Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ከጠመንጃ ጋር የማይገናኙበት ዘመን ይሁንልን!

የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ከጠመንጃ ጋር የማይገናኙበት ዘመን ይሁንልን!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ እንዲሆንልን በየፊናችን፣ በየቤታችን የምንለዋወጠው መልካም ምኞት ትርጉም የሚኖረውና እውነት የሚሆነው አገራችን በውስጧ ሰላሟ ሲጠበቅ፣ መሠረት ሲይዝና ይህም ከሌሎች አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በዋስትናነት የሚያረጋግጥ ጭምር ሲሆን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መጪው 2015 ዓ.ም. የፖለቲካ ሰላማችንን የነካካውና ያበላሸው አንዳች ነገር ተወግዶ አገራችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የምንመኘው ሁሉንም ለፈጣሪ በመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የራሳችንንም ድርሻ አሟጠን ስንወጣ ጭምር ነው፡፡ የአገራችን አብዛኛው ሕዝብ የሚከተላቸው እምነቶች ሁሉ ከሞላ ጎደል በዚህ ይስማማሉ፣ ወይም ከተፈቀደልኝ በዚህ ያምናሉ፡፡ ‹‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል››፣ ‹‹አላህንም እመን በቅሎህንም እሰር›› የሚባለው በዚህ እምነት ምክንያት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአንድን አገር የፖለቲካ ሰላም (የአገራችንንም ጭምር) ሊፈታተኑና አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ የእምነት፣ የሃይማኖት ነፃነት አለመከበር ነው፡፡ ውጣ ውረድ በበዛበት በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ‹ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው› ይባል የነበረ ቢሆንም፣ የሃይማኖት ሰላማችንን የጠበቀልን ከደኅንነትና ከጥርነፋ መረቡ ይልቅ፣ እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ የሕዝቦች የልማት፣ ከድህነት የመውጣት ጥማት፣ ትርምስና ንቁሪያን መታከትና በቱግታ ለመግለብለብ አለመቸኮል የመሳሰሉት ‹‹ምርቃቶች›› ናቸው፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በኋላ የመጣው ደርግ ቢያንስ ቢያንስ በሕግ ደረጃ ያስተዋወቀው ሃይማኖትንና መንግሥትን ያለያየና አሁን ደግሞ 27 ዓመት በሞላው ሕገ መንግሥት የፀናው ይህ በአንፃራዊነት አዲስ ባህል ግን እግዚአብሔርን/አላህን በሚፈሩ ቅን አማኞች ያላግባብ መነካካትና መሸርሸር፣ ለአደጋም መጋለጥ የለበትም፡፡ ይህ እግረ መንገዳዊ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ማስታወሻ ነው፡፡

እናም ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጦርነቱን የለኮሱትን ልዩ ልዩ ችግሮቻችንን በሙሉ ማስቆምና ማስወገድ በሚያስችል አገራዊ ርብርብ ውስጥ መግባት አለብን፡፡ ስለዚህም ይህንን ጦርነት ይብቃ ከማለት በላይ የትኛውንም ዓይነት ጦርነት የሚለኩሱትን፣ የማያስነሱትን ጉዳዮች ማቆም አለብን ማለት ድረስ ከፍ ማለት አለበት፡፡ የዚህ ትርጉም የተለያዩ ሐሳቦችን፣ የሐሳብ ልዩነቶችን፣ ክርክሮችን፣ አለፍ ሲልም ፀብ የሚያመጡ የአመለካከት ልዩነቶችን እናስወግዳለን ማለት አይደለም፡፡ የሐሳብ ልዩነቶቻችንና ክርክሮቻችን ከጠመንጃ ጋር ሳይገናኙ የሰላም፣ የሥልጣኔና የአዲስ ባህል ግንባታችን ይህን በመሰለ ሰላምን ራሱን አቅፎና ደግፎ በሚያፋፋና በሚያስፋፉ አዲስ የግንኙነት አውታር ላይ እናዋቅራለን ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዚህ ዓይነቱ አያያዝና ለውጥ ለወግ ሳይሆን፣ ከምር የተጀመረው በ2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህ አሁን የምንነጋገርበት ጦርነት የመጣው መንግሥት ሳይፈርስ፣ አገር ሳይናጋ በተጀመረው በዚህ ለውጥና ሰላማዊ ሽግግር ላይ የለየለት ክህደት በመፈጸሙና የአንድ ፓርቲ የግልና የምርኮ ሀብት ሆኖ በተዋቀረው የመከላከያ አቅም ላይ አደጋ በመከፈቱ ነው፡፡ ከዚያ በፊትም ቢሆን ሰፍኖ የኖረውን አፈናና ጥርነፋ መላላትና መንቃት ምክንያት በማድረግ የገዥው ፓርቲ የበላይ ገዥነት/ልዩ ሥልጣን ከተናጋ በኋላ፣ ትናንት እሱ በገዥነት ቁንጮ ላይ በነበረበት ወቅት የሰቀዛቸውን የመብትና የነፃነት ጥያቄዎች እየቀሰቀሰና ግፋ በለው እያለ የሽግግሩን ወቅት የምጥና የጭንቅ ጊዜ የሚያደርግ የግጭት ዘሮችን ዘራ፡፡

ይህም ሆኖ አሁን ያለውና በዓለም ደረጃም በፀጥታው ምክር ቤት የአጀንዳ ወይም የርዕስ አያያዝ ውስጥ የኢትዮጵያ (በቅንፍ የትግራይ) ጦርነት እየተባለ የሚጠራው የተጀመረው፣ ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ ወረራና ጥቃት በመፈጸሙ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ያነሳሁትና የጠቀስኩት ማርቲን ፕላውት የተባለው በ‹‹ግጭት ጋዜጠኝነት›› ላይ ‹‹የተካነው›› (የተካነ የሚባለው) እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያው ጦርነት የእርስ በርስ ጦርነት ሳይሆን፣ አካባቢያዊ ወይም የክልል (ሪጅናል) ጦርነት ነው ማለቱን ገልጫለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር ከዚያ በላይ የሚገርምና የሚከነክን ነገር ይላል፡፡ ‹‹ይህ ጦርነት የትግራይ ውስጥ ጦርነት ብቻ ተደርጎ ይቀርባል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎችም፣ ከትግራይ ጋር ጭራሽ ምንም ግንኙነት የሌላቸው ግጭቶች አሉ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አምስትና ስድስት ያህል የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ የትግራይ ግጭትም የዚሁ አካል ብቻ ነው፡፡ እና የኢትዮጵያ የሥር የመሠረት ችግር የ80 ወይም የ90 ‹‹ኤትኒክ ቡድን ኢምፓየርን›› ችግር እንዴት ትፈታዋለህ? እንዴት ወደ ዴሞክራሲ ትለውጠዋለህ ነው፡፡›› ይህ የማርቲን ፕላውት ሌላው ጉድ ነው፡፡

ሽግግሩ ወደ ዴሞክራሲ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ከኢሕአዴግ አምባገነንነት፣ ፈላጭ ቆራጭነትና አድራጊ ፈጣሪነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ለውጥና ሽግግር ደግሞ በሕወሓት ቁጥጥር የብቻ ባለሙሉ ሥልጣንና ምርኮ ሥር የነበረውን መንግሥታዊ አውታር ገለልተኛ አድርጎ ማዋቀር ያስፈልጋል፡፡ ሕወሓት ሲበዛ የተቃወመው፣ ተቃውሞም መላ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች እንዲዘረገፉ የሠራው ይህንን ቆሜ አላይም ብሎ ነው፡፡ የማርቲን ፕላውት ‹‹ሥዕል›› የሚገርመው፣ ዛሬም ደርግ ጭሰኝነትን ካፈረሰ በኋላ፣ ኢሕአዴግም በተለይም የኢሕአዴግ ዋና አከርካሪና ትርታ፣ የኢሕአዴግን መንግሥታዊ አውታር በብቸኝነት ይዘውረው የነበረው ሕወሓት ‹‹የብሔሮችን በቋንቋ የመሥራትና የመተዳደር መብት›› ተግባራዊ አደረግሁት ካለ በኋላ፣ የሕወሓቱ ‹‹ወኪል ነገረ ፈጅ›› ማርቲን ፕላውት ስለኢትዮጵያ ኢምፓየርነት፣ የኢትዮጵያንም የሥር ችግር ከኢምፓየርነት ወደ ዴሞክራሲ የማሸጋገር ችግር አድርጎ የሚያወራው እንዴት እንደሆነ የሚገባ አይደለም፡፡

የሰውየው ‹‹እንግሊዝነት›› ግን በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የሚካሄደው (የትግራይ ጦርነት) ብቻ  አይደለም ይልና፣ በአገሪቱ ውስጥ ሌሎችም ከትግራይ ጋር ምንም/ፈጽሞ ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ጦርነቶች/ግጭቶች አሉ የሚለው መሠሪነቱ/እንግሊዝነቱ ተድበስብሶ ሊጠፋብን አይገባም፡፡ ይህንን የማርቲን ፕላውት የነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የአልጄዚራ ላይ ‹‹አቋም›› እንደሰማሁ ብዙም ሳይቆይ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስን (ኦፌኮ) የነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ አየሁ፡፡ ይህም መግለጫ ስለ ‹‹በሰሜን ኢትዮጵያ [እንደገና] በተቀሰቀሰው ጦርነትና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት›› ይናገራል፡፡ ስለዚህ ‹‹ግጭቶች መባባስና መቀጠል…›› ያወራል፡፡ ስለ ‹‹ግጭቶች›› ብቻ ሳይሆን ስለጦርነቶችም ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ‹‹እነዚህ አውዳሚ ጦርነቶች›› ይላል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመላው ኦሮሚያ የተስፋፋውን ጦርነት ለመፍታት ቀርቶ ዕውቅና ሊሰጠው አለመቻሉን…›› እንዳሳሰበው ይገልጻል፡፡ ኦፌኮ እነዚህን ከሌሎች መካከል የጠቃቀስኳቸውን ጉዳዮች የሚያነሳው ችግሮች በሰላም/በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ባስተላለፈው ጥሪውና ተማፅኖው ውስጥ ነው፡፡

እኔን የቸገረኝና የጠበበኝ፣ ደንታዬም ሆኖ በእጅጉ ያሳሰበኝ ጦርነቱ ‹‹በብዙ ቁጥር››/ወይም ባለብዙ ቁጥር መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያሉ ‹‹እነዚህ አውዳሚ ጦርነቶች›› እያለ ስለብዙ (ቢያንስ ቢያንስ ከአንድ በላይ ስለሆኑ) ጦርነቶች ያወራል፡፡ ይህ እውነት ነው ወይ? ይህን ጥያቄ በመጠየቅ ላይ እያለሁ ግን መጀመርያ ነገሩን ለማጥራት ይህ መጀመርያ ማርቲን ፕላውት ያነሳው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከትግራዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ብዙ ግጭቶች አሉ ያለው፣ ኋላም ኦፌኮ ያነሳው የ‹‹አውዳሚ ጦርነቶች›› ነገር አሁን ሰሞኑን፣ በተለይም ከነሐሴ 18 እንደገና ማገርሸት ወዲህ የተነሳ/የመጣ ጉዳይ ነው? ወይስ ከዚህ ቀደምም በመላው ድኅረ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የነበረ ዕይታ/መከራከሪያ ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ ራሴን የጠየቅሁበት ምክንያት ሁላችንም የሆነ ‹‹ዝንባሌ›› ወይም አንጋዳነት አለብንና ይህ ነገር አሁን አዲስ የመሰለኝ ሳልሰማው ቀርቼ ነው? ወይስ እየሰማሁት፣ ቢያንስ ቢያንስ እየተነገረ እኔ አልሰማው ብዬ ነው ብዬ ራሴን ደጋግሜ ጠየቅሁ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ ራሴን ሞገትኩት፡፡ በተቻለ መጠን በቤተሰብም፣ በጓደኛም ከዚያም አልፎ በተለያዩ ኑሮ/የሥራ ሕይወት ውስጥ ያሉኝን ግንኙነቶች እየተከተልኩ ያልተጨፈነ ማለት ሀቅን የቆነጠጠ ሐሳብ ከሌሎች ማግኘት የመጀመርያ ዕይታዬ ያመጣልኝን አቋም ሳላደርቅ በክፍት አዕምሮ ተወያየሁ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ስህተቱ የኔ ነው፣ እኔ ሳልሰማ ቀርቼ እንጂ ይህ የብዙ ሰው/ሁሌም የሚቀርብ መከራከሪያ ነው ብዬ ብነሳም ይህንን የሚያረጋግጥልኝ አጣሁ፡፡

 ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እውነቱስ ምንድነው? የሚለውም ዋናው ጉዳይ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ራሱ ከኖቬምበር 2020 ጀምሮ የተነጋገረባቸው ጉዳዮች፣ አጀንዳዎች ራሳቸው በርዕሳቸው/በስያሜያቸው ኢትዮጵያ (ትግራይ) የሚሉ ናቸው፡፡ አዎ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው ግድያ አለ፣ ዕልቂት አለ፡፡ እስከ ጥቅምት 24 የለየለት አደጋ ድረስ 113 (አንድ መቶ አሥራ ሦስት ግጭቶች እንደነበሩ) የተነገረን ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ጦርነት በተነሳና መንግሥት ትግራይ ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቋቋመ በኋላ በመጀመርው የፓርላማ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ላይ ነው፡፡ እስከተጠቀሰው እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 113 ግጭቶች ነበሩ፣ ይህም የጥቅምት 2013 ዓ.ም. ክህደትና ወረራ አይጨምርም ሲባል ይህ ራሱ የ‹‹ግጭት››ን ትርጉም፣ ልክና መልክ የሚናገር ይመስለኛል፡፡ ግጭት ሲባል ዝም ብሎ አለመግባባት ማለት፣ አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሲባልም ዝም ብሎ ቁጥር ብቻ እንዳይመስለን፣ ለምሳሌ ሲዳማ ውስጥ ወላይታዎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ የዚህ ዓይነት የጦርነት ድግሶች ናቸው፡፡ 113 ‹‹ግጭት›› በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ማለት በየሳምንቱ አንድ የጦርነት ድግስ ማለት ነው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ 37፣  አማራ ክልል 23፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 15፣ አዲስ አበባ ላይ 14 ግጭቶች ወይም አደጋዎች ተመስክረዋል ሲባል ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ፣ ከምታውቁት መካከል የሃጫሉ ግድያ ተከታዩ ጣጣና መዘዝ አንዱ ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን በመላው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ሽብር ሲናኝ፣ ወጥቶ መግባት ብርቅ ሲሆን፣ የመንግሥት ተራና መሠረታዊ ሕግ የማስከበር ተግባር ሲሽመደመድ፣ እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዳሉት ‹‹የመንግሥት ሥራ እዚህም እዚያም ማልቀስና መቅበር… ከአንደኛው ለቅሶ ሳንነሳ ወደ ሌላው ለቅሶ መሄድ›› ብቻ ሲሆን ትግራይ ክልል ውስጥ ግን ግጭት የለም፣ መገደል የለም ሁሉም ሰላም ነው፡፡ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በዚሁ የፓርላማው መግለጫ ላይ ያሉቱን ልጥቀስ››

‹‹…በሁሉም ክልሎች ግጭትና መገደል አለ፡፡ ትግራይ ክልል ግን የለም፡፡ እነሱም [ሕወሓቶች] ትንሽ አያፍሩም እኛ ብቻ ነን ሰላም ይላሉ፡፡ አንዳንድ የውጭ ሰዎችም ሳይቀሩ ሰላም እኮ ያለው ትግራይ ክልል ብቻ ነው ይላሉ፡፡ አዎ! እዚያ ሰላም አለ፣ ሰላም የሚያደፈርስ ቀን ከሌሊት የሚሠራ የለም፡፡ እዚህ ያለውን የሚያደፈርሱት እነሱ ስለሆኑ፡፡ ሁሌም የእኛን ቁስል እየቆሰቆሱ ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ አባሉት፡፡ አሠራሩ ግን ተራ አልነበረም፡፡ ፋይናንስ፣ ሥልጠና፣ ሥምሪትና ሚዲያ አለ፡፡ ሚዲያ ተቋም ይዘጋጅና አንድ ነገር ሲፈጠር ኦሮሞ አማራን እንዲህ አደረገ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ አማራን እንዲህ አደረገ ብለው ቀድመው የሚናገሩ እነሱ ናቸው፡፡ በሶሻል ሚዲያና በዋናው ሚዲያ ይናገራሉ፡፡ ሌላው ሞኛ ሞኝ ይከተላቸዋል፡፡ ያንን ተከትሎ እርስ በርስ ይባላል፡፡ ለበለጠ ዕልቂት ይተጋል፡፡ ግጭቱ ቶሎ እንዳይረጋጋ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር በከፍተኛ ደረጃ ሠርተዋል፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ ክፉ ጊዜ፣ ወሳኝ ወቅት፣ የሞት የሽረት፣ የውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ቀውጢ ጊዜ የተናገሩት ብዙ ነገር ያብራራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ‹‹ጦርነት›› ነው? ‹‹ጦርቶች›› የሚለውን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ጥያቄውን እንድናነሳ ያደረገንን የእነ ማርቲን ፕላውትን ‹‹አቋም››፣ ‹‹ሐተታ››፣ ‹‹ትንታኔ›› እንቆቅልሽ ያፍታታል ብዬ እገምታሁ፡፡ በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዚህ ደጋግሜ በጠቀስኩት የፓርላማ ንግግራቸው፣ ይህንን የአንድ መቶ አሥራ ሦስት የግጭት ነገር አንስተው ሲያስረዱ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ጠይቀው መልስ ሰጥተዋል፡፡ ሕወሓቶች ይህንን ሁሉ እያደረጉ/አድርገው ‹‹ተሳክቶላቸዋል ወይ?›› ብለው ጠየቁ፡፡ ስኬት ከሆነ ሰዎች ተገድለዋል፣ ንብረት ወድሟል ብለዋል፡፡ የሕወሓት ‹‹ስኬት›› መለካት ያለበት ግን ከዚህ በላይ ሰፋ ባለ ዕይታ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡

አጠቃላይ የድኅረ 2007 ምርጫ የሕዝብ ትግል በሥርዓቱ ላይ እየበረታ መጥቶ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ መከፋፈል ደረሰ፣ መከፋፈሉም ደጅ ድረስ ወጥቶ መታየት ጀመረ፣ የገዥው ግንባር ኅብረት ይበልጥ እየላላ መጣ፣ የሕወሓት የበላይነትና አቅጣጫ ነዳፊነት፣ ባህሪ ቃኝነት ተናጋ፡፡ የሕወሓት ከቁንጮ ገዥነት መንሸራተት ብቻ ሳይሆን ወደ ትግራይ ወደ ‹‹ክልሉ›› አፈገፈገ፡፡ ይህም ከወደ ሰሜን በኩል ያለው ምላሽ የምን ታመጣለህ፣ ምን አባክ ትሆናህ ፍጥጫ ያለበትም ነበር፡፡ የዚህ ምክንያትና ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉልበት መገለባበጥ የደረሰበት ኢሕአዴግ አገር ይገዛ የነበረው፣ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበረ መንግሥታዊ አውታር/አወታረ መንግሥት አማካይነት ስለነበር ነው፡፡

አዎ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ብዙ ግጭቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ ጠላቶች ብዙ ናቸው፡፡ የሸኔ፣ የጉሙዝ፣ የጋምቤላና የቅማንት የሚባሉ ቡድኖች በገዛ ራሳቸው ቆመው የመላወስ አቅም የሌላቸው ሕወሓት የሚባል ቡድን ሌሎዎች ናቸው፡፡ እና ኢትዮጵያ ውስጥ በቡድኖች፣ በቅጥረኛ ቡድኖች ቁጥርና ልክ ጦርነቶች የሉም፡፡ የውስጥ ጠላቶቻችን ብዙ ቢሆኑም፣ ሥምሪት የተሰጣቸው በተለያዩ ክልሎች መሆኑ ባያከራክርም ጦርነቱ ግን ብዙ አይደለም፡፡ እውነት ነው የሚካሄድብን ጦርነት ባለ ሁለት ምድብ ነው፡፡ ሸኔና የሸኔ ዓይነቹ የሕወሓት ሎሌዎች የሚና ምድባቸው እዚህም እዚያም ውርውር እያሉ በመግደል፣ በመጨፍጨፍና በማውደም ተግባራቸው አገራዊ የህልውና ርብርቡን መበታተን ነው፡፡ ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ጉራፈርዳ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ወዘተ እያለ አንዱን ሲሉት ወደ አንዱ የሚካሄድ ማንነት ላይ ያተኮረ አረመኔያዊ ግድያና ጭፍጨፋ ዒላማው የአማራ ክልል ሕዝብን አጭሶና የጭካኔ አዘቅት ውስጥ አውርዶ፣ እዚያም በኦሮሞ ላይ በቀል እንዲጀመር፣ በዚህም አማካይነት የተያዘው የ2010 ዓ.ም. ለውጥ የወለደው የአማራና የኦሮሞ ምሁራን፣ ፓርቲዎች ምክር/ምክክር እንዲከሽፍ በመላ ኦሮሚያ ሙሉ የማፅዳትና የበቀል ፍጀት እንዲጀመር በዚህም ገዥው ፓርቲ ብልፅግናም፣ ኢትዮጵያም ተተርትረው ድብልቅልቃችን እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ተሳካላቸው? ተሳካለት? ማለትን የመሰለ ጥያቄና መልስ ትርጉም የሚሰጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ነው ጦርነቶች ያሉት ብሎ የክርክር ጭብጥ የሚገባው ይህን ስንረዳ ነው፡፡

የሕወሓት ሸፍጥና ወንጀል፣ የሕወሓት የሚዲያም ሆነ የዲፕሎማሲ ደላሎችና አባባዮች በየጊዜው እንደ አዲስ የሚፈበረክ መከራከሪያ፣ በየአጋጣሚው የሚለቀቅ ‹‹ነጠላ ዜማ›› ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነውን፣ የክልሉን የትግራይን ሕዝብ ዋነኛ ሚና፣ ባለቤትነትና ባለመብትነት ሊያዘናጋን አይገባም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው በተለይም በዚህ በ2014 ዓ.ም. መሰናበቻና የ2015 ዓ.ም. መባቻ ላይ ቆመን የትግራይን ሕዝብ የምንማፀነው፡፡

የትግራይ ሕዝብ ሆይ!

የሕወሓት ጦረኞች እንድትፋታቸው፣ አንቅረህ እንድትተፋታቸው እየተማፀኑህ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ነፃነት የሰላምና የልማት ኑሮ ውስጥ የመግባት ዕድልህ የአንተን ውሳኔ እየጠበቀ ነው! እያልን የምንለምነው!

የኢትዮጵያን ህልውና ከአደጋ ተከላክሎ ዘላቂ ህልውናዋን የማረጋገጥ ዋናው አደራ የለውጡና የሽግግሩ ዋና ግዳጅ ከሆነው ዴሞክራሲን ከማደላደል ሥራ ጋር የገጠመበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያን ማዳን ሙሉ የሚሆነው የትግራይን ሕዝብ ማዳን ሲቻል ነው፡፡ የሕወሓት ጦረኛ አሸባሪዎች ትግራይ ላይ ተተክለው፣ የክልሉን ሕዝብ አግተው እያሉ ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም፡፡ የአገርም የብሔርም ተቆርቋሪነት የተሰለበባቸው እነዚህ ከሃዲዎች ትግራይ ላይ ነገሡ ማለት፣ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ሁሉ በጉያዋ የጦር ሠፈር እንዲያቋቁሙ ፈቀደች ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መቀጠል፣ ዘላቂነትና ሰላም ማግኘት ከሕወሓት ጦረኞች ጋር አብሮ ሊኖር የማይችል ነገር ሆኗል ማለት ደግሞ፣ የትግራይ ሕዝብ ሰላምና ልማትም (ከሕወሓት ጋር) የህልም እንጀራ ሆነ ማለት ነው፡፡ አሁን ዛሬ ይህንን ሀቅ ለመረዳት የትግራይ ሕዝብ ዕውን አንቂ ትሻለህ?! የሕወሓት ጦረኞች ያለ ደም መኖር እንደማይችሉ እነሱ ራሳቸው በተግባር እየተናዘዙልህና እያሳዩህ እኮ ነው!! ሕፃናትህን እየማገዱ በአጎራባች ወገኖችህ በአፋርና በአማራ ላይ የዘመቱት፣ መልሰው መላልሰው የሚዘምቱት ለአንተ ሰላምንና ብልፅግናን ወይም መሬት በጆንያ ጭነው ሊያመጡልህ እንዳነበረና እንዳልሆነ፣ ለበቀል የዘመቱበት የአፋርና የአማራ ሕዝብ በቁጣ ተንጨርጭሮ በአንተና በተወላጆችህ ላይ እከሌ ከእከሌ ሳይል እንዲዘምትና አንተን በማስጠቃትና በማስፈጀት፣ እነ አሜሪካ ለእነሱ እንዲደርሱላቸው መዘየዳቸው እንደነበርና እንደሆነ ለማጤን አስረጂ ያስፈልግሃል?

ትግራይ እንደ ጅግጅጋና ድሬዳዋ ለባህር በር (ለዚያውም በሁለት በኩል ለጂቡቲና ለኤርትራ ወደቦች) ቅርብ እንደ መሆኗ፣ ምርጥ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ ልማት ማዕከል የመሆን ዕድል ያላት አካባቢ መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ የሕወሓት ጦረኞች ግን የውጭ ጠላት አደግዳጊ ሆነው አረፉትና ይህንን ዕድል አንቀው በደምህ እየታጠቡ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ምን እስኪያደርጉህ ትጠብቃለህ? ሕዝባዊነቱን በቅርብ ከምታውቀው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ሆነህ የነጠቁህን በዴሞክራሲያዊ ነፃነት ራስህን በራስህ የማስተዳደር መብት፣ የነጠቁህን የሰላምና የግስጋሴ መናኸሪያ የመሆን ዕድል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ንጠቃቸው!!

እነዚህ ግፈኞች በየአካባቢው ሰርጎ በመግባት ሽብርና ትርምስ የመፍጠር ጣዕረ ሞታዊ መንፈራፈር ውስጥ በሚገኙበት ሁኔታ ውስጥ ግብረ አበራቸውን ከደህነኛው መለየት አስቸጋሪ ነውና፣ በየትም ያለህ ትግራዊ ሁሉ ከኢትዮጵያ ወገኖችህ ጋር በፀረ ሽብሩ ንቁ ትግል ውስጥ ግባ!

በሕወሓት አባልነት ውስጥ የቆያችሁም ሁሉ ከአናታችሁ የተቀመጡትን የሽብር ራሶች በመክዳት ከትግራይ ሕዝብ ጋር መቆማችሁን አስመስክሩ! በአሸባሪ የውጊያ ሥምሪት ውስጥ ያላችሁም፣ እየሸሻችሁና እጅ እየሰጣችሁ የትርምስና የጦረኝነት መጠናቀቅ አካል ሁኑ!

የትግራይ ሕዝብ ሆይ!

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደምና ሽብር የለመደባቸውን የሕወሓት ጦረኞች እያራወጠ በሌላ ድል ትግራይ ውስጥ ቢዘልቅ እንኳ፣ ከእነሱ አፈና ለመላቀቅ አንተ ሆ ብለህ እስካልተነሳህ ድልም፣ የአንተ ኑሮም እየፈጩ ጥሬ ከመሆን ፈቀቅ አይልም፡፡ ለሰላምና ለአዲስ ሕይወት ቆርጠህ ከተነሳህ ግን በመከላከያ ሠራዊት ታግዘህ ያመንካቸውንና ከራስህ የወጡ ሕዝባዊ የደኅንነትና የፀጥታ ዘቦች አቁመህ፣ ከታች እስከ ላይ አንተው የመረጥካቸውና አንተው የምትቆጣጠራቸው ሰዎች የተዋቀሩበት ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም፣ የአፈና መዋቅር ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሚናቸውን እንዲለዩ እያደረግህና እያፀዳህ ቋሚ አስተዳደርህን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች ማደላደል ትችላለህ፡፡

አንዴ እዚህ ቆራጥ ዕርምጃ ውስጥ ከገባህ ወደኋላ መመለስም ሆነ እንደገና ድንግዝግዝ ውስጥ መግባት ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ የምዕራባውያን የሕወሓት ጦረኞችን የደገፉ ጫጫታና ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማዕቀብ የማነቅ ጥረት ሁሉ እምሽክሽኩ ይወጣል፡፡ ሕዝብን ማረን ማለትና እጅ መስጠት ሞታችን ያሉ የሕወሓት ጦረኞች ትጥቅ ትግል እንሞክራለን ብለው በረሃ ቢገቡ እንኳ ዕድሜ አይኖራቸውም፡፡ ምክንያቱም ሕወሓቶች የገነዙት ሁለገብ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴህና ልማትህ ነፍስ ይዘራል፡፡ ነፍስ ዘርቶም ደህነት በሠለጠነበት ሕይወትህ ላይ ከወረት የዘለለ ለውጥ ማምጣት እስከተቻለ ድረስ፣ በረሃ ገብተው ሊተኩሱብህ የሚሞክሩ ርዝራዥ ጦረኞች መክሰማቸው አይቀሬ ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...