Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:

  • የአማራ ክልል ታጣቂዎች ከክልሉ ተሻግረው ጥቃት ስለመፈጸማቸው እርግጠኛ አለመሆኑን ተናግሯል

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ፣ ታጣቂዎች ለሁለት ቀናት በፈጸሟቸው ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለው ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በፈጸሟቸው ጥቃቶች የተነሳ ከ20 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ ተፈናቃዮዎቹ ያሉበት ሁኔታ ‹‹በከፍተኛ ደረጃ›› የሚያሳስብ መሆኑን ትናንት ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

የኢሰመኮ ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ለሁለት ቀናት የዘለቀው ጥቃት አገምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙና ጀቦ ዶባንን ጨምሮ ኡሙሩ ወረዳ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ የተፈጸመ ነው፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች የተገደሉት ‹‹የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ›› ነዋሪዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ የጥቃቱ መነሻ የሆነው በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች የኡሙሩ ዋና ከተማ የሆነችውን ኦቦራን ለመያዝ ጥረት እንዳደረጉና በዚህም እንቅስቃሴ ሦስት ‹‹የአማራ ተወላጆች›› መገደላቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ኢሰመኮ በሪፖርቱ፣ ‹‹ከኡሙሩ ወረዳ፣ ሀሮ አዲስ ዓለም ከተባለ ቀበሌና አጎራባች ከሚገኘው የአማራ ክልል፣ ቡሬ ወረዳ የተውጣጡ ታጣቂዎች በኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ነዋሪዎች ላይ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽመዋል፤›› ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ፣ በሁለቱ ቀናት ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች ስለመገደላቸውና ከ70 በላይ የሚሆኑት ስለ መቁሰላቸው እንዲሁም የነዋሪዎች የቤት ንብረቶችና የቀንድ ከብቶች ስለመዘረፉ ከአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች እንደተረዳ አስታውቋል፡፡

‹‹በጥቃቱ ምክንያትም ከ20 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በኦቦራ ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፤›› ያለው ሪፖርቱ፣ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቀበሌዎች መካከል አሁንም ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ስለመኖራቸው መረዳቱን በሪፖርቱ ላይ አካቷል፡፡

ኢሰመኮ ያሰባሰበው መረጃ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በሚገኙት ጃርደጋ ጃርቴ፣ ኪረሙና በአቤ ዶንጎሮ ወረዳዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊፈጸሙ ይችላል የሚል ሥጋት ነዋሪዎች ላይ መፈጠሩን እንደተረዳ አስታውቋል፡፡

የኢሰመኮ የጂማ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በአካባቢው ላይ መሰማራታቸውን፣ ነገር ግን ‹‹ተመሳሳይ ጥቃት ሊደገም ይችላል›› የሚለው ሥጋት አሁንም እንዳልተቀረፈ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ከክልሉ አጎራባች ወረዳ የተሻገሩ ስለመሆናቸው መገለጹን አስተባብሏል፡፡

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እንግዳው ጠገነው፣ ጥቃቱ መፈጸሙን መስማታቸውን ገልጸው፣ ጥቃት አድራሾቹ ከቡሬ ስለመሻገራቸው ‹‹የመረጃው ምንጭ ምን ያህል ትክክል ነው የሚለው መታየት አለበት፤›› የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡

ኃላፊው፣ ይህንን አቋማቸው ሲያስረዱ፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዓባይን ተሻግሮ መሄድ የማይቻል መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር፣ ‹‹እኛ ባለን ክትትል ከቡሬ ወለጋ መስመሩ ዝግ ነው፣ ቦታው ላይ ያለው ፌደራል ፖሊስ ነው፣ በየት ተሻግሮ ነው ጥቃት ሊፈጸም የሚችለው?›› ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ሲያዘጋጅ የተጠቀማቸው የመረጃ ምንጮች ‹‹ትክክለኛነት መታየት እንዳለበት›› የተናገሩት አቶ እንግዳው፣ ‹‹የተሰጠው መግለጫ ትክክለኛ ነው? አይደለም? የሚለው በሚገባ ታይቶ ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ መረጃው ትክክል ከሆነ ‹‹የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ›› ሥራ የክልሉ ቀጣይ አጀንዳ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ከክልሉ ስለተነሳው ሐሳብ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢሰመኮ የጂማ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ፣ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ሲያዘጋጅ የክልሉ ኃላፊዎችን ባለማነጋገሩ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው የጥቃቱን ተጎጂዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የአይን እማኞችና የአካባቢው ባለሥልጣናት በማነጋገር መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እንደዚያ ስለተባለ ብቻ ያወጣነው ሪፖርት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት ከተለያዩ አካላት ጋር በተገኙ መረጃዎች ላይ የወጣ የመጀመሪያ ሪፖርት እንደሆነና የፀጥታ ሁኔታው እንደፈቀደ ኮሚሽኑ በቦታው ተገኝቶ ሙሉ ምርመራ እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ በጥቃቱ ላይ የሚያደርገውን ክትትል እንደሚቀጥል መናገራቸው በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይም ተጠቅሷል፡፡

ኮሚሽነሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የፀጥታ ሥጋት ካለባቸው አካባቢዎች ወደ ሌላ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅት የነዋሪዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የንብረት መብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ተገቢ የሆኑ ጥንቃቄዎች መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ኢሰመኮ በአስቸኳይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ተሰማርተው ነዋሪዎችን ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ወደ ተረጋጋ ሕይወት እንዲመልሱ ጠይቋል፡፡ በንፁኃን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተም ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠራ አሳስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...