Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር ጠየቁ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር ጠየቁ

ቀን:

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች እንደገና ያገረሸው ጦርነትና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ ቆመው፣ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር 35 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጠየቁ፡፡

የግጭቶቹ ተሳታፊ አካላትን በሙሉ ያካተቱ የእርቅ ንግግሮች መጀመር አለባቸው ሲሉ የገለጹት ድርጅቶቹ፣ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ካልተፈቱ፣ አገሪቱ መውጣት የማትችልበት ቀውስ ውስጥ ትገባለች ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቁጥራቸው 35 የሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም በጋራ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ሊሰጡ የነበረው መግለጫ በፀጥታ ኃይሎች በመከልከሉ በበይነ መረብ በሰጡት ‹‹የሰላም ጥሪ›› ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ የሰላም ጥያቄ የሚነሳው ችግር በተፈጠረበት ወቅት በመሆኑ እንደገና የተጀመረው ጦርነት በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትልባቸዋል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ድርጅቶቹ ‹‹የዕርቅ ንግግሮች›› በማለት የገለጹት የሰላም አካሄድ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሊደረግ የታቀደው ድርድር? ወይስ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት ሊካሄድ የታሰበው ብሔራዊ ውይይት? የሚሉ አማራጮች ተለይተው አለመቅረባቸውን፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አመሐ መኮንን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የዕርቅ ሒደቱ በየትኛው አካሄድ መሄድ አለበት የሚለውን ለመመለስ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ እኛ የገለጽነው በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ጦርነት የአገር ሀብትና ዜጎችን ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ በአስቸኳይ ወደ ሰላም መገባት አለባቸው፤›› የሚል መሆኑን አቶ አመሐ ገልጸዋል፡፡

ጦርነቱ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ የሰላም አማራጮችን ሲያቀርቡ እንደቆዩ የገለጹት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ፣ በማንኛውም የዕርቀ ሰላም ንግግር ሒደቶች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሰላም ድርድር ለመካሄድ በሒደት ላይ እያለና በጦርነቱ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ከጉዳታቸው ባላገገሙበት ሁኔታ፣ እንደና ጦርነት መከሰቱ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ድርጅቶቹ በትግራይና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩና ዕርዳታ ያለ እንቅፋት እንዲደርስ፣ ፆታዊ ጥቃት የፈጸሙ ተዋጊ አካላትን ጨምሮ ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ያደረሱ አካላት ላይ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ የተጠያቂነት ዕርምጃ እንዲወሰድ፣  በግጭቶቹ ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ፈጣን የሕክምናና የማኅበረ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ በተጨማሪም በግጭቶች ተሳታፊ ያልሆኑ ንፁኃን ተጋላጮች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የጥበቃ ከለላ እንዲደረግላቸው ድርጅቶቹ ጠይቀዋል፡፡

ተጠያቂነትን ለማስፈን በተለያዩ አካላት እስካሁን ድረስ ከተገኙት ምርመራዎች በተጨማሪ በገለልተኛ ተቋማት ምርመራ እንዲደረግ፣ የጥቃቱ ፈጻሚዎችም ተለይተው ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፍልግ አቶ አመሐ አሳስበዋል፡፡

‹‹በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ የሚሆኑትን ለመለየት በመጀመሪያ ግጭት መቆም አለበት፡፡ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ ምናልባት የሽግግር ፍትሕ የሚያስፈልግ ከሆነ የሚያስፈልግውን ዕርምጃ ለመውሰድ ይረዳል፤›› ሲሉ አቶ አመሐ ገልጸዋል፡፡

ብሔር ተኮር ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ እንዲሁም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በቁጥር አነስተኛ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች (minorities) የልዩ ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ ተፋላሚ አካላትና ደጋፊዎቻቸው ከማንኛውም የጦርነት ፕሮፓጋንዳና ግጭት አባባሽ ንግግሮች እንዲሁም ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ኃይሎችና አክቲቪስቶች ድምፃቸውን ለሰላምና ለዕርቅ ብቻ እንዲያውሉ ድርጅቶቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአጠቃላይ 35 የሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ‹‹አስቸኳይ የሰላም ጥሪ›› በሚል ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም ከረፋዱ 3፡30 ላይ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ሊሰጡ ያቀዱት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በፀጥታ ኃይሎች ተከልክሎ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ማንነታቸውን ያልገለጹ ነገር ግን የመንግሥት አካል ነን ባሉ ግለሰቦች ምክንያቱ ባልታወቀበት ሁኔታ መግለጫው መከልከሉን የገለጹት ድርጅቶቹ፣ ለመንግሥት የፀጥታ አካላት ቅድሚያ ማሳወቅ የሚያስፈልገው የአደባባይ ሠልፎችን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አሠራር የሕግ የበላይነትን የሚፃረር ከመሆኑም ባሻገር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ሊጫወቱ የሚገባቸውን ድርሻ የሚነፍግ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...