Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነትና ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሻገር የቆመችው ‹‹ትምራን››

‹‹ትምራን›› በሴት ስም የምትጠራ የሲቪል ማኅበር ስትሆን የተቋቋመችውም በመጋቢት 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ የተቋቋመችውም ኢትዮጵያውያን ሴቶች በፖለቲካና በሕዝብ አስተዳደር መስክ ፍትሐዊ ውክልናና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ብሎም የአመራር ሰጪነት ሚና እንዲኖራቸው የማስቻል፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት የማስፈንና የሴቶችን መብት የማረጋገጥ ሥራን ለማከናወን ነው፡፡ ይህም ትምራን በኢትዮጵያ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግን ዋነኛ ትኩረት አድርጋ የተቋቋመች ብቸኛ የሲቪል ማኅበር ያደርጋታል የሚሉት ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ሰሎሞን ናቸው፡፡ ትምራን ከተቋቋመችበትም ማግስት ጀምሮ ለተቋማዊ አደረጃጀት መጠናከር ቅድሚያ በመስጠት የተቋሟን የሰው ኃይል ቁጥር ማጠናከር፣ የፋይናንስና የሰው ኃይል አስተዳደር መመርያ ማዘጋጀት፣ ከተለያዩ የሲቪል ማኅበራትና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አሠራርን መዘርጋት፣ ሥልታዊ ግንኙነቶችን መፍጠር፣ እንዲሁም ሀብት የማሰባሰብ ሥራዎችን አከናውናለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተቋሟን ገጽታ ለማሳየትና መረጃ ለመስጠት የሚያስችል ድረ ገጽና የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገጽን ለመገንባት ችላለች፡፡ ስለየትምራን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሥራ አስኪያጇን ወ/ሮ ኢየሩሳሌምን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ትምራን ከተቋቋመች ከሁለት ዓመት በላይ ቢሆናትም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወነቻቸውን ተግባራት ሊያስረዱን ይችላሉ?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ በትምራን አዘጋጅነት ተካሂዲል፡፡ እንዲሁም በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባው ተሳትፎና ሊገጥሟቸው ስለሚችሉት መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በሰፊው ውይይት ተደርጓል፡፡ በምርጫውም ሒደት በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በወረዳ አምስትና ሦስት አባላቷ በምርጫ ታዛቢነት ተገኝተዋል፡፡ ትምራን ከኖርዌይ የክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር በመተባበር ለፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ተወዳዳሪዎችና አባላት የሥልጠና መድረክ አዘጋጅታለች፡፡ ሥልጠናዎቹ በሁለት ዙር የተካሄዱት በባህር ዳርና በሐዋሳ ከተሞች ሲሆን በአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ላይ የተሳተፉት አዲስ የፓርቲ ዕጩዎችና በፖለቲካ ሕይወት የዳበረ ልምድ ያላቸው ሠልጣኞች ነበሩ፡፡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ያተኮረው በዋናነት በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል ከመራጮች ምዝገባ ጋር ተያይዞ በተነሳው ቅሬታ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው ገለልተኛ የአጣሪ ቡድን ውስጥ ትምራን አባል በመሆን የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ትምራን ሴቶች በፖለቲካና በማንኛውም ሕዝባዊ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ውሳኔ ሰጪ የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት ራዕይ አድርጋ የተቋቋመች የሲቪል ማኅበር ስትሆን፣ ራዕይና ተልዕኮዋን ለማሳካት ሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ ከተግባራቱም መካከል አንደኛው ሴቶችን ማነቃቃት፣ ግንዛቤ መፍጠርና ማብቃት ነው፡፡ ይህም ሁለት አንጓዎች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል የሴቶችን ጥያቄዎች ለሚወክሉና ፍላጎታቸውን ለሚያሳኩ ድምፃቸውን እንዲሰጡ ማንቃት ነው፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ ሴቶች ራሳቸው ተመራጮች ሆነው እንደቀረቡ ማበረታታትና ተገብውን ድጋፍ መስጠት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ወንዶች ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ ማድረግና ተፅዕኖ መፍጠር ነው፡፡ በወንዶች ዙሪያ የሚካሄደው ቅስቀሳ ለሴት ፖለቲከኞች ድምፃቸውን በመስጠት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ የሚያደርግ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ሴቶችን በዕጩ ተወዳዳሪነት በመመልመልና የፓርቲ ቁልፍ የአመራር ቦታዎችን እንዲይዙ በማመቻቸት ረገድ ተግባራዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ያሉባቸውን ጫናዎች ሁሉ ተቋቁመው ወደ ውሳኔ ሰጪነትና ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲመጡ ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ ኃላፊነት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሴቶች በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ምን ታስቧል?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- በሰላም ግንባታ ላይ ‹‹ሴቷ ሰላምን ትምራ›› የሚል ፕሮጀክት አዘጋጅተናል፡፡ ለፕሮጀክቱም ተግባራዊነት ከክልል እስከ ቀበሌ ደረጃ አስፈላጊው እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ የሴቶች አመራር ሰጪነት ቁጥር በበቂ ሁኔታ እንዲኖር ሁሉን አቀፍ ጥረት ይደረጋል፡፡ ሴቶች በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ውስጥ ትርጉም ባለው ሁኔታ ሊሳተፉ የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህ ጥረት ሴቶች ስለ ምክክሩ ማወቅ የሚያስችላቸውን ሥልጠና ለመስጠት ተዘጋጅተናል፡፡ ይህንና በአጠቃላይ ሴቶችን የማብቃት ሥራ ለማከናወን ፋይናንስ ማስፈለጉ ግድ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል አዘጋጅተን ለውጭ አጋር ለጋሽ ድርጅቶች አስገብተናል፡፡ በፕሮጀክቱ ዙሪያም ከተጠቀሱት ድርጅቶች ጋር ከስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ በተረፈ በሰላም ግንባታው ዙሪያ አዲስ አበባና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ላይ ውይይት አካሂደናል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችም በቅርቡ እናካሂዳለን፡፡ የዚህም እንቅስቃሴ ውጤት ሴቶች በሰላም ዙሪያ ምን ማካሄድ አለባቸው የሚል ስትራቴጂ በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትምራን ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጋር ያላት ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- ትምራን ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጥራለች፡፡ የጥምረቱም ሴክሬታሪያት ሆና ተመርጣለች፡፡ ጥምረቱም ሥራዎችን የሚያሳልጥበት አቅጣጫ ላይ ሰፋ ያለ የጋራ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ሰባት የሲቪል ማኅበራትን በአባልነት ያቀፉ ስቲሪንግ ኮማቴ ለማቋቋም ተችሏል፡፡ ኮሚቴውም ከአሥራ አንዱም የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጋር ተገናኝቶ በጋራ በሚከናወኑ ተግባራት ያተኮረ ውይይትና የሐሳብ መለዋወጥ አድርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ ብሔራዊ ኮሚሽኑም ብሔራዊ ምክክሩን አስመልክቶ ባዘጋጀው ‹‹የስትራቴጂክ ፕላን›› ላይ ስቴሪንግ ኮሚቴው ሐሳብና አስተያየት እንዲሰጥበት አድርጓል፡፡ በዚህ ሒደት ላይ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሐሳብ አስተያየታቸውን እንዲያክሉበት ተደርጓል፡፡ በተረፈ ስቲሪንግ ኮሚቴው ሐሳብና አስተያየቱን ያንፀባረቀው ስትራቴጂክ ፕላኑን ከሴቶች የነቃ ተሳትፎ አኳያ ከገመገመ በኋላ ነው፡፡ በተረፈ ትምራን ጥምረቱን በሴክሬታሪያት ደረጃ የምትመራው የሚከናወኑ ሥራዎችን በማዘጋጀት፣ ሀብት በማፈላለግ፣ ሥራዎች በጥምረቱ አባላት በጥራት እንዲከናወኑ በማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትምራን በሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያጋጠማት ችግር ይኖር ይሆን?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- ችግሩ ውስጣዊ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ትምራን ከተቋቋመች ገና ሁለት ዓመቷ ነው፣ በእግሯ ለመቆምና ብዙ ኃላፊነት ያለውን የጥምረቱን ሥራ ለማከናወን በሰው ኃይል ማነስና በበጀት እጥረት የተነሳ ትንሽ ይከብዳል፡፡ በተረፈ ይህ ነው የተባለ ሌላ ችግር አላጋጠማትም፡፡

ሪፖርተር፡- ሴቶች በፖለቲካና በሕዝብ አስተዳደር በሌሎችም እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፉ ጋሬጣ ሆኖ ባስቸገራቸው ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ጥናት አካሂዳችኋል?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- ሁሉም ሰው ሊያየው ከሚችለው በፖለቲካ ተሳትፎ ላይ የሴቶች ቁጥር በጣም አናሳ ነው፡፡ ሴቶች በብዛት እየተሳተፉ አይደለም፡፡ ‹‹ፖለቲካና እሳት በሩቁ›› እየተባለ ነው የምንሰማው፡፡ ይህም ሴቶች በአመራር ሰጪነት እንዲመጡ አላደፋፈራቸውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ደግሞ የሴቶች ሕይወት በተፈለገው መንገድ የተለወጠ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ በየቦታው በሴቶች ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች ብዙ ናቸው፡፡ ሴቶች በፖለቲካና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ያደረጉባቸው ተግዳሮቶችን ለማወቅ፣ ብሎም ለመለየትና በየደረጃው መፍትሔ ለማስቀመጥ በሚያስችል ላይ ያተኮረ ጥናት በብሔራዊ ደረጃ ለማጥናት ፍላጎቱና እምነቱ አለን፡፡ ሰሞኑን ከታዩት አስደንጋጭ ክስተቶች መካከል በአንዲት ሠራተኛ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሁለት ሕፃናትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱም አሳዛኝ ድርጊት የሚያሳየን ነገር ቢኖር ሴቶች ልጆቻቸውን አጠገባቸው አድርገው ሥራቸውን ሳይቸገሩ የሚሠሩበት ሁኔታ ቢመቻች እንዲህ ዓይነት ችግሮች ላይከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሴት ልጅ በቅታ ትልቅ ደረጃ ከደረሰች በኋላ ለልጆቿ ስትል ከፖለቲካም ሆነ ከኃላፊነት ቦታዎች ራሷን ልታገል ትችላለች፡፡ ምክንያቱም ቅድሚያ የምትሰጠው ለልጆቿ ስለሆነ፡፡ ከዚህ አኳያ ለልጆች ጥበቃ ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር እንደ አንድ ተግዳሮት ይታያል፡፡ ሌላው ደግሞ አዎንታዊ ዕርምጃ በአግባቡ ሥራ ላይ አለመዋሉ ሌላው ተግዳሮት ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሴቶች በትምህርታቸውና በሥራቸው ላይ የሚያጋጥሟቸው መሰናክሎችስ?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- ሴቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ከወንዶች ይልቅ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲም የሚገቡት የመግቢያ ነጥብ በመቀነስ ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ከገቡም በኋላ ሁልጊዜ የሚኖር ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የቲቶር አገልግሎት መስጠትና ሌሎችም አቅማቸውን ሊያጎለብት የሚያስችሉ ሥራዎች ሊከናወኑላቸው ግድ ይላል፡፡ በራስ የመተማመንን አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ የተዘረዘሩት ድጋፎች አለመኖር ሴቶች ወደኋላ እንዲቀሩና በፖለቲካው ፍሬ እንዳይሳተፉ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን እየሰፈነ ያለው የወንድ የበላይነት ነው፡፡ ወንድ በመንገድ ላይ ሲሄድ የሚያሳቅቀው ነገር የለም፡፡ ሴት ልጅ ግን ከቤቷ ወጥታ ሥራዋን ሠርታ ወይም ትምህርቷን ተምራ ወደ ቤቷ እስከምትደርስ ድረስ ብዙ መሰናክሎችን ታልፋለች፡፡ ይህም ማለት መንገድ ላይ ከሚያንጓጥጡት፣ ከስድቡና ለከፋ ወዘተ ሁሉ አልፋ ነው የምትንቀሳቀሰው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮቿ ሊያስተካክሉላትና ሊቀርፍላት የሚያስችሉ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ ወንዶች ሊተባበሩ ይገባል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የግንዛቤ ማጎልመሻ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ነጥብን አስመልክቶ ለሴቶች የሚሰጠውን አዎንታዊ ዕርምጃ (አፈርማቲቭ አክሽን) እንዴት ይገመግሙታል?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- አፈርማቲቭ አክሽን ማለት አቅም የላትም ማለት አይደለም፡፡ ግን ሴቷ ያለፈችበትን መሰናክል ወንዶች አያልፉበትም፡፡ ለተጠቀሱት ተቋማት መግቢያ ወንድ ሦስት ነጥብ፣ ሴቷ ደግሞ 2.8 ነጥብ ብታመጣ ልዩነት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሴቷ ዕድሉ ቢሰጣት ወይም ሁኔታዎች ቢመቻችላት ከሁለት ነጥብ ስምንት አልፋ አራት ነጥብ ልታመጣ የምትችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ አፋርማቲቭ አክሽን አቅም የላትም ማለት እንዳልሆነ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ይህንን ጉዳይ ዝርዝር አድርገው ቢያብራሩት?

ወ/ሮ ኢየሩሳሌም፡- ሴቶች የሚያልፉበትን መሰናክል ወንዶች ቢያልፉ ጥሩ ነበር፡፡ ችግሩንም እንዲገነዘቡት ያደርጋቸዋል፡፡ ከቤት አስተዳደጋችን ጀምሮ ያለውን እንቅስቃሴ ብናይ በሴቶች ልቦና ላይ ጫፍ የሚያሳድሩ በርካት ኋላቀር አባባሎች አሉ፡፡ ከአባባሎቹ መካከልም ‹‹ሴትና ድመት ወደ ማጀት፤ ሴት ብታውቅ በወንድ ይለቅ›› የሚሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ በባልና ሚስት መካከል ያለው ግንኙነት ሲታይ ደግሞ ሴት የተፈጥሮ ግዴታዎች እንዳሉበት ዕሙን ነው፡፡ ከግዴታዎቹም ውስጥ ልጅ መወለድ፣ የማጥባት ወዘተ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ሥራ ውላ ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ የቤት ውስጥ ሥራ ይጠብቃታል፡፡ ባል ቤቱ ውስጥ ገብቶ ቴሌቪዥን በመመልከት መረጃ ይቃርማል፡፡ ወይም ይሰበስባል፡፡ ወንዶች ከጓደኞቻቸው ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት ፈጥረው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ለሴቷ ግን ይህ ዕድል አይሰጣትም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በራስ መተማመን እንድታጣና ትልቅ ደረጃ የመድረስ ውጥኗንም ክፉኛ ይፈታተናታል፡፡ እነዚህም ሌሎች ያልተጠቃቀሱት መሰናክሎች ሁሉ ሴትን በሥራዋና በትምህርቷ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሴት ዩኒቨርሲቲ ለማስገባት የሚያስችላትን ነጥብ ዝቅ በማድረግ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም፡፡ ዩኒቨርሲቲም ከገባች በኋላ የተለየች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን፣ በትምህርቷ ልትጠናከርበት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ስታልፈው የነበረው መሰናክሎች አዕምሮዋ ላይ የጣሉባት የአልችልም ባይነትና የዝቅተኝነት ስሜት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ልክ እንዳልሆነ፣ እሷ ግን አቅም እንዳላት፣ ብቁ እንደሆነች ሊያሳዩዋትና ሊያጠናክሯት የሚገቡ ተግባሮች ሊሠሩ ይገባል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...