ከ30 በላይ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ‹‹አስቸኳይ የሰላም ጥሪ›› በሚል ዛሬ ጷግሜ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ካሳንቺስ በሚገኘው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ያዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ በ‹‹ፀጥታ›› ኃይሎች ተከለከለ።
ረፋድ 3:30 ሰዓት ላይ ሊካሄድ የነበረው መግለጫ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የሰላም ጥሪ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀው ነበር።
የመግለጫውን ጥሪ ያስተላለፈው የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ሲሆን ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር፣ ሴታዊትና ሌሎችም አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተሳተፉበት ነው።
ይሁንና ‹‹የፀጥታ ኃይል›› የሆኑ ግለሰቦች መግለጫው እንዳይካሄድ መከልከላቸውን 4:00 ሰዓት አከባቢ አዘጋጆቹ በሆቴሉ ለተገኙ ጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንደሆኑ የገለጹ ግለሰቦች ጠዋት 1:00 ሰዓት አከባቢ ‹‹መግለጫው ፈቃድ የሌለው በመሆኑ በሆቴሉ ማካሄድ እንደማይቻል›› ለሆቴሉ አመራሮች መግለጻቸውን ሪፖርተር ከአዘጋጆቹ ተሰምቷል።
የፀጥታ ኃይል እንደሆነ የገለጸ አንድ ግለሰብ ከአዘጋጆቹ ሲያነጋግር የነበረ ጋዜጠኛን ስምና ስልክ ቁጥር ሲመዘግብ ነበር። አዘጋጆቹ በቀጣይ ምንም ለማድረግ እንዳልወሰኑ አስታውቀው፣ በቀጣይ ተወያይተው እንደሚያሳውቁ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።