በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ብልጫ ለሚያገኙ ዕውቅና የሚሰጥበት የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባህልና ቴአትር አዳራሽ ለአራተኛ ጊዜ ተካሂዷል።
‹‹ለጥበብ ዳበራ! ለዕውቀት ጎታ!’›› በተሰኘ መሪ ቃል የተዘጋጀው ዓመታዊው የሥነ ጽሑፍ ሽልማት በ2011 ዓ.ም. ለሕትመት ከበቁ መጻሕፍት መካከል ብልጫ ያገኙት በልቦለድ፣ በአጭር ልቦለድ፣ በግጥም፣ በልጆች መጽሐፍ፣ በግለ ታሪክ፣ በምርምር ዘርፍ የተዘጋጁ ይገኙበታል፡፡ በሥነጽሑፍ የሕይወት ዘመን ባለውለታ የሕይወት ዘመን ተሸላሚና ሦስት ለሥነ ጽሑፍ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ተቋማትም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በማኅበራዊ ዲጂታል ሚዲያ መጻሕፍትን ለአንባቢያን በማዳረስ፣ ሥነ-ጽሑፍን ለማኅበራዊ ግልጋሎት በማዋልና ለአካል ጉዳተኞች አካታች ፕሮግራም በማካሄድ ላቅ ያለ ተግባር የፈጸሙም ተሸልመዋል፡፡