Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአቅርቦቱና ፍላጎቱ ያልተመጣጠነው የትራንስፖርት አገልግሎት

አቅርቦቱና ፍላጎቱ ያልተመጣጠነው የትራንስፖርት አገልግሎት

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በአገልግሎት ዘርፍ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ውስጥ የትራንስፖርት አቅርቦት ከቀዳሚዎቹ ይመደባል፡፡ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ተገልጋዮችን የሚፈትን ቢሆንም፣ ችግሩ ቀኑን ሙሉ የሚታይ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡

በየትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መነሻና መድረሻ ሥፍራዎች ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ተሠልፈው ማየቱም የተለመደ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን ወደ ዘርፉ ያስገባ ቢሆንም፣ ዛሬም በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ አልተቻለም፡፡

ይህም ተገልጋዮች ከሚገባው ታሪፍ በላይ ከፍለው እንዲጓጓዙና ከፍላጎታቸው እንዲስተጓጎሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ አንበሳ አውቶቡስ፣ ሸገር ባስ፣ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች፣ ታክሲ፣ ሃይገር፣ በከተማዋ ዳርቻ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮም በየጊዜው ችግሮችን ያቃልላሉ የተባሉ አሠራሮችን የዘረጋ ቢሆንም፣ የተገልጋዮች ለሰዓታት ትራንስፖርት የመጠበቅ ችግርን አልፈታም፡፡

በአንድ ድርጅት ውስጥ በገንዘብ ሰብሳቢነት እንደምትሠራ የነገረችን ወጣት፣ ችግሩ ጠዋትና ማታ የባሰ ይመስላል እንጂ፣ ሙሉ ቀን እንዳለ ገልጻለች፡፡

የሥራዋ ባህሪ ሆኖ በአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫዎች ስትዘዋወር እንደምትውል፣ በዚህም በብዙ ሥራፍዎች የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግርና የተገልጋይ እንግልት እንደታዘበች ራሷን ምሳሌ አድርጋ ነግራናለች፡፡

በተለይ ሚኒባስ ታክሲዎች ረዥም መንገድ ካልሆነ አጭር መንገድ መሥራት እንደማይፈልጉ፣ ዋጋውንም መንግሥት ካወጣው ታሪፍ በእጥፍ እንደሚያስከፍሉ፣ አጫጭር መንገድ የሚሠሩ ላዳና ራይዶች ደግሞ በግለሰብ ከ30 ብር እስከ 50 ብር፣ እያስከፈሉ እንደሚጭኑ ገልጻለች፡፡

ለአብነትም ከዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ቦሌ ድረስ ሚኒባስ ታክሲዎች በግለሰብ ሰባት ብር የሚጭኑ ሲሆን፣ ላዳ ደግሞ በግለሰብ 30 ብር እንደሚጭኑ አስታውሳለች፡፡

ከ22 ማዞሪያ (ጎላጉል) ቦሌ በግለሰብ በላዳ 50 ብር እንደሆነ፣ ከ22 ማዞሪያ እስከ ሲኤምሲ ሃያት አደባባይ በሚኒባስ 25 ብር እንደሚያስከፍሉ፣ ነገር ግን ሃያት በመጥራት ፋንታ ጣፎ ጠርተው በጣፎ ሒሳብ 30 ብር እንደሚጠይቁ፣ ተሳፋሪ ቀድሞ ሳህሊተምሕረት ወይም መገናኛ ቢወርድ እንኳን ሙሉ ታሪፉን 30 ብር እንደሚከፍል፣ ይህንን ያመጣው በዘርፉ ላይ ያለው የትራንስፖርት እጥረት እንደሆነ አክላለች፡፡

ከሥራ ወደ ቤት ለመሄድ ከመነሻ ሥፍራ ረዥም ሰዓት ተሠልፋ እንደምትሄድ፣ ጠዋት ግን ሥራ እንዳይረፍድ በተገኘው ትራንስፖርት የተጠየቀችውን ከፍላ እንደምትሳፈርም ነግራናለች፡፡

ድጋፍ ሰጪና ሌሎች መንግሥት የሚያቀርባቸው የትራንስፖርት አገልግሎቶች በአብዛኛው የሚገኙት ከመነሻ ቦታዎች እንደሆነ፣ የከተማ አውቶቡሶች ደግሞ ሰው በሚንቀሳቀስበትና በሚፈልግበት ሰዓት ሁሉ እንደማይገኙ፣ ይህም የትራንስፖርት ተጠቃሚው ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እንዲዳርግ ማድረጉን አክላለች፡፡

‹‹መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የሚያደርጋቸው መፍትሔዎች ከእኛ ከትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ጋር የተመጣጠኑ አይመስለኝም፤›› ብላለች፡፡

የመንገድ መተሳሰርም ሌላው ችግር እንደሆነ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በሰዓቱ እንዳይደርሱ እያደናቀፈ መሆኑን መታዘቧንም ነግራናለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ፍሰት ለማሳለጥና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱ ዘመናዊነትን የተላበሰና ለማኅበረሰቡ ምቹ ለማድረግ ቢሮው የአሥር ዓመታት ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ለረዥም ዓመታት በችግር ውስጥ ተዘፍቆ የቆየውን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቀላጠፍና ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ገልጸዋል፡፡

ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት 15 የሚሆኑ የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መስመሮች መለየታቸውን፣ በተለይም የትራንስፖርት ዕቅድና የመሬት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለና ችግሩን ለመቅረፍ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ስትራቴጂ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ስትራቴጂ የሥምሪት አስተዳደርን፣ የመኪና ማቆሚያን፣ የትራፊክ ደኅንነት ክፍተትን፣ ለመንገድ ደኅንነትና ተያያዥ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከ500 ያላነሱ አውቶቡሶች ተገዝተው ወደ ሥምሪት እንዲገቡ ተደርጓል ያሉት አቶ ምትኩ፣ እነዚህም አውቶቡሶች ምልልሳቸውን በማፋጠን ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ አምስት ኮሪደሮች ላይ የአውቶቡሶችን ምልልስ ለማፋጠን አውቶቡሶች ብቻ የሚጓጓዙበት መንገድ መዘርጋቱን፣ በዚህም ሰፊ የሆነ ለውጥ መምጣቱን አክለዋል፡፡

የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍ ቢሮው በቅርቡ 110 አውቶቡሶችን ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቅሰው፣ ይህም የማኅበረሰቡን የትራንስፖርት እንግልት በተወሰነ መልኩ ሊቀርፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡና የማኅበረሰቡ ፍላጎት አለመመጣጠኑን ያነሱት አቶ ምትኩ፣ በከተማዋ የቀን የትራንስፖርት የጉዞ ምልልስ 2.8 ሚሊዮን መሆኑንና የማኅበረሰቡ ፍላጎት መጠን ከ4.2 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በከተማዋ እየታየ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የግል ባለሀብቱ ትልቅ ሚና እንዳለውና ይህንን ታሳቢ በማድረግ ባለሀብቱ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በመግባት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ስትራቴጂው በ2013 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን፣ እስከ 2022 ዓ.ም. ይቆያል፡፡ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን፣ ዘርፉንም በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመናዊ ለማድረግ የትራንስፖርት ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም የተሰኘ ፕሮጀክት መኖሩን፣ ለፕሮጀክቱም 197 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መበጀቱን አብራርተዋል፡፡

በትራንስፖርትና ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በሚነሱ ችግሮች የተነሳ የትራንስፖርት ዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት መኖሩን የቢሮው የአቅም ግንባታ ባለሙያ አቶ አላቸው ሥዩም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...