Monday, December 4, 2023

የተጀመረው የሰላም ሒደት እንዲቀጥልና የመገናኛ ብዙኃንም ስለሰላምና አብሮነት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ምክር ቤቱ አሳሰበ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከጦርነትና ግጭት ትርፍ ሊያገኝ የሚችል የኅብረተሰብ አካል እንደማይኖር በመጠቆም፣ ለዜጎችም ሆነ ለአገር የሚበጀውን፣ ጠቃሚ የሆነውንና ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተጀምሮ የነበረው የሰላም ሒደት በአስቸኳይ እንዲጀመር ጠይቆ፣ የመገናኛ ብዙኃንም ስለሰላምና አብሮነት ትኩረት ሰጥተው አሳስቧል፡፡

ምክር ቤቱ ጳጉሜን 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሰራጨው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ዳግም ጦርነት ውዱ የሰው ሕይወት በመቀጠፉ የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፣ ሁኔታውን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ተፋላሚ ኃይሎች የድርድር ሒደት ይበል የሚያስኝ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን  ምክር  ቤት ከ60 በላይ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃንና እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማኅበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም መሆኑን አስታውሶ፣ በሥነ  ምግባር የታነፀና  በኃላፊነት ስሜት  ሕዝብን  የሚያገለግል ሚዲያ  በኢትዮጵያ እንዲጎለብት የሚሠራ መሆኑንና ዳግም ያገረሸው ግጭት ተባብሶና ሰፍቶ የሚቀጥል ከሆነ፣ ከሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት በተጨማሪ ለከባድ ሰብዓዊ ቀውስና የንብረት ውድመት የሚያጋልጥ መሆኑን ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የጦርነት ጠባሳ ሕያው ምስክር መሆኑን አብራርቷል፡፡

መገናኛ ብዙኃን ወቅቱን አስመልክተው የግጭት መረጃዎችን ለሕዝብ በሚያደርሱበት ጊዜ በምክር ቤቱ የፀደቀውንና ማንኛውም ጋዜጠኛ ሊከተላቸው የሚገቡ የሥነ ምግባር ደንቦችን በማክበር መሆን እንዳለበትም ምክር ቤቱ አክሏል፡፡

የሚዲያ ተቋማት በዚህ ወቅት በተቀናጀ መልኩ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ላይ በማተኮር እንዲሁም የሕዝቦችን ለዘመናት የኖረውን አብሮነት በማስቀደም፣ ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሠሩ የሚገባበት ሰዓት መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ‹‹ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለሕዝብ የሚቀርቡ ዘገባዎችን ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሊዘነጋ አይገባም፤›› ብሎ፣ በተለይም መገናኛ ብዙኃን ጦርነቱን የሚያባብሱ፣ ጥላቻን የሚሰብኩና ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን ክልከላዎች ማክበር እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ በዘገባዎቻቸው ማናቸውንም የኅብረተሰብ ክፍል በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም ፖለቲካዊ አስተሳሰብን አስመልክቶ ጥላቻን የሚያበረታታ፣ ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ ምክር ቤቱ ባፀደቀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ መሥፈሩን ጠቁሞ፣ መገናኛ ብዙኃንም የሥነ ምግባር ደንቡን አክብረው መሥራት እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡

‹‹የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ሥነ ምግባር ጋር የተቆራኘ ነው፣ በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት አለባቸው›› ያለው ምክር ቤቱ፣ ከሕዝቦች፣ ከብሔረሰቦች ወይም ከሃይማኖቶች ጋር በተያያዘ በሚነሱ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች ላይ የሚሠሩ ዜናዎች፣ አስተያየቶች ወይም የሚሰነዘሩ ሐሳቦች እውነታዎቹ በተገቢው ሁኔታ ከተረጋገጡ በኋላ መቅረብ ያለባቸው በመሆኑ፣ ትኩረታቸው በመፍትሔው ላይ ሆኖ የሕዝቦችን ትስስር፣ ወዳጅነትና ሰላምን ለማስፈን በሚያስችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ በተለይ በሕዝቦች መካከል የመነሳሳት ስሜቶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ የጦር ሜዳ ፎቶግራፎችንና አሰቃቂ ምሥሎችን ከማሳተም ወይም ከማሰራጨት መታቀብ እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡

የሰላም ጥሪ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች፣ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ ከውጭ አገሮች መንግሥታት፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከተመድና ከተለያዩ ወገኖች እየተስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ተፋላሚ ወገኖች መሣሪያቸውን አውርደው ወደ ንግግር እንዲገቡና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ለሰላም ዘብ በመቆም ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡም እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

ጦርነቱ እንዳገረሸና ግጭቱ እንደተባባሰ በኃላፊነት ስሜት መረጃዎችን እያስተላለፉ ያሉ የሚዲያ ተቋማት የመኖራቸውን ያህል፣ በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አሳሳች መረጃዎችና መላምቶች ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች መስተዋላቸውን አስታውሶ፣ በዚህ አጋጣሚ መረጃዎችን ከታማኝ የዜና ምንጮች ብቻ በመጠቀም መሥራት የሚገባ መሆኑንና አደገኛ የሆኑና ለኅብረተሰቡ ቢሰራጩ ተጨማሪ ጉዳት የሚፈጥሩ ያልተረጋገጡ መረጃዎች እንዳይሰራጩ መከላከል ቸል ሊባል የማይገባ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመግለጫው አስታውሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -