Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአፀያፊው የነዳጅ ዝርፊያና ወረራ

አፀያፊው የነዳጅ ዝርፊያና ወረራ

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

እኔን የሚገርመኝ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የምዕራባውያኑ አፈ ቀላጤዎች የግብዝነት ጫጫታ ነው፡፡ አሁን የነዳጅ ዝርፊያ ለወሮበላው ጉጅሌ ቁምነገር ሆኖ ነው ያን ያህል የተካበደው?

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ገና ሲፈጠር አንስቶ ጥርሱን ነቅሎ ያደገውና እዚህ ደረጃ የደረሰው ባንኮችን በጠራራ ፀሐይ እየዘረፈ፣ የካዝና ቁልፍ ገንጥሎ የሕዝብ ገንዘብ እየመነተፈ፣ መንገድ እያፈረሰና ድልድይ እየደረመሰ አይደለም እንዴ?

ዝርክርክና ዓይቶ አያውቆቹ የትሕነግ ጀሌዎች እኮ ሰብዓዊ ማዕበል ተጠቅመው የዛሬ ዓመት አማራ ክልልን በግፍ በወረሩበት ወቅት በውድ ዋጋ የሚሸጠውን ነዳጅ ይቅርና አርሶ አደሯ እመቤት አቡክታ በቡሆ ዕቃዋ ያስቀመጠችውን ያደረና ሊጋገር የደረሰ ሊጥ እየገለበጡ በመጠጣት፣ ጠኔያቸውን ለጊዜው ሲያስታግሱና የደረቀ ጉሮሯቸውን ሲያርሱ አስተውለናል፡፡ ለወራት ቤተሰብ ፍጆታ የተቀመመና በጉሽጉሻ የተቀመጠ ሽሮ፣ ወይም በርበሬና የተደቆሰ ድልህስ መቼ ቀራቸውና፡፡

እነሆ ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ ተከማችቶ ይጠበቅ ነበር የተባለውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ማዕከላዊ መጋዘን በኃይል ጥሰው በመግባት፣ በዚያ የተቀመጠውን 570,000 ሊትር ነዳጅ ዘይት የተሞላባቸውን 12 ታንከሮች ጭነው ወሰዱ ተብሎ በሰበር ዜናነት ሲስተጋባ መሰንበቱ ለማያውቁሽ ታጠኚ ያሰኛል፡፡

‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› ይላሉ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን፡፡ ይህንን ጆሮ የሚበክል ዜና በመጀመሪያ ወደ አደባባይ አውጥተው ያሰጡት ዴቪድ ቢስሊ (David Beasley) ሲሆኑ እሳቸው ከፍ ብሎ የተጠቀሰው፣ ማለትም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡

በእርግጥ ወሬውን ከእሳቸው ቀበል አድርገው የተመድ ዋና ጸሐፊ የአንቶኒዮ ጉተሬስ ቁጥር አንድ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፈን ዱጃሪክ (Stephan Dujarric) በይፋ ደግመው አስተጋብተውታል፡፡

ቀድሞ ነገር ትሕነግ ራሱ በጫረውና አለቅጥ በተራዘመው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ክፉኛ ለተሽመደመዱትና ኑሯቸው ለተናጋባቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የዕርዳታ እህል፣ ነፍስ አድን መድኃኒትና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ያገለግል ዘንድ ታስቦ የተቀመጠ ነበር የተባለለትን ብዛት ያለው ነዳጅ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 24 ቀን 2022 ሊነጋጋ አካባቢ በዝርፊያ ጭነው ወስደውታል፡፡ መጋዘኑን በኃላፊነት ይጠብቁ የነበሩትና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የድርጅቱ ሠራተኞች ሊከላከሉ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው እንደቀረ ሁለቱ ባለሥልጣናት ከገለጹ በኋላ፣ በዝርፊያ የተወሰደው ነዳጅ በአፋጣኝ እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡ ድንቄም ተመለሰ፡፡

ወገኖቼ ሆይ

ይህ አጋጣሚ ለጊዜው በመጠኑ ፈገግ ያሰኝ እንደሆነ ነው እንጂ ክፉኛ ያሳዝናል፣ ያማልም፡፡

ከልባቸው ይሁን ከአንደበታቸው ባይታወቅም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ራሳቸውም ቢሆኑ አስነዋሪውን የትሕነግ ወንበዴዎች አድራጎት ፍፁም አናዳጅና አሳፋሪ (Outrageous and Disgraceful) ሲሉ ነበር በወቅቱ የተበሳጩ መስለው የገለጹት፡፡

አጅሬ ትሕነግስ ምኑ ሞኝ ነው ታዲያ? ነዳጁን እንደ ተወራው እኔ አልዘረፍኩም፣ ያበደርኩትን ነው በራሴ ሥልጣን መልሼ የወሰድኩት ብሏቸው እርፍ አላለም መሰላችሁ?

ቡድኑ እንደሚያላግጠው በመካከላቸው የብድር ውል ከነበረ በአበዳሪው የተናጠል ስርቆት ወይም ድፍረት የተሞላበት ቅሚያ ሊፈጸም መቻል አለመቻሉን የሚያውቀው ራሱ ትሕነግ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡

‹‹የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ›› እንዲሉ የለየለት ሹፈትና ቅጥፈት ይሏችኋል ይህ ነው እንግዲህ፡፡ ለነገሩ የነዳጅ ዝርፊያው እንኳ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ነው፡፡

እነሱም ቢሆኑ ነውረኛው ቡድን ለምን ይህንን አፀያፊ ድርጊት እንደፈጸመ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ሳይተባበሩት እንዳልቀሩ ብንጠራጠርም እኮ አይፈረድብንም፡፡

ያንኑ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ተከትሎ ክልፍልፉና አረመኔው የትሕነግ ሠራዊት በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ በበርካታ ግንባሮች ሦስተኛ ዙር ጥቃት ለመክፈት ቀናት አልወሰደበትም፡፡ አንቶኒዮ ጉተሬስና የበታች ሹሞቻቸው ግን ወራሪውን ለይቶ በፅኑ ከመኮነን በመታቀብ፣ አጥቂና ተጠቂ ያካሂዱታል ያሉትን ወታደራዊ ግጭት አቁመው በጠረጴዛ ዙሪያ ለሰላማዊ ድርድር ይቀመጡ ዘንድ ያለ መታከት ሲመክሩና አልፎ አልፎም ሲገስጹ እንሰማቸዋለን፡፡

በእርግጥ እነዚህ ወገኖች ብለን ነበር ለማለት ያህል ብቻ ከተራ ውግዘት ባለፈ ተፋላሚ ኃይሎች በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ረገድ ያሉባቸውን ግዴታዎች እንዲወጡ በማለት፣ የተለመደውን የቁራ ጩኸታቸውን ከማሰማት ቦዝነው የሚያውቁበትን ጊዜ በበኩሌ አላስታውስም፡፡

እዚህ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጭራሽ ሊስተው የማይችለው ጥሬ ሀቅ ቢኖር ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ብቻ ሳትሆን፣ በማቋቋሚያ ቻርተሩ አንቀጽ ሦስት መሠረት የራሱ የመንግሥታቱ ማኅበር መሥራች አባል ጭምር መሆኗን ነው፡፡ ትግራይ ክልል ግን በአንፃሩ የዚህችው አገር ክፍለ ግዛት እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ምድር አይደለችም፡፡

በአሁኑ ወቅት በፈላጭ ቆራጭነት ተቆጣጥሮ የሚያስተዳድራት ቡድንም በመጥፎ ፀባዩ ምክንያት በአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አማካይነት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ተሳዳጅ ድርጅት እንጂ፣ በመንግሥታቱ ማኅበር ዕውቅና ተሰጥቶት የተመዘገበ ነፃና ሉዓላዊ አካል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡

ታዲያ ይህ መሆኑ በሚገባ እየታወቀ ተወደደም ተጠላ ሕጋዊውን ማዕከላዊ መንግሥትና በሽብርተኝነት ተፈርጆ ሳለ፣ ይህ አልበቃው ብሎ አስቀድሞ በፈጸመው ወንጀል ከመፀፀት ይልቅ፣ በአገሪቱ ህልውናና የግዛት አንድነት ላይ እንደገና ጦር ሰብቆ የተነሳውን አጉራ ዘለል ድርጅት እኩል በአንድ ሚዛን ላይ አስቀምጦ አርፋችሁ ተቀመጡና ለሰላም ተደራደሩ በማለት ማላገጥና የተዛባ ብያኔ መስጠት ከነውሮች ሁሉ የላቀ ነውር መሆን አለበት፡፡

መቼም ምዕራብ አውሮፓውያኑና አሜሪካውያኑ ለብሔራዊ ጥቅሞቻቸው መከበር ይበልጡኑ በማጋደል እንዲህ ያለውን የወገናዊነት ዝንባሌ ቢያሳዩ እኮ እምብዛም ላይገርም ይችል ይሆናል፡፡ የዋና ጸሐፊውን ጨምሮ በኃያላኑ መንግሥታት ምሪትና ተፅዕኖ ሥር ወድቆ በዚህ ደረጃ ባይዘወር ይመረጥ የነበረው የተመድ ልዩ ልዩ ተቋማት ጭፍን ፍርደ ገምድልነት ግን፣ ድርጅቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ማግሥት ከተቋቋመበት መሠረታዊ ፍልስፍና አኳያ ቅቡልና ተገማች ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ተመድ የነፃና ሉዓላዊ አገሮች ማኅበር ሲሆን፣ በቻርተሩ አንቀጽ አራት ንዑስ አንቀጽ (አንድ) ሥር በተደነገገው መሠረት በአባልነት ተቀብሎ የሚመዘግበው ሰላም-ወዳድና ማኅበሩ የሚጥልባቸውን ግዴታዎች ለመፈጸም ዝግጁና ፈቃደኛ ሆነው የተገኙትን መንግሥታት እንጂ፣ እንደ ትሕነግ በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት የተፈረጁ ሕገወጥና ተሳዳጅ የአመፃ ድርጅቶችን አይደለም፡፡

የወቅቱ ዋና ጸሐፊ ግን የቻርተሩን መንፈስና ኃይለ ቃል በግልጽ በሚቃረን ያፈነገጠ አቀራረብ፣ ሕጋዊውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የወሮበላውን ቡድን መሪ እኩል በሆነ አቋም ሲገናኟቸውና ሲያዋሯቸው ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፅንኦት ሰጥተን የምንከታተለው፡፡ ይህ መቼም የዲፕሎማሲ ሀሁን ላልቆጠረ ሰው እንኳ የሚመጥን ዘይቤ አይደለም፡፡

በዚህ ዓይነቱ የተወላገደ የውጭ አካላት ዕይታ ጭምር የተደፋፈረው ትሕነግ እንደ ልማዱ የአማራና የአፋር ክልሎችን እንደገና ማተራመስ፣ ሰላማዊ ዜጎችን በጭካኔ ማረድ፣ አንጡራ ሀብታቸውን መዝረፍ፣ ማውደምና ከመኖሪያ ቀዬአቸው ማፈናቀል ከጀመረ እነሆ ሁለት ሳምንታትን ሊደፍን ትንሽ ነው የቀረው፡፡

ለሰብዓዊ ዕርዳታ ፍሰትና ተደራሽነት ሲባል ከአምስት ወራት በፊት የፌዴራሉ መንግሥት በተናጠል ወስዶት የነበረውንና ትሕነግ ራሱ ዘግይቶ የተቀበለውን የተኩስ ማቆም ዕርምጃ ያላግባብ ተጋፍቶ በከፈተውና የመጨረሻው መጀመሪያ በሚመስለው በዚህ ሦስተኛ ዙር ዕብሪት ወለድ ወረራው፣ ከትግራይ ጋር ተዋሳኝ በሆኑት የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች ላይ እየወረደ ያለው የመከራ ዶፍ መጠኑ የበዛና ሊቋቋሙት የማይቻል ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ ካለፈው ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ አዲስ ተቀስቅሶ ቁጥር ሥፍር ወደ ሌላቸው የከተማና የገጠር ቀበሌዎች በተስፋፋው ጦርነት እየደረሰ ካለው የንፁኃን ወገኖቻችን ዕልቂት፣ የማኅበረሰቦቻችን ከየመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀልና መጠነ ሰፊ የሀብት ውድመት ይልቅ በምስኪኑ የትግራይ ክልል ነዋሪ ወገናችን ስም በየብስና በአየር ማጓጓዣዎች ለዋልጌው የትሕነግ ሠራዊት ሊተላለፍ የሚገባው ወታደራዊ ቀለብ መቋረጥ አብዝቶ የሚያስጨንቃቸው ግብዞቹ እነ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ እነ ሳማንታ ፓዎርና እነ አንቶኒ ብሊንከን በግፍ እየተጠቃም ቢሆን መንግሥት የተከፈተበትን ወረራ ከመከላከል ይታቀብ ዘንድ በተገላቢጦሹ አጥብቀው ሲወሰውሱት ይደመጣሉ፡፡

እንግዲህ ጫፍ የረገጠና ከዚህ የባሰ ፍርደ ገምድልነት ከየት ሊመጣ እንደሚችል ለመረዳት ጨርሶ ያዳግታል፡፡

ወያኔ ከውልደቱ ጀምሮ ሌላው ይቅርና ራሱ በበቀለበት የትግራይ ሕዝብ ችጋርና ሥቃይ ሲነግድና ሲበለፅግ የኖረ መሰሪ ድርጅት እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በአስከፊው የረሃብና የቸነፈር ወቅት እንኳ ለተረጂዎች የሚለገሰውን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ እህልም ሆነ ሌላ ቁሳቁስ በሱዳን ገበያ በግላጭ እየቸረቸረ የጦር መሣሪያ ይሸምትበት እንደነበር፣ በጊዜው አብረውት የሠሩ ሁሉ እስኪበቃን ድረስ ነግረውናል፡፡ ለዚህ ደግሞ እነ አቦይ ገብረ መድኅን አርዓያ ህያዋን እማኞች ናቸው፡፡

ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ጥምር ጦር በሚያካሂደው የመከላከል ፍልሚያ በሚደረምሳቸው የትሕነግ ምሽጎች ውስጥ እንደተከማቸ በቁጥጥር ሥር እየዋለ ያለው የስንዴና የበቆሎ ዱቄት፣ ኃይል ሰጪ ብስኩትና መድኃኒት ለሰብዓዊ አገልግሎት ከተላከ የአቅርቦት መጋዘኖች በዝርፊያ የተሰባሰበ ወይም ከእኩያን አጋሮቹ በትብብር የተገኘ እንጂ፣ ወንበዴው ኃይል ጻድቅ ሆኖ ከሰማይ የወረደለት መና ነው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ ይህንን ቅሌት በሚገባ ለማረጋገጥ በየመባልዕቱና የነፍስ አድን መድኃኒቶቹ የማሸጊያ ከረጢቶች ላይ የታተመውን የለጋሽ ኤጀንሲዎች ስምና ዓርማ በጨረፍታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል፡፡

ዓለም በሚገባ ይወቀው እንጂ ታዲያ ይህ በቡድኑ ዘንድ አሳፋሪ ድርጊት ነው ተብሎ አይወሰድም፡፡

ከሳምንታት በፊት እንኳ ለዕርዳታ የሚላክ የምግብ አቅርቦት ለተዋጊ ኃይሎች ቀለብ ታውላላችሁ በሚል ለቀረበለት አሸማቃቂ ጥያቄ የወያኔው ፕሬዚዳንት ነኝ የሚለው የቡድኑ ፊታውራሪ፣ እየተቅለሰለሰም ቢሆን የሰጠው ምላሽ ፍፁም አስተማማኝና ታዳምያኑን በሰፊው ያስገረመ ሆኖ ነበር የተደመጠው፡፡

ሰውየው የቡድኑን ምግባረ ብልሹነት በአፅንአት ለመከላከል እምብዛም አላቅማማም፡፡ ይልቁንም ዓይኑን በጥሬ ጨው አጥቦ፣ ‹‹ሠራዊታችን ምን በልቶ እንዲዋጋ ነበር የምትጠብቁት?›› ሲል በፖሊሲ የተደገፈ የሚመስለውንና በጄኔቫ ስምምነቶች ጭምር የተወገዘውን ድርጅታዊ ሌብነት በአደባባይ ለማስተጋባት አንዳች ዓይነት ኃፍረት አልተሰማውም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...