኅብረት “እረኛዬ” ይመሰክራል። ዛሬ አንዱ ለአንዱ ምቀኛና ቀናተኛ በሆነበት አገራችን በጋራ ሠርተው የጋር ፍሬያቸውን በጋራ እንድንመለከት፣ እንድንመሰጥ፣ እንድንገረም፣ እንድናለቅስና እድንጓጓ እያደረገ የተጓዘ ተውኔት ነበር ብል አብዛኞች ይጋሩኛልና ልክ ነኝ።
“እረኛዬ” ኪነት ለአገር፣ ኪነት ለኢትዮጵያ፣ ኪነት ለሕዝብ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ በላይ ሥር የሰደደ መልዕክት የተላለፈበት ተውኔት ነው። “እረኛዬ” በጨለማ ውስጥ የደመቀ ኮከብ ነው። ደምቆም አላቆመም ተወርዋሪ ሆኖ ሕዝብ ጋ ደርሷል።
“እረኛዬ” በአብነት መንደር ኢትዮጵያዊነትን ረጭቶ በእማማ ቸርነት ጎጆ መማር ለፈለገ ትህትናን፣ ቀናነትን፣ አብሮነትን አስተምሮ የተጓዘ ተውኔት ነው፡፡ ወግን፣ ጥጋብን፣ ጥበብን፣ ፍቅርን፣ እንባን፣ ዝላይን፣ ጭፈራን፣ ታዛዥነት፣ ትህትናን፣ በእናና አጋጅነት ተሰባስበው የተረጩበት ተውኔት ጎልቶ የታየበት ተመልካችን ያስደመመ ሁሉም ዘር ዓይንና ጆሮ የሰጠው ተውኔት ደራሲያኑንና ከኒያኑን በጥቅሉ በ“እረኛዬ” ላይ አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉ ደስ….ስ ስላለኝ አመሠግናለሁ።
በዚህ አጋጣሚ ስለአገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ድምፃውያን አድምቀው አንጎራጉረዋል። ሁሉንም ባይሆን ስሜቴን ከኮረኮሩት ውስጥ ትንሽ ልበልና ላስታውሳቸው፡፡ ዛሬ ከመድረኩ ራቅ ብትልም ሕወሓት/ኢሕአዴግ “ጉሮ ወሸባዬ” ብሎ የዛሬ 31 ዓመት ይዞት የተነሳውን ዘረኝነት ገና ከጅምሩ ‹‹የዘር በሽታ፣ መድኃኒት አለው የማታ ማታ›› ብላ አንጎራጉራ የፍቅር ረሃቧን ለአየር ያበቃችው ጂጂ እምቅ ሥራዎችን መለስ ብዬ እንድቃኝ አድርጎኛል። ‹‹ጎጃም ያረሰውን ወለጋ ካልሸጠ፣ የሸዋ ሰው ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ›› ምኑን አገር አለች አገርስ ያሰኛል፡፡ ብላ ቀደምት ሙግቷን ለአገር ያበረከተችው ሥራዋ ዛሬም ነገም ሲታወስ ይኖራል።
ለዓባይ ያላዜመ ድምፃዊ ባይኖርም ስለዓባይ ሲጻፍ፣ ሲተረክ ለአገሩና ለሕዝቡ አገልጋይ ይሆን ዘንድ “ዓባይ ወቶ አዳሪ…” ብላ ዘለዓለማዊ ድምጿን ከሕዝብ አድርሳለች። የስደት ሕይወትን ከአገሯ ባህል ጋር ስትገልጸው በአጭር አገራዊ አገላለጽ “የሰው በግ እያየሁ…” ስትል ቅኔዋን ዘርፋለች። ዛሬ እምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ባላውቅም ጂጂ ብልጭ ብላ ድርግም ያለችብኝ አገርን በፍቅር፣ ባህላችንን በወግ አላስነካ ያለች ጎበዝ “ስንት በሠራች” ቁጭት ይወረኛል። “አልወድም ጎበዝ ጀግና ሲረሳ” ብላ ለጀግኖቻችን እስትንፋስ የሰጠች ኪነት ለኢትዮጵያ ያበረከተች፣ ኢትዮጵያዊነት መሠረት ውሉ እንዳይበጠስ አጥብቃ የተውረገረገች ዜመኛ ሥራዋ ሁሌም ይጠራታል።
ወያኔ/ሕወሓት ሕዝብ ሆነበትና ባይገድለውም የምሬት ዳርቻቸው ለእስር የዳረገው የኢትዮጵያ ልጅ ቴዲ አፍሮ ዕውን ማን እንደ እሱ ለአገር ሞገተ? ማን እንደ እሱ ስለአንድነት ሰበከ? ማን እንደ እሱ ኢትዮጵያዊነትን አነቃነቀ? ማን እንደ እሱ ምኒልክ፣ ቴዎድሮስ ላይ ስቅታ ለቀቀ ቢባልለት ሲያንሰው ነው።
የዛሬ 17 ዓመት ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ዋዜማ ለአየር በቅቶ ፖለቲከኞቻችን ገደል ቢከቱትም፣ ምርጫው በድል ይጠናቀቅ ዘንድ ፊት ለፊት የተጋፈጠው “ያስተሰርያል” ዜማው አንድነትን ፈጥሯል፣ ሕዝባዊነትን አቀናጅቷል፣ ፍቅርን አንግሷል፣ ወያኔን አርበድብዷል፣ ኢሕአዴግን ዘርሯል። ፖለቲከኞቻችንና ምሁሮቻችን መጠቀም አቃታቸው እንጂ ኦሮሞን፣ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌ፣ ከጋምቤላ፣ ከሐረሪ፣ ከወላይታ፣ ከሲዳማ ሁሉን ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ያያያዘ ነበር። “ይቅር እንባባል” ብሎ ፍቅርን የሰበከ፣ ማማዬ፣ ኢትዮጵያዬ ብሎ መድረክ ላይ የተፋለመ፣ በሚሊዮኖች ያነቃነቀ ፖለቲካውን በዜማ ቅላጼው የተቆጣጠረ ብርቅዬ ነበር ዛሬም ነው።
የቴዲ ሥራዎች በተለይ በወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት እንዳይሳሳ፣ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይረሳ፣ ጀግኖች እንዳይደበዝዙ፣ አዚሟል “ኡ ኡ ታዬ” ብሎ እሪ ብሏል። ምኒልክን አንግሦ፣ ቴዎድሮስን አሞግሶ ትውልድን ቀስቅሷል፣ አነቃቅቷል። እስላም ክርስቲያኑን አንድ ነው ቤታችን ብሎ አስተቃቅፏል። ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ አንድነትን፣ ኅብረትን በጠነከረ ዜማው ከሕዝብ አዋህዷል። ኢትዮጵያዬ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን አሳይቷል። ዘመን ከፈጠራቸው የትውልድ ጀግና፣ አዋጊ ዜመኛ፣ ድምፃዊ ፓርቲ ቢባል ይገባዋል።
“እረኛዬ” ወደ ሌላ ተዛማጅ ጉዳዮች ቢወስደኝም አንኳሩ ኪነት ምን ያህል ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለትውልድ ያላትን እምቅ ችሎታ ለማስመር ነው። የ“እረኛዬ” አባላትንም ሆነ ሌሎች ባለሙያዎች ሌላም የፈጠራ ሥራዎቻችሁን አሳዩን እያልኩኝ፣ የምሥጋና ድምፄን በአንድ ቃልና በአራት ነጥብ ላብቃ። በርቱ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡