በአራት ዓመታት አንዴ ስድስት፣ በሌሎቹ ደግሞ አምስት ቀናትን የምትይዘውን የጳጉሜን ወር፣ ኢትዮጵያውያን እንደ ባህላቸውና አካባቢያቸው በተለያየ ሁነት ያሳልፉታል፡፡
የጳጉሜን ቀናት በተለይ በሕፃናትና በታዳጊ ልጆች ልዩ ሆነው የሚያልፉ ቢሆንም፣ በአዋቂዎች ዘንድም በሃይማኖታዊ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅባ የምታልፍ ወር ናት፡፡
በጳጉሜን ቀናት በሌሊት ወንዝ ወርዶ ገላን መታጠብ፣ በከተማ ደግሞ በየአብያተ ክርስቲያኑ መጠመቅ፣ የቆሸሸም ሆነ ያልቆሸሸ ልብስን አጥቦ ወደ አዲሱ ዘመን መሻገር፣ በጳጉሜን መጨረሻው ቀን ገላን መታጠብ፣ በጳጉሜን ሦስት ቀን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ዝናብ ጠብቆ በዝናብ መጠመቅ፣ በዘመን መለወጫ ዋዜማ በጳጉሜን መጨረሻ ቀን ቂጣ፣ ቆሎ/ ፈንድሻ፣ የተወቀጠ ኑግ አዘጋጅቶና ቡና አፍልቶ አሮጌውን ዓመት መሰናበት፣ ችቦ ማብራትና እንግጫ ነቀላ፣ የታዳጊ ሕፃናት የእንቁጣጣሽ ‹‹አበባ አየሽ ሆይ›› ዘፈንና ሌሎችም የሚከወኑበት ነው፡፡
ባህላዊ ጭፈራ የሚደራበት፣ የባህል አልባሳት የሚለብሱበት፣ በዚያው ልክም የሚወደድበት ነው፡፡
‹‹የጎመን ምንቸት ውጣ፣ የገንፎ ምንቸት ግባ›› ተብሎ ወሩ የሚሸኝበት ለዓመቱ በሰላም አድርሰን ተብሎ የሚመራረቁበትም ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በመንግሥትና በግል ተቋማት ደረጃ የጳጉሜን ወር በተለያዩ ኩነቶች ማክበር ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮም የጳጉሜን አምስት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበሩ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊ ትውፊቶች ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች፣ የምርት አገልግሎቶች፣ የብሔር ብሔረሰብ ትውውቆች እንዲሁም ሌሎች ቁም ነገር አዘል ፕሮግራሞች የሚቀርቡበት ፌስቲቫል በእንጦጦ ፓርክ ማዕከል ሊካሄድ መሆኑን ጳጉሜን አብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታውቋል፡፡
ከጳጉሜን 1 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በእንጦጦ ፓርክ የሚካሄደው ፌስቲቫል ‹‹ጳጉሜን የአፍሪካዊያን ወርቃማ ወር›› በሚል መሪ ቃል የሚደረግ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል፡፡
የጳጉሜን አብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይላብ መሬሳ እንደገለጹት፣ በእንጦጦ ፓርክ ለአምስት ቀናት በሚካሄደው ፌስቲቫል ላይ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርስ የሚተዋወቁበት ይሆናል፡፡
ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው ፌስቲቫል አዲስ አበባ የሚገኙ አፍሪካውያንና ዓለም አቀፍ የማኅበረሰብ ክፍሎች የኢትዮጵያን የአየር ንብረት፣ ቋንቋና ባህል፣ ሃይማኖት፣ የተፈጥሮ ሀብትና ታሪካዊ ይዘቶች የሚመለከቱበት እንደሚሆን አቶ ኃይላብ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጳጉሜን ወር ፌስቲቫል በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የሚከበር እንደሆነና ትልቅ የሆነ ታሪካዊ ዳራ ያለው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ደስታ ሎሬንሶ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ጳጉሜን አብዛኛውን ጊዜ የሚያከብሩት ሕፃናት ልጆች መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ በተለይም በደቡብ አካባቢ የሚገኙ ‹‹ቃቆ›› አሳድጊን በማለት ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት በደስታ የሚቦርቁበት ነው ብለዋል፡፡
ጳጉሜን የኢትዮጵያውያን ልዩ ወር መሆኑን፣ ወሩም በፌስቲቫል ሲከበር ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን የሚተዋወቁበት እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት የሚያገኝበት እንደሆነ ደስታ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በየትኛውም ዓለም ላይ የሌለች የጳጉሜን ወር ያላት አገር መሆኗን ያስታወሱት ኃላፊው፣ ይኼንን ወር ታሳቢ በማድረግና የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያን ባህላዊ ትሩፋት ጠብቀው ሕፃናት ልጆች እንዲያድጉና ያላቸውን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ፌስቲቫሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሎሬት ስለሺ አበራ (ጋሽ አበራ ሞላ) ተናግረዋል፡፡
ለአምስት ቀናት የሚካሄደው ፌስቲቫል ላይ በርካታ ፕሮግራሞች የሚካሄዱ መሆኑንና እያንዳንዱ ቀንም ለየት ያሉ ይዘቶች ይኖራቸዋል ሲሉ ሎሬት ስለሺ ተናግረዋል፡፡
ለአምስት ቀናት በሚካሄደው ፌስቲቫል ጳጉሜን 1 የሰላምና የፍቅር ቀን፣ ጳጉሜን 2 የባህልና የአፍሪካ ቀን፣ ጳጉሜን 3 የአፍሪካ ልጆች ክብረ በዓልና የዝናብ ላይ ሩጫ ቀን፣ ጳጉሜን 4 እንነግድ፣ ጳጉሜን 5 የጳጉሜን ውቦች በሚል እንደሚከበሩ ተገልጿል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ሁነቶች ታስበው እንደሚውሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
መንግሥት የ2015 ዘመን መቀበያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለሚያከናውናቸው ተግባራት አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ሁነቶች ታስበው እንደሚውሉ፣ ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. የተፈጥሮ አደጋዎችን፣ ጦርነትንና ሌሎች ችግሮችን ብታይም በብዙ ስኬቶች የታጀበች አስታውሷል፡፡
ጳጉሜን 1 የበጎ ቀን፣ ጳጉሜን 2 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን፣ ጳጉሜን 4 የአገልጋይነት ቀንና ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን ሆነው ታስበው እንደሚውሉ ቢሮው አስታውቋል፡፡