Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዓላት የዋጋ ግሽበትን ስለሚያባብሱ ቁጥጥር እንዲደረግ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓላት የዋጋ ግሽበት ከሚባባስባቸው ወቅቶች ዋናዎቹ በመሆናቸው፣ መንግሥት የግብይት ሰንሰለቶቹን ከማሳጠር አንስቶ የገበያ ቁጥጥር እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡

የዋጋ ግሽበት ብዙ ጊዜ ከሚባባስባቸው አንዱና ዋናው ምክንያት በዓላት መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸው፣ በዓላትን ተከትለው የሚመጡ የዋጋ ጭማሪዎች በተለይም የምግብ ዋጋ ግሽበትን ከፍ እንደሚያደርጉት አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አረጋ ሹመታ (ዶ/ር)፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በዓላትን ተከትሎ የሸማቾች ሸቀጦችን የመግዛት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ስለሚረዳ ምርቶችን በመደበቅና በመቀነስ ሰው ሠራሽ እጥረት ሊፈጥር ስለሚችል፣ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በግልጽና በቁርጠኝነት ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት በበዓላት ወቅት የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር የሚችልባቸው ሁኔታዎች ላይ፣ በተለይም የኅብረት ሥራ ማኅበራትን አቅም በማጎልበት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅማቸው ጎልብቶ ምርቶችን ከአምራች ወደ ተጠቃሚው በአጭር የግብይት ሰንሰለት ማድረስ ይገባቸዋል ሲሉ አረጋ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

እንደ የኢኮኖሚ ተመራማሪው፣ ዓበይት የኢኮኖሚ ችግሮች ከሚባሉት አንደኛው የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ ሁለተኛው የሥራ አጥነት ቁጥር መጨመር ሲሆን፣ ያልተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ ደግሞ ሦስተኛው ነው፡፡ አራተኛ የሆነውን የገንዘብ ምጣኔ መቀነስ ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች አበይት የአንድ አገር የኢኮኖሚ ችግሮች እንደሚባሉ አክለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት ለሁሉም አገሮች ችግር ቢሆንም በአገር ደረጃ የትኛውን ዓይነት የዋጋ ግሽበት ነው እያስተናገድን ያለነው የሚለውን በደንብ ማየት አስፈላጊ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያው ገልጸው፣ ‹‹ይህም የፖሊሲ ዕርምጃዎችን የሚለይ ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በአንድ አገር የሚወሰደው የፖሊሲ ዕርምጃ እንደ አገሮቹ የዋጋ ግሽበት ዓይነት የሚለይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያጋጠማት ያለችው ምግብ ነክ በሆኑ ግብዓቶች መሆኑን ያስረዱት የኢኮኖሚ ተመራማሪው፣ ምግብ ነክ ሰብሎችን ከአንድ ጊዜ በላይ በማምረት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊያመጣ የሚችለውን ምርት ለገበያ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተግባር ዕውን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት ለግብርናውና ኢንዱስትሪው የሚሰጠው ትኩረት ከሌሎች ክፍለ ኢኮኖሚዎች የበለጠ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን ለረዥም ዓመት እየመራው ያለው የኢንዴክስ ክፍል  የምግብ ዋጋ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህም ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የጥራጥሬና የዳቦ እህሎች የሚባሉት ናቸው፡፡ ከዚህም በመነሳት የግብርናው ዘርፍ ማምረት ያለበትን ያህል እንዲያመርት በርካታ ሥራዎች አለመከናወናቸውን የሚያሳይ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

በየወሩ ይፋ የሚደረገው የሸማቾች ዋጋ ኢንዴክስ ላይ የሚመዘገበው የምግብ ዋጋ ግሽበት አኃዝ፣ በተለይም በዚህ ወቅት በገበያ ሥፍራዎች ላይ ያለውን ዋጋ ያንፀባረቀ አይደለም የሚል አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ለዕለት ፍጆታ የማይጠቀማቸው ምርቶች ዋጋ ከምግብ ዋጋ ጋር ተደምሮ ሲገለጽ ሥሌቱ ትክክል አይደለም ይገባል ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሐሳብ አንድ ቢሆንም፣ የተለያዩ ምክንያቶች ከጀርባ እንደሚኖሩት ይታወቃል ይላሉ፡፡ ውስጣዊ ግጭት፣ አለመረጋጋት፣ የምርት እጥረት፣ የግብዓት ዋጋ መናርና የግብይት ችግር፣ እንዲሁም የመንግሥት የፊሲካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ በትክክል አለመሥራት ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትክክለኛ ምክንያቶችን አጥንቶ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዕርምጃዎች ሊወስድ ይገባል ሲሉ አረጋ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች