Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቲማቲም በሽታ በመግባቱ ምክንያት የቲማቲም እጥረት ተከሰተ

የቲማቲም በሽታ በመግባቱ ምክንያት የቲማቲም እጥረት ተከሰተ

ቀን:

‹‹በሽታው ከዝናብ ጋር የተያያዘ ነው›› ግብርና ሚኒስቴር

በመቂ ከተማ ክረምት ክረምት በሚከሰት ‹‹ሊፍ ስፖት›› ፈንገስ በተባለ በሽታ ምክንያት የቲማቲም ምርት እጥረት መከሰቱን፣ ከመቂ ከተማ የመጡ የቲማቲም አምራቾች ተናገሩ፡፡ የቲማቲም ዋጋ ጭማሪ በቀጥታ ከበሽታው መከሰት ጋር ይገናኛል ብለዋል፡፡

‹‹ሊፍ ስፖት›› የተባለ የፈንገስ በሽታ በቲማቲም ፍሬና ቅጠሎች ላይ ጥቁር ምልክት በመፍጠር የሚያጠቃ በሽታ በመቂ ከተማ በተደጋጋሚ የሚከሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዝናብ ጋር ተያይዞ በሚመጣው በሽታ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው አካባቢ የቲማቲምና ሽንኩርት ምርት ሙሉ በሙሉ ማምረት የሚያቆሙበት ወቅትም በመሆኑ፣ ከፍተኛ እጥረት ተከስቷል ሲሉ አምራቾቹ ገልጸዋል፡፡

‹‹የፈንገስ በሽታ እንዳይከሰት የክረምት ዝናብ ከመጀመሩ በፊት፣ የፈንገስ ኬሚካል ርጭት መደረግ አለበት፤›› ሲሉ በግብርና ሚኒስትር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሤ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሊፍ ስፖት› የተባለው ፈንገስ በሽታ ከዝናብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እርጥበት በሚበዛበት ጊዜ የተባዩ ሥርጭት ከፍተኛ ስለሚሆን፣ በክረምት ወቅት በብዛት ይከሰታል፡፡ ዝናብ እየቀነሰ ሲመጣ በሽታው እንደሚጠፋ አቶ በላይነህ ገልጸዋል፡፡

የቲማቲም ዋጋ በአሁኑ ጊዜ ከ60 እስከ 80 ብር በተለያዩ አካባቢዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የቲማቲም ዋጋ ጭማሪና የምርት እጥረት በቀጥታ ከበሽታው ጋር የተገናኘበት ምክንያት፣ በሽታው በሚከሰትበት ወቅት ጥራት የሌለውና አነስተኛ ምርት በመሰብሰቡ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገረቻቸው አምራቾች ገልጸዋል፡፡

ከ ‹ሊፍ ስፖት› የፈንገስ በሽታ በተጨማሪ ከእሳት ራት ዝርያ የሚመጣ ‹ቅጠል ሰርሳሪ› (Tuta Absoluta) የተሰኘ ከሰባት ዓመታት በፊት ከደቡብ አሜሪካ የገባ ተባይ በየጊዜው በመከሰት ጉዳት እንደሚያደርስ አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡

ከደቡብ አሜሪካ በመጣበት የመጀመሪያ ወቅት ላይ ብዙ የቲማቲም ምርት ካወደመ በኋላ፣ በሽታውን ለመቆጣጠር ኬሚካል በውድ ዋጋ በመግዛት የመከላከል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

ይህ በሽታ ሊከሰት የሚችለው ኬሚካሉ ውድ ስለሆነና ገበሬዎች በማሳቸው ላይ መከሰቱን ባለማስተዋል ርጭት ባለማድረጋቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አቶ በላይነህ ገልጸዋል፡፡

በአብዛኛው የቲማቲሙን ቅጠል ሰርስረው የሚገቡ በላዩ ላይ ስለሆነ ኬሚካሉ በሚረጭበት ጊዜ የተፈጠሩት ‹ቅጠል ሰርሳሪ› የተባለው ትል ይሞታል፡፡ ይህ ትል መፈጠሩ ከታወቀ በኋላ በኬሜካሉ መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ኬሚካሉ በሊትር 14 ሺሕ ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ ገበሬዎች በማኅበር ተደራጅተው አንድ እሽግ 250 ሊትር በመግዛት ይጠቀማሉ፡፡ በአንድ ጊዜ 250 ሊትር ታሽጎ ስለሚመጣ በጋራ ማኅበር ፈጥረው ይገዛሉ፡፡ ለአንድ ሄክታር አነስተኛ የሆነ ሚሊ ሊትር ኬሚካል መርጨት ስለሚቻል በአንድ ሊትር በርካታ ሄክታር መጠቀም ይችላል፡፡ በደንብ እርሻውን በማሰስ ተባዮቹ መከሰታቸው ከታወቀ በኋላ ኬሚካሉን መርጨት አስፈላጊ መሆኑን አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡

ገበያ ውስጥ የሚታዩት ጥቁር ነገር የሌለው ቲማቲም ከሆኑ፣ ኬሚካል የተደረገባቸው ስለሆኑ በበሽታው የተጠቁትንም ሆነ ኬሚካል የተደረገባቸውን ቲማቲሞችን የሚጠቀሙ ሰዎች በማጠብና ንፁህ ቦታ ላይ በማድረግ መሆን አለበት ሲሉ አቶ በላይነህ ገልጸዋል፡፡

እየተመረቱ ያሉት የቲማቲም ምርቶች በውድ በተገዙት ማዳበሪያ የተመረቱ መሆናቸው ዋጋው ላይ ጭማሪ መፍጠራቸው፣ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ የጎርፍ አደጋ መከሰቱ፣ በዚህ ወር ተግባራዊ የሆነው የኮንትራት ፋርሚንግ ስምምነት ላይ የኮንትራት መሬት ዋጋ መጨመር የምርት እጥረትና ዋጋ መጨመር ሌላኛው ምክንያት መሆናቸውን አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታ የቲማቲም ምርት የሚመረት ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ምርት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች እንደ ሐዋሳ፣ ዝዋይና መቂ አካባቢዎች ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ አምራቾች ዋጋ የሚጨምሩበት ሌላኛው ምክንያት አዲስ አበባ በሚገኙ ደላሎች የሚገለጽላቸው ዋጋ መሆኑን የገለጹት አቶ በላይነህ፣ ከገበሬው ላይ በመውሰድ ለተጠቃሚው የሚያቀርብ ደላላ አስፈላጊ ቢሆንም ያላግባብ ዋጋ የሚጨምሩት ከአምራቹ የበለጠ መሆን የለበትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ዋናው መፍትሔ ማኅበራቶችን በማደራጀት ከገበሬው አርሶ አደሮች ጋር በመገናኘት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጥ መደረግ አለበት ሲሉ አቶ በላይነህ ገልጸዋል፡፡

‹‹በክረምት በአብዛኛው አካባቢ የቲማቲም ምርት አይመረትም፡፡ በገበያ ላይ ዋጋ ጭማሪ የተፈጠረው ጥቂት አካባቢዎች ጋር ብቻ ምርት ስለሚመረት ነው፤›› ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሰሩር ገልጸዋል፡፡

በበሽታው ምክንያት እጥረት ተከስቷል በሚል የደረሰ ሪፖርት የለም ሲሉ አቶ ኡስማን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...