Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹አዲስ አበባ ቤቴ›› የድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ማስታወሻ

‹‹አዲስ አበባ ቤቴ›› የድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ማስታወሻ

ቀን:

አዲስ አበባ ቤቴ (4)

ሸጋ ልጅ ቆንጆ

አለች ጎረቤቴ (7)

ኧረ እንዲያው ይመኙሻል (3)

በምኞት ቢጓጉ ወዴት

ያገኙሻል ያገኙሻል፤ (6)

የሚለውን ግጥም በማዜም የብዙ ሰዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ በተለይም ቄንጠኛ በሆነ አለባበሱ መድረክ ላይ ወጥቶ ዜማዎቹን በማንጎራጎር ስመ ጥር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ (ነብስ ኄር) በሕይወት እያለ በተለያዩ አገሮች ተዘዋውሮ በማዜም ሙዚቃውን አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ካደረጉ ድምፃውያን ተርታ ይመደባል፡፡

ዓለማየሁ እሸቴ የሠራቸውን ሥራዎች ታሳቢ በማድረግ ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹ፣ የሙያ አጋሮቹና ሌሎች ባለሙያዎች በተገኙበት በኤሊያና ሆቴል ላይ የዕረፍት አንደኛ ዓመት ተዘክሯል፡፡ በዝክሩ ላይም ድምፃዊ መሐሙድ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን የድምፃዊው የሕይወት ታሪክና ሥራዎች የሚያወሳ መጽሐፍም ለምርቃት በቅቷል፡፡

‹‹አዲስ አበባ ቤቴ›› የተሰኘውና የዓለማየሁ እሸቴን የሕይወት ታሪክ የሚቃኘው መጽሐፍ ለንባብ ያበቁት አቶ ወሰን ጥበበ ናቸው፡፡

መጽሐፉ ለአንባቢያን ለማቅረብ አምስት ወር መፍጀቱን አንድ ሺሕ ኮፒ ብቻ መታተሙን የገለጹት ደራሲው፣ በቀጣይም መጽሐፉንም በብዛት አሳትሞ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ባለ400 ገጽ መጽሐፉ በተለይ የዓለማየሁን የፍቅር ሕይወትና የሙዚቃ ሥራዎቹን እንዲሁም ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

ለመጽሐፉ የተሰጠው ርዕስ ‹‹አዲስ አበባ ቤቴ›› የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት ዓለማየሁ እሸቴ የራሱ ሥራ ስለሆነና አዲስ አበባዊያንን ጭምር ያነቃቃ በመሆኑ እንደሆነ አክለዋል፡፡

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ያዘጋጀው አንደኛ ሙት ዓመት ዝክር ላይ ድምፃዊ ኩኩ ሰብስቤና ዳዊት ጽጌ መድረክ ላይ ወጥተው በመቀባበል ዓለማየሁ ከኩኩ ሰብስቤ ጋር የዘፈነውን  

‹‹እንግዳዬ ነሽ የእኔ እንግዳ

በበሩ ገብተሽ አረፍ በይ ጓዳ›› ን

በማዜም የታዳሚውን ቀልብ ስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዓለማየሁ አድናቂዎች የሆኑ ድምፃውያን በየተራ በመነሳት የርሱን ሙዚቃዎች በመጫወት አክብሮታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኩር ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ሲታወስ

የበኩር ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ዓምና በነሐሴ መገባደጃ የተሰማውን ዜና ዕረፍቱን ተከትሎ ሙያዊ አስተያየቷን የሰጠችው ዕውቋ የሥነ ሙዚቃ (ሙዚኮሎጂ) ፕሮፌሰር፣ ትምክሕት ተፈራ (ዶ/ር) ናት፡፡ እንዲህም ብላ ነበር፡- ‹‹የዓለማየሁ እሸቴ ዘፈኖች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶች ዓውደ ሕይወታቸውን እንዲቃኙ ያደረጉ፣ የማነቃቂያ ምንጭም የሆኑላቸው ናቸው፡፡››

የዓለማየሁ ሙዚቃ ትሩፋቶች ከልጅነትና ታዳጊነት አልፎ እስከ ልሂቅነት በሕይወት መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጋቸውም ይወሳል፡፡ በዓለማየሁ ሙዚቃ ሥራዎች ላይ በርካታ ጥናቶችን አዘጋጅታ በጆርናሎች ያሳተመችው፣ ባለፈው ሐምሌ ወርም Reminisscing the Ethiopian James Brown Alemayehu Eshete`s Artistic Legacy (የኢትዮጵያዊው ጀምስ ብራውን ዓለማየሁ እሸቴ ጥበባዊ ውርስ) በአማዞን በማሳተም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሠራጭቷል፡፡ 

 ትምክሕት ለአብነት በማሳያነት ያቀረበቻቸው ዘፈኖቹን እንደሚከተለው ሰድራዋለች፡፡ አዲስ አበባ ቤቴ፣ ጭሮ አዳሪ ነኝ፣ ሕይወቴ አባቴ ነው፣ ማን ይሆን ትልቅ ሰው? መማር መመራመር፣ ተማር ልጄ፣ ትምህርት ቤቴ እና እናት እንጀራ እናት፡፡ እነዚህን ጥቂቶቹን ዘፈኖች በዘመን አይሽሬ ቅኝት አግዝፋዋለች፡፡

ከስድስት አሠርታት በፊት የተጀመረው ሙዚቃዊ ሕይወቱ ዓለማየሁ እስከ 400 የሚደርሱትን ሥራዎቹን ማቅረቡንም አውስታለች፡፡

በተለይ ‹‹ወርቃማ ዘመን›› ተብሎ በሚታወቀው የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ዐረፍተ ዘመን ገንነው ከተነሱት ድምፃውያን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሠለፈው ዓለማየሁ ዘፈኖቻቸውን በሸክላ ካሳተሙ የመጀመርያዎቹ ድምፃውያን አንዱ ነበር፡፡ በአምሃ እሸቴ ሪከርዲንግ የተቀረፁት ሁለቱ ሥራዎች ‹‹ትማረኪያለሽ›› እና በሱዳንኛ ያቀነቀነው ‹‹ያታራ›› ናቸው፡፡

በ1933 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው ዓለማየሁ እሸቴ፣ በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ በ1955 ዓ.ም. ተቀጥሮ ለስድስት ዓመታት አገልግሏል፡፡ በእነዚያ ዘመናት ያቀነቀናቸው ዘፈኖች ተቃውሞና ፖለቲካ አዘል እንደነበሩ የትምክሕት ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከነዚያ ዘፈኖች መካከል ያበጠው ይፈንዳ፣ ስቀሽ አታስቂኝ፣ ሲያውቁልሽ አታውቂ፣ ወልደሽ ተኪ እናቴ ይጠቀሳሉ፡፡

የፖሊስ ባንድ ባልደረባ የነበሩት የኮሎኔል ግርማ ኃይሌ ድርሰትና ቅንብር የሆነው ‹‹ወልደሽ ተኪ እናቴ›› በዘመኑ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ጭቆና፣ ጉቦ፣ ኢፍትሐዊ አስተዳደርን በሰምና ወርቅ መንገድ የተገለጸውን ነው ዓለማየሁ ያቀነቀነው፡፡

ሃይ ዘራፍ እያሉ እያረረ አንጀቴ

እኔስ አልረባሽም ወልደሽ ተኪ እናቴ

አጋምና ቀጋ ለኔ ተስማምቶኛል

ቅቤማ ከጠጣሁ እንጥል ይወርደኛል

በስቃይ ወልደሽኝ በስቃይ አድጌ

መቼም አልተሻሻልኩ ልኑር ከሰው ግርጌ

ዮሜሳን ለሆዴ መች ይገዛልኛል

እንቆቆ እየተጋትኩ ዶሮ ማታ ይሉኛል

ቅቤውም ይትረፍረፍ ጮማም ይቆረጥ

እማማ እኔና አንቺ ሽሮ እናሯሩጥ፡፡

ዓለማየሁ ከፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ በኋላ ባንዶች በሮሃ፣ ሸበሌ፣ አይቤክስ፣ ሶሊኮስ ባንድና በሙላቱ አስታጥቄ ባንድ መጫወቱ ይታወሳል፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ ገዝፈው ከተገኙት ሥራዎቹ ስለ ትምህርት የተጫወተው ‹‹ተማር ልጄ›› ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በጀርመን ሽልማት ያገኘበት የዚህ ዘፈን አንዱ አንጓ የመማርን ልዕልና ያንፀባርቃል፡፡

‹‹ተማር ልጄ ተማር ልጄ

ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝ ከጄ

ስማኝ ልጄ ሌት ፀሓይ ነው

ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...