ደራሲ በዓሉ ግርማ በ1972 ዓ.ም. ባሳተመው ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት መንገድ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሌ የሚታወስ ነው፡፡
‹‹መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡
ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፡፡ አደስ ተቀቡ፡፡ እንሶስላ ሞቁ፡፡ ወንዝ ወረዱ፡፡ ቄጤማ ለቀሙ፡፡ ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣ ‹አበባዬ ሆይ – ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ – እንደ ጮራይቱ፡፡ የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡
ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ ‹ኢዮሃ አበባዬ- መስከረም ጠባዬ› ተባለ፡፡››