Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበተደበላለቁ አገራዊ ስሜቶች የምንቀበለው አዲስ ዓመት

በተደበላለቁ አገራዊ ስሜቶች የምንቀበለው አዲስ ዓመት

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አሮጌው አልፎ አዲስ ዓመት ሲመጣ፣ ዝናባማው ጨፍጋጋ ወቅት አልፎ ፀሐይ ስትወጣ፣ አበቦች ሲፈነዱ፣ ጋራ ሸንተረሩ ልምላሜ ሲላበስ እንደ አገር ተስፋ ማሳደር ያለና የሚጠበቅ ነው፡፡ ተማሪው እንደ አቅሙ አዲስ ልብስ አሰፍቶ/ገዝቶ፣ ደብተር መጽሐፉን አንግቦ አዲስ ክፍል በአዲስ ስሜት የሚጀምርበት፣ ከያኒው፣ መምህሩ፣ ነጋዴው፣ ሐኪሙ፣ ገበሬው… በአዲስ ዕቅድና በታደሰ መንፈስ ወደ ሥራ ለመግባት ደፋ ቀና የሚልበት ነው፡፡

ለነገሩ ሰፊው አርሶና አርብቶ አደርም ቢሆን ምንም እንኳን በመስከረም ወር ምርት ማፈስ ባይችልም፣ እሸት የሚቀምስበትና እስከ ዓመቱ አጋማሽ የሚሰበስበውን ምርት በጉጉት የሚያይበት ወቅቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው በየእምነቱና በየማንነቱ ልማድ አዲስ ዓመትን በራሱ ዓውድና መንፈስ በልዩ ስሜት እየተቀበለ ዓመቱን በብሩህ አዕምሮ ለመጀመር የሚተጋው፡፡

ያም ሆኖ እንደ አገር የምንገኝበት ወቅትና አገራዊ ሁኔታ ፈተናም ተስፋም መሳ ለመሳ ተግተልትለው የተደቀኑበት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ዜጎች ከሰላም ዕጦትና ከመንቀሳቀስ መብት መገደብ አንስቶ ፋታ በማይሰጠው የኑሮ ውድነት ውስጥ ሆነው አዲሱን ዓመት መቀበላቸው፣ ለመንግሥትም ቢሆን የሚጠፋው አይደለም፡፡ ቀዳሚው ችግር እንደ አገር ያሳለፍናቸው አራት ዓመታት የለውጥ ዕርምጃ የተጀመረባቸው ቢሆኑም ከፍተኛ የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የማንነት ጥቃትና ግጭት፣ ብሎም ጦርነትና ምስቅልቅል የተስተናገደባቸው ነበሩ፡፡ ይህም አሁንም ድረስ የፖለቲካ አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ በመሆኑ በሰላምና ደኅንነቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በምጣኔ ሀብትና ዴሞክራሲ ግንባታው ረገድ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

ስለሆነም በርከት ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች የንፁኃን ሕልፈትና ጉዳት፣ የሀብት ውድመትና ጥፋት፣ መፈናቀልና ተረጅነት ተባብሶ እየታየ ነው፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታም እንደ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና የወጭ ገበያ ባሉት ዘርፎች ላይ ያሳደረው  ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በአገር ላይ የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት እንዲባባስም በር እየከፈተ ይገኛል፡፡ በግርግር ውስጥ ሙስናና ዘረፋ ውስጥ ገብቶ የሚርመጠመጠውና ሕዝብ የሚያስለቅሰው አመራርና ባለሙያም ትንሽ አይመስልም፡፡

በዜህ ላይ እንደ ኮቪድ-19፣ የታላላቅ አገሮች ጦርነትና የዓለም አቀፉ የሰብል ገበያ መለዋወጥ ጫናቸው ቀላል አልነበረም፡፡ ከሁሉ በላይ የችግራችንን ሥረ መሠረት ሳይለይም ሆነ አውቆ እያሳሳተ ጫና ለማሳደር የሚሞክረው የምዕራቡ ዓለም ሁኔታም ለችግራችን አለመቃለል አንድ ደንቃራ ፈጥሯል፡፡

በእነዚህ ቀላል የማይባሉ ጫናዎች ውስጥም ሆነን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ ወደ መጠናቀቅ መቃረቡና ኃይል ማመንጨት መጀመሩ፣ የአረንጓዴ ልማትና የበጋ ስንዴን የመሰሉ ተስፋዎች መታየታቸው፣ የቱሪዝም ዘርፉን ሊያስመነድጉ የሚችሉ የመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች መስፋፋታቸው፣ የውጭ ባንኮችን የመሰሉ አዳዲስ የምጣኔ ሀብት ገጾች በአገር ላይ እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱና መሰል መልካም ጎኖች በታዩበት ወቅት ነው አዲሱን ዓመት የምንቀበለው የሚለው ተስፋ ያጭራል፡፡

በሰላምና በደኅንነት ረገድ ድርድር ወይም ውይይት መሠረት የሆናቸው የፖለቲካ መፍትሔዎች ባይፈጠሩም፣ በመንግሥት ረገድ ዋነኛ እንቅፋት የሆኑት አማፅያንን ከሕዝብ ነጥሎ ክፉኛ የመታበትና ያደከመበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ሌላው ቀርቶ በውጭ ጠላቶች ደጋፊነት ድንበር ጥሶና የአገር ሉዓላዊነትን ገፍቶ የመጣው የአልሻባብ ቡድን ክፉኛ ተመትቶ የተመለሰበት፣ የሱዳን ወታዳራዊ ኃይልም የመጨረሻዎቹን ዕድሎች በጥሞና እንዲመለከት የተገደደበት ሁኔታ መኖሩን አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ግን መጭው ጊዜ ብሩህ ስለመሆኑ በቂ መረጋገጫ አይሆኑም፡፡

እስከ ጳጉሜን መጨረሻ 2014 ዓ.ም. ድረስ በአገራችን የተፈጠረው የፖለቲካ መካረር (በተለይ የሕወሓትና የሸኔ የቀውስ መንገድ) በአገሪቱ ሁለንተናዊ የለውጥ መንገድ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ቆይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሒደቱ መንግሥት በሚወስዳቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዕርምጃዎች ላይ ሁሉ አለመተማመንና ውዝግብ እየተፈጠረ፣ ከትርምሱ የሚወጣበት ሁኔታ ናፍቆን ነው የከረመው፡፡

ያም ሆኖ  አዲስ ዓመት ስንቀበል በተስፋና በብሩህ ዕሳቤ መጀመር ግድ ስለሚል እንደ አገር ደፍረን የምንመኘው ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት ብሎም ለውጥና መሻሻልን ነው ማስተጋባት ያለብን፡፡ መጪውን ዕድላችንን የምንወስንበትን የመነጋገርና የመደማመጥ ተግባር ማስቀደምና እንደ ሕዝብ እየገጠሙን ያሉትን ፈተናዎች በመተሳሰብና በመተባበር ለመፍታትና ለማቃለል መነሳት እንዳለብን ማስታወስም ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ከሴራና ከመጠላለፍ በመውጣት ለሕዝብ ጥቅም ይህን ከማድረግ ሌላ ምን የተሻለ አማራጭ አለ?

በየመስኩ ወደ መጪው ዓመት እየተንከባለሉ የሚቀጥሉ የአስተሳሰብ ግድፈቶችንና የአገር ዕዳዎችን ለማስቀረትና ቢያንስ ለመቀነስ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ መንግሥትና ሕዝብ በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ከሠለጠነውና ከጠንካራው ዓለም ትምህርት መውሰድም ብልህነት ነው፡፡

በተለይ አገራችን ምናልባትም ላለፉት በርካታ ዘመናት በተመላለሰችበት የጦርነትና የግጭት አዙሪት ውስጥ መግባቷ ፈጣን መፍትሔ የሚሻ ችግራችን ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ በርከት ላሉ ዓመታት “ተንፈስ” ያለን ሕዝብ ለስደት፣ ለሞትና ለእንግልት እየዳረገ ያለው የሰሜኑ ጦርነት ጉዳይ አንዳች እልባት እንዲያገኝ ካልተደረገ፣ ከታሪክ የማንማር ደካማ መሆናችንን ነው የሚያጋልጠው፡፡ በእውነቱ ሕዝብን ዕረፍት መንሳት በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቅ ወንጀልነቱ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በተለይ ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ስም እየማለና እየተገዘተ ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት በአሥር ሺዎች ሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን ገብሮ የፖለቲካ ሥልጣን ያዘ፡፡ ይዞም በአገር ላይ ኢፍትሐዊነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከማንገሥ በላይ፣ ይከተል የነበረው የዘውግ ፌዴራሊዝም ተብዬ የተቃርኖ ሥርዓት የአገር አንድነትና የሕዝቦች አብሮነት ክፉኛ የጎዳ ነበር፡፡ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታም አገርን ወደ ከፋ ጫፍ ከመውሰዱ ባሻገር፣ ሕወሓት መራሹን መንግሥት በሕዝብ ማዕበል እስከ መጠረግ አድርሶታል፡፡

ይህ ኃይል ካለፈው ስህተት ተምሮ የሕዝቡን (በተለይም የአዲሱን ትውልድ ፍላጎት ተገንዝቦ) ራሱን ከማሻሻል ይልቅ፣ ከየትኛውም አካል ጋር ተደራድሮም ሆነ የሕግ የበላይነትን አክብሮ የፖለቲካ ተሳትፎውን ማስቀጠል ሲገባው መልሶ የትግራይን ሕዝብ ወደ እሳት መማገዱ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አሁን ያለው ሥርዓትም ቀደም ሲል ከተተከለው የተሳሳተ አካሄድ (የብሔር ፖለቲካ አተካሮ) ካልወጣ አገር ማስቀጠል የሚቻል አይሆንም፡፡

ስለዚህ አዲሱ ዓመት ይዞልን የመጣውን የአዲስ ሕይወትና አካሄድ ፈለግ  በአግባቡ ለመጠቀም፣ ሕወሓትም ሆነ መንግሥት በውስጣቸው ያለውን የአሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት አቁመው፣ የአሠራር ልምድና አካሄድ ትብትቡን በጣጥሰው መቀየርና ለአዲስ ዓመት የሚመጥን ባህሪ፣ ዘዴ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ ግድም ይላቸዋል፡፡ የሰው ልጅ ያለ ለውጥ መኖር የማይችል ፍጥረት መሆኑ አይዘነጋምና፡፡

በዚህ ረገድ አንድም ከግትርነትና ከእልህ ወጥተው ንፁኃንን እየፈጁና እስፈጁ ያሉ ኃይሎች ከሕገወጥ ድርጊታቸው መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም ጉዳት የቀነሰና ውጤት የሚያመጣ ሕጋዊ ዕርምጃ ማጠናከር ወይም ለመነጋገር ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ከሁሉ በላይ በተዛባ ትርክት፣ በቂምና ቁርሾ ብሎም በግጭትና በጦርነት የተቋሰለውን ሕዝብ በብሔራዊ ዕርቅና ይቅር መባባል ዳግም አግባብቶ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ለመውሰድ፣ የዕርቅና የምክክር ጅምሮችን ማጠናከር ይገባል፡፡

ለመንግሥትም ሆነ ለአገር ዕቅዶች መሳካት ደግሞ፣ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ፖለቲከኞችና ምሁራንም በየፊናቸው ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በተለይ ሁሉም ቢሆኑ ከአሮጌ አቁማዳ ውስጥ ወጥተው፣ የሚገዳደራቸውን የአመለካከትና የተግባር ችግር ከየውስጣቸው አውጥተው፣ በአዲስና የተሻለ የአሠራር ሒደት ለመቀየር ራሳቸውን ሊመረምሩና ሊደማመጡ ይገባቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ሰላምና ደኅንነት፣ የፖለቲካ መረጋጋት ከሌለ ዕድገትም ሆነ ዴሞክራሲ፣ ብሎም የሰው ልጅ ዕፎይታ ሊያመጣ እንደማይችል ተገንዝበው ወገናቸውን መታደግ ይኖርባቸዋል፡፡

እዚህ ላይ በጥብቅ መስተዋል ያለበት ለማንም ሆነ ለምንም ቀይ መስመር መቀመጥ ያለበት ሕግና ሥርዓትን የማክበሩ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ተፋላሚ ወገኖችም ሆኑ በግጭቱ ተጎጂ የሆኑ ሰዎች የአንድ አገር ዜጎች እንደ መሆናቸው፣ አገር የምትመራበትን ሕገ መንግሥት (ከእነ ጉድለቱም ቢሆን) መጠበቅና ማስጠበቅ የሁሉም ግዴታ መሆን ነው ያለበት፡፡ ለድርድር የማይቀርበው መሬት ላይ ያለው ሀቅ ብሔራዊ ጥቅምን የማስቀደሙ ጉዳይ ብቻ ነውና፡፡

ሕዝብ እርስ በርሱ በፍቅርና በሰላም ተቻችሎ መኖር እንዳለበት በምድር ብቻ ሳይሆን፣ በሰማይ የተደነገገ እውነት ነው፡፡ በፆታ፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባህል፣ በአካልና በአዕምሮ ተለያይቶ የተፈጠረው እርስ በርሱ እንዲተዋወቅና አብሮ እንዲኖር መሆኑ በቁርአንም/በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረ ነው፡፡ ይህ ልዩነት ጌጥ እንጂ ሸክም አለመሆኑ እየታወቀ ፅንፈኛ ልሂቃን (የትኛውም ችግር የሕዝብ እንዳልሆነ ይታወቃል) ሕዝብን ዒላማ አድርገው ማጥቃታቸውም ሆነ ማለያየታቸው ወንጀል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በምንም መለኪያ ተባይነትም ሊኖረው አይገባም፡፡

አምላክ አለያይቶ የፈጠረውን ሕዝብ የግድ አንድ ዓይነት ለማድረግ “የእኔን እምነት”፣ “የእኔን ባህል”፣ “የእኔን መንገድ” መከተል አለብህ ማለት ፈጣሪን መዳፈር ብቻ ሳይሆን እጅግ የበዛ ድንቁርና ነው (በእውነቱ አሁን ሕወሓትና አሁን ያለው መንግሥት ያለ ጦርነት ችግሩን ፈትተው ቢሆን፣ በአገር ላይ ከደረሰው ኪሳራ አንፃር ምነኛ ባተረፍን ነበር)፡፡ በልዩነታችን ኮርተን፣ በአንድነታችን ፀንተን፣ ተከባብረንና ተደማምጠን የመኖር ግዴታ ያለብን ሕዝብ መሆናችንም ለድርድር የማይቀርበው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ጎበዝ አንታለል ለምድራዊ ቆይታችንም ሆነ ለሰማዩ ቤታችን የሚጠቅመንን ነገር አንዘንጋ፡፡ በአዲሱ ዓመት ግድ መሆን አለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ ተመራጩ መንገድ ራስን መመርመር (መገምገም)፣ እንዲሁም መታገል እንጂ አንዱ በሌላው ላይ እያላከከ፣ ጣት እየተቀሳሰረ ባለፈው ዓመት ጆሮ እየሰማ መጥፎ አሠራርን መቀጠል አይደለም፡፡ በተለይ ሕወሓትንና ኦነግ ሸኔን በህቡዕም ሆነ በግልጽ የሚደግፉ ኃይሎች ሕዝብ እንደ ሕዝብ የተፈጥሮ በረከቶቹንና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቹን ለራሱ ሲል በራሱ ማስከበር  እንደሚችል ማጤን አለባቸው፡፡ መንግሥትም ማየት ያለበት ነገር ካለ ለሞራልና ለሕዝብ ጥቅም ሲል ማየት አለበት፡፡ በቸልተኝነት አገርን ወደ ውድቀት መውሰድ አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል እንደ ሕዝብ በየመስኩ ያለብንን ኃላፊነት በተገቢው ለመወጣት በቁርጠኝነት የምንነሳበት ዓመት ሊሆን ይገባል፡፡ አዲሱ የምንቀበለው 2015 ዓ.ም. ሌላው ቀርቶ ከአገልግሎት ሰጪ፣ ከሕክምናና ከትምህርት ወይም ከፀጥታና ከሰላም ጠባቂዎች ጋር በተገናኛ የሚደርስብንን ጫናና የሙስና ምልክት መታገል/አለመታገል በእጃችን ላይ ያለ ጉዳይ ነው (በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ በአንዳንድ ክልሎችና በአዲስ አበባ ያሳደረው የሕዝብ ምሬት በተለየ ሁኔታ ተመልካች ካላገኘ የመጪው ጊዜ የቀውስ ምክንያት መሆኑ አይቀርም)፡፡

በገጠርና በከተማ ከተፈቀደላቸው በላይ መጠንና ክፍያ የትራንስፖርት ታሪፍ የሚጭሩ፣ ሸማች የሚያስለቅሱ አሻጥረኛ ነጋዴዎችና አገልግሎት አቅራቢዎች መጫወቻ ከመሆን በተናጠልም ሆነ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ የእኛ ፋንታ ነው፡፡ ጥገኛ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማራመድ ሲሉ ንፁኃንን ለችግር የሚያጋልጡና በሰው ልጅ ደም የሚነገዱም አደብ እንዲይዙ ሕዝብ መታገል አለበት፡፡

እዚህ ላይ የሕግ ጥሰቱ በፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ውስጥም ስለሚኖር፣ ሁሉም መንግሥት ያወጣለትን ሕግ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በአዲሱ ዓመት፣ አዲስ ምዕራፍና መንፈስ ከፍቶ መረባረብ ነው የሚበጀው፡፡ ለነገሩ እንደ መገናኛ ብዝኃን፣ የእምነት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ወዘተ ያሉ አካላትም ወደ አዲስ ምዕራፍ ተነቃቅተው በመግባት አገር ሊታደጉ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

እንደ ዜጋ ትንሹም ትልቁም የራሱን ሚና ሳይጫወትና የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ፣ ለሁሉም ጉዳይ የመንግሥትን እጅና ጣልቃ ገብነት መጠበቅ የማይበጀውም ከዚህ አኳያ ነው፡፡ አገርን ወደ ግጭትና ትርምስ፣ ሕዝብን ወደ ሥቃይና መከራ የሚገፉና በየጊዜው በክፉ ሰዎች እየተፈበረኩ ለሚሠራጩ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሰለባ ከመሆን ራሱን መጠበቅ፣ የሕዝቡ የአዲሱ ዓመት ሞራላዊ ግዴታ መሆን ነው ያለበት፡፡ የሕግ ተጠያቂነት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችም ይኖራሉ፡፡ በተለይ እሳት ከማጥፋትና የዕርቅ መንፈስ ከመስበክ ይልቅ እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለመባባስ ነዳጅ የሚያርከፈክፉ ተራ የዩቲዩብና የማኅበራዊ ድረ ገጾች ነጋዴዎች “ሃይ” ማለት ያሻል፡፡  የፖለቲካ ሸቃጮች ከመልዕክቱ በስተጀርባ ሊኖር ስለሚችለው ሥውር ዓላማ ከመጨነቅ ይልቅ፣ ፊት ለፊት በግልጽ የተላለፈውን መልዕክት በቁሙ ማየትና የተሻለውን መምረጥ፣ ከአድሎና ኢሚዛናዊነት የራቀውንም መለየት የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ወደ አድስ መንፈስ መሻገር የሚባለው አንዱ ጭብጥ፣ ዓለም አቀፉን ተፅዕኖ እየተቋቋሙ ትውልድ መታደግ ሊሆን ይገባል፡፡

ሌላው ጠቃሚ የአዲሱ ዓመት ተግባር መሆን ያለበት መንግሥት አዳማጭ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝብ (በውስጡ ልሂቁና ፖለቲከኛው እንዳለ ልብ ይሏል) መንግሥት መደማመጥ አለባቸው ሲባል “እኔ ብቻ አውቃለሁ” ከሚል አዙሪት ወጥተው፣ ወቅቱን የዋጀና የመሀል ቤት ሐሳብን ያራምዱ ለማለት ነው፡፡ አረረም መረረም፣ ሕዝብ መንግሥትን፣ መንግሥትም ሕዝብን መስማት ካልቻሉና ካልተቀራረቡ መጪው ዘመንም ተስፋ ሊሰጠን አይችልም፡፡ የገጠሙ አገራዊ ፈተናዎችም እንዲህ በቀላሉ ሊቃለሉ አይችሉም፡፡

በ2015 ዓ.ም. ከነባር ችግሮቻችን ለመላቀቅ ወይም ቢያንስ እንዲቃለሉልን ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ራሳችንን እንመርምር፡፡ ‹‹ከሐሰተኛ ወዳጅ እውነተኛ ጠላት ይሻላል›› የሚለውን ሁሉም ፖለቲከኞቻችን አጢነው በውጭ ኃይሎች ከመነዳት መቆጠብም ለሁሉም ተፋላሚዎች መነገር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ነገር ሁላችንም የአገር ጥቅምን የምናስቀድም፣ አንዳችን ሌላኛችንን የምንሰማ፣ ብሔራዊ ራዕይ ያለን ዜጎች እንሁን ማለት ይጠቅም ይመስለኛል፡፡ አዲሱ ዓመት የተሻለ ሰላም፣ መረጋጋትና ዕድገት የሚታይበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...