Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሥር ዓመቱ አገራዊ የልማት ዕቅድ እንዲከለስ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ጥሪ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተሰናድቶ ትግበራው የተጀመረው  የአሥር ዓመቱ አገራዊ የልማት ዕቅድ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ እንዲከለስ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ከመጣ በኋላ የተዘጋጀው የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ የውስጥ አቅም መጠቀም ላይ ማተኮሩ መልካም ቢሆንም፣ ነገር ግን ዕቅዱ ሲዘጋጅ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮችና በዚህ ወቅት በተግባር ያለው የተለያየ መሆኑን አሶሴሽኑ አስታውቋል፡፡  

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ነሐሴ 27 እና 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት ያደረገውን የፖሊሲ ውይይት ፎረም መጠናቀቅ አስመልክቶ በተሰጠ መግለጫ ላይ፣ አገሪቱ የልማት ዕቅዱን በምትነድፍበት ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ እንዲሁም ከተጀመረ መንፈቅ የሞላው የዩክሬይንና የሩሲያ ጦርነት አልነበሩም ተብሏል፡፡

የልማት ዕቅዱ ሲነደፍ ይሳካሉ ተብለው የተቀመጡ ጉዳዮች አሁን ባለው ሁኔታ ማሳካት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል፣ አሶሴሽኑን በመወከል ገለጻ ያደረጉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ‹‹የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ክለሳ ያስፈልገዋል›› የሚል እምነት እንዳለው የተናገሩት መንግሥቱ (ፕሮፌሰር)፣ ለዚህም ምክንያቱ በተለይም አገሪቱ በዚህ ወቅት ያለችበት የውስጥ ግጭት ካልቆመ፣ በልማት ዕቅዱ ትግበራ ላይ ታሳቢ የነበረው አቅምና ገንዘብ ወደ ጦርነቱና ከዚያ ለማገገም ተግባር ከመዋሉ ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ምክንያት የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት ስለሚከብድ ክለሳ ይፈልጋል የሚል ሐሳብ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ ያለችበት የውስጥ ግጭት በአጭር ጊዜ መቆም እንደሚገባው በአሶሴሽኑ መግለጫ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ሲሆን በቀጣይ የሚኖረው ተግባር ከግጭት ማገገምና የመልሶ ማልማት ሥራ በመሆኑ፣ አገሪቱ ከጉዳት መውጣት ብቻ ሳይሆን የጦርነት አካባቢዎችን ወደ ቀደመ ሰላማቸው ለመመለስ በራሱ የሚጠይቀው አቅም ታሳቢ ሊደረግ ይገባል ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም መንግሥት በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥጋቶችን ተቋቁሞ ግቡን ለማሳካት እንዲረዳው የዕቅድ ክለሳ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚል ሐሳብ ሲንሸራሸር ቢቆይም፣ ‹‹የአሥር ዓመቱ ዕቅድ ክለሳ አይደረግበትም፣ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ የሦስት ዓመት ዕቅድ እየተዘጋጀ በመሆኑ ፓርላማ ባፀደቀው ሕግ ላይ ክለሳ አይደረግም፤›› ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የምርምርና የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፣ ቀደም ሲል የፕላንና ልማት ሚኒስቴር  የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱን ክለሳ ለማድረግ፣ ከተለያዩ ባለሙያዎች አስተያየትና ግብዓት ወስዷል የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡

የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ይከለሳል ተብሎ ቢገለጽም እስካሁን ድረስ አለመከለሱን፣ ነገር ግን የሦስት ዓመት የተከለሰ ዕቅድ እየተዘጋጀ ነው የሚል መረጃ መሰማቱን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም (ዶ/ር) ከሰሞኑ እንዳስታወቁት፣ የአሥር ዓመቱ ዕቅድ ሲታቀድ ታሳቢ ያልነበሩት ጉዳዮች ማለትም የኮቪድ-19 ወረርሽን መከሰት፣ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ይሳካል ተብሎ ከታሳበው ዕቅድ (ግብ) ያነሰ ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የ2015 የበጀት ዓመትን ጨምሮ ያለፉት ሁለት ዓመታት የዕቅዱ ክፍል በየዓመቱ በተቀረፀ ዕቅድ እንደሚተገበር ያስረዱት ሚኒስትሯ፣ ነገር ግን ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም. የሚተገበር የአሥር ዓመት ዕቅዱ ዝርዝር መተግበሪያ ፕሮግራሞች የያዘ ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም በዝግጅት ላይ ይገኛል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በዝግጅት ላይ ያለው የሦስት ዓመት ዕቀድ ያለፉትን ሶስት ዓመታት አፈጻጸም ታሳቢ ያደርጋል የተባለ ሲሆን፣ ይህም ከተቀመጡት ግቦች የትኞቹ እንደተሳኩና እንዳልተሳኩ ተመልክቶ፣ ባልተሳኩት ላይ ግቡ ይከለስ ወይስ አቅም ይጨመርበት የሚለው የሚታይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

‹‹የመንግሥት የኢንቨስትመንት ዕቅድ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው በመጋቢትና በሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ተጠናቆ እንደሚወጣ የሚጠበቀው ዕቅድ፣ አንዳንዶቹን ግቦች ሊከልስ እንደሚችል የተመላከተ ሲሆን፣ ጥናቱም በዚህ ወቅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ፍፁም (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች