Friday, September 22, 2023

የ2014 ዓ.ም. ዓበይት ሁነቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ተሰናባቹ የኢትዮጵያውያን ዓመት በርካታ ሁነቶች የተከሰቱበት ነበር፡፡ ዓመቱ ድብልቅ ስሜቶችን ከሳች ጉዳዮች ሲፈራረቁበት ያለፈ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአዲስ መንግሥት ምሥረታ ሒደት ትልቅ ተስፋ በሕዝቡ ዘንድ ሲፈነጥቅ የታየውን ያህል፣ ወዲያው በሚፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች በመላ አገር ላይ ሐዘን ሲያጠላ የታየበት ዓመት ነበር፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌትና ኃይል ማመንጨት በአገሪቱ ሐሴት ሲፈጠር የመታየቱን ያህል፣ በዜጎች መፈናቀሎችና ግድያዎች ደግሞ የሐዘን ጥላ ሲያጠላ ነበር፡፡

በብሔራዊ እግር ኳስ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና በግብፅ ብሔራዊ ቡድን ላይ ድል ማስመዘገብ ዜጎች እንኳን ደስ ያለህ ተባብለዋል፡፡ በአትሌቶች ተአምራዊ ድል ተቃቅፈው በደስታ አንብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው በአሰቃቂ የጦርነት ትራጄዲዎች በሐዘንና ጭንቀት ተውጠዋል፡፡ ዓመቱ በትልልቅ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ልዩ ደስታ የተፈጠረበት ብቻ ሳይሆን፣ በኑሮ ውድነትም የሚቆዘምበት ዓመት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡

በተሰናባቹ ዓመት እጅግ ተስፋ ሰጪ አጋጣሚዎች የተፈጠሩትን ያህል፣ ተስፋ አስቆራጭ ገጠመኞችም ተፈጥረውበታል፡፡ አስደሳችም፣ አሳዛኝም፣ በአጠቃላይ ድብልቅ ስሜቶችን የፈጠረው ዓመቱ ሁሉንም ሆኖ ያለፈ የማይረሳ ተብሎ ወደ ታሪክ መዝገቦች የተሸጋገረ ዓመት ነበር፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን የመሳሰሉ (የኢትዮጵያ አራተኛው ፓትሪያክ) የእምነት አባቶችን ያጣችው ኢትዮጵያ፣ በፖለቲካው ዘርፍም ትልልቅ ሰዎችን አጥታለች፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ካሳሁን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ እንዲሁም ካሳ ከበደ (አምባሳደር) በሞት ከተለዩ አንጋፋ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ዓመቱ በሮፍናን ኑሪ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ የተጨፈረበት ብቻ አልነበረም፡፡ ዓመቱ ኢትዮጵያውያን በኑሮ ውድነትና በሰላም ዕጦት ሲናጡ የኖሩበት ብቻ አይደለም፡፡ ዓመቱ በህዳሴ ግድብ ስኬትና በአትሌቶች ድል በፈንጠዚያ ብቻ ተሞልቶ ያለፈ አልነበረም፡፡ ዓመቱ በጭንቀትና ግድያዎች ተሞልቶ ያለፈ ብቻም አይደለም፡፡ በ2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና አርበኝነት ያሳዩበት ዓመትም ጭምር ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የክተት አዋጅ በማወጅ ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ያካሄደውን ወረራ ለመቀልበስ ወደ ግንባር የዘመቱበት ዓመትም ነበር፡፡ የእሳቸውን የክተት ጥሪ ተከትሎ ከአርቲስት እስከ አትሌት ሁሉም ወደ ጦር ግንባር ሲተሙ ታይተዋል፡፡

ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ጦርነት የነበራቸው ጣልቃ ገብነትና ኢፍትሐዊ ዳኝነት ያስቆጣቸው ኢትዮጵያውያን በመስቀል አደባባይ ለተቃውሞ ሲጠራሩ የታየበት ዓመት ነበር፡፡ በመላው ዓለም የሚኖረው ዳያስፖራ በ30 ከተሞች ለተቃውሞ ተጠራርተዋል፡፡ ዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያውንና በኢትዮጵያ ደጋፊዎች ስትጥለቀለቅ ታይታለች፡፡

ዓመቱ ግን በእናት አገር ፍቅር ስሜትና ወኔ ብቻ የተሞላ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ህልውና፣ እንዲሁም በበቃ (No More) እንቅስቃሴ ‹‹አለን አለን ልጆችሽ ወታደር ነን›› እያለ በስሜት ለአገሩ የቆመው ኢትዮጵያዊ ታኅሳስ ተሸኝቶ ጥር ሲተካ ስሜቱ ተለውጦ ይታይ ነበር፡፡ የህልውና ዘመቻ መገባደድን ተከትሎ መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ብዙዎችን ያስከፉ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ጥምር ጦሩ ትግራይ ሳይገባ ባስለቀቃቸው ቦታዎች ይቁም መባሉ፣ በገና በዓል ምሽት የቀድሞ የሕወሓት ባለሥልጣናት ከእስር መፈታታቸው፣ መንግሥት በድብቅ ከሕወሓት ጋር ድርድር ጀመረ መባሉ፣ ሁሉም ነገር ወደ ሰላምና ወደ ዕርቅ ይመለስ መባሉ ሁሉ በወኔ አገሩን ለመደገፍ በተሰበሰበው ኃይል ስሜት ላይ ውኃ የሚቸልስ አጋጣሚ እንደነበር በወቅቱ ከተንፀባረቁ ስሜቶች መረዳት ተችሏል፡፡

በእነዚህ ሁኔታዎች ድብልቅ ስሜቶችን እያስተናገደ ያለፈው ዓመቱ፣ አልፎ አልፎ ከተለመደው የተለየ ትኩረት ሳቢ ክስተቶችንም አላጣም፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የደረሰው ከባድ የድርቅ አደጋ በፖለቲካ ቀውሶች ላይ አርፎ የዘለቀውን የዜጎች ትኩረት የወሰደ ፈታኝ አጋጣሚ ሊባል ይችላል፡፡ የሱዳን ትንኮሳና ድንበር ዘለል ጥቃት ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ወደየት እያመራ ነው የሚል ስሜት የፈጠረ ነው፡፡

ሃይማኖታዊ ሚና ያላቸው ግጭቶችና ውዝግቦች በጎንደር፣ በወልቂጤና አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መፈጠራቸው የራሱ ተፅዕኖ የነበረው አጋጣሚ ነበር፡፡ በደቡብ ክልል በሁሉም አቅጣጫ የተስፋፋው የማንነት ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ እስካሁን የቀጠለና የፖለቲካውን አየር ተቆጣጥሮ የከረመ ነበር፡፡

የሶማሌና አፋር ክልሎች የድንበር ግጭት፣ በቤኒሻንጉልና በምዕራብ ኦሮሚያ ያሉ አለመረጋጋቶች፣ በኦሮሚያና አማራ ክልል አዋሳኞች ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር ተደማምረው ተጨማሪ ቀውስ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ ድርቅና በነዳጅ አቅርቦት እጥረት ክፉኛ ሲፈተን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቡና የወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማሳካት የተቻለበት ነበር መባሉ አስገራሚ አጋጣሚ ነበር፡፡ የነዳጅ ድጎማ መነሳት፣ የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ መከፈት፣ እንዲሁም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአገሪቱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዓበይት አጀንዳዎች ነበሩ ብሎ ማንሳት ይችላል፡፡

በዴሞክራሲ አያያዝና በሰብዓዊ መብቶች ረገድ ብዙ ችግሮች የታየበት የ2014 ዓመት በተልይ በጋዜጠኞችና በማኅበራዊ አንቂዎች የተደጋገመ እስራት መገለጽ የሚችል ነው፡፡ በየአጋጣሚው ሲፈጠር የታየው የዜጎች መታፈንና የት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ የመቆየት ጉዳይ፣ በዓመቱ መነጋገሪያ የነበረ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነበር፡፡

የብሔር ወይም የክልል ፉከክሮች ጎልቶ በታየበት በ2014 ዓ.ም. በገዥው ፓርቲ ብልፅግና ውስጥ ጭምር ይኼው ሽኩቻ እየታየ የታለፈበት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ ዛቢያ የሚያሽከረክረው ብልፅግና የ2013 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫን ማሸነፉን ተከትሎ በ2014 ዓ.ም. ለአዲስ መንግሥት ምሥረታ መብቃቱ ተጠባቂ ሁነት ነበር፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባዔ በደማቁ ማስተናገዱ ከኢሕአዴግ በኋላ ጠንካራ አውራ ፓርቲ በኢትዮጵያ መፈጠሩን የሚያውጅ ይመስል ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይዘገይ ከፓርቲው አፈንግጠው የወጡ ሰዎች ስለፓርቲው ገመናና የኃይል አሠላለፍ በሚዲያ ለሕዝብ ማጋለጣቸው፣ ብልፅግናን ገና የራሱን የውስጥ ቅራኔዎች ያልፈታ ፓርቲ ያስመሰሉት ነበሩ፡፡

በ2014 ዓ.ም. በቀጣናዊና በውጭ ግንኙነት ፖለቲካው መስክም ብዙ ውጣ ውረድ አገሪቱ ማየቷን ከገጠሙ ሁኔታዎች በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑኮች ምልልስ ስትቆጥር የከረመችው ኢትዮጵያ፣ ጄፍሪ ፊልትማን የሚሉ ስሞችንና ኤችአር የሚባሉ የማዕቀብ ማስፈራሪያ ሕጎችን በተደጋጋሚ ስትሰማ ያለፈችበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የኬንያና የሶማሊያ ምርጫዎችን በቅርብ ርቀት በዓይነ ቁራኛ ስትከታተል ያሳለፈችው ኢትዮጵያ፣ ከሱዳን በኩል ግልጽ ትንኮሳና ወረራ ሲገጥማት ቆይታለች፡፡ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ከሰላም ስምምነት መድረስ ትልቅ የቀጣናው ለውጥ ሊባል የሚችል ሲሆን፣ የሱዳን ጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የኢትዮጵያ ጉብኝትም አንደኛው ጂኦ ፖለቲካዊ ክስተት ሊባል የሚችል ነበር፡፡

በእነዚህ ሁሉ የዲፕሎማሲያዊ ክስተቶች ተሞልታ የተጓዘችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ማስተናገዷ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖው ቀላል አልነበረም፡፡ ምዕራባውያን ኃይሎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ወጥረው በያዙበት ከባድ የጫና ዓመት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በተጨማሪ የቻይና አፍሪካ የሰላም ስብሰባን ማስተናገዷ፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን ማስተናገዷ ዓመቱ በመጥፎ ሁኔታ ብቻ አለማለፉን የሚጠቁም ነበር፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የእስራት ሰለባ የመሆናቸውን ጉዳይ የ2014 ዓ.ም. ሌላኛው አሳሳቢ የውጭ ግንኙነት አጀንዳ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ በሳዑዲ እንግልት የሚደርስባቸው ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ ቢሠራም፣ ችግሩ አገር ውስጥ ባሉ ቀውሶች ላይ ተጨማሪ ራስ ምታት የፈጠረ እንደነበር ሊገለጽ ይችላል፡፡

ተሰናባቹ ዓመት በድብልቅ ስሜቶችና ገጠመኞች እንዲገለጽ የሚያደርጉ ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል እጅግ ዘመናዊና ቅንጡ የሆኑትን የአብርሆት ቤተ መጻሕፍትና የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ዋና መቀመጫ ሕንፃ ያስገነባችው አዲስ አበባ ከተማ፣ አንበሳ ፋርማሲና ኢትዮጵያ ሆቴልን የመሳሰሉ የከተማ ታሪክ መገለጫ ሕንፃዎች ሲፈርሱባት መታየቱ የ2014 ዓ.ም. ድብልቅ ሁነት ገጠመኝ ሊባል ይችላል፡፡

ከሁሉ በላይ ግን በሰኔ 2014 ዓ.ም. የተፈጠሩ ሁነቶች የዓመቱን የተደበላለቁ ስሜቶች በሙሉ አካተው ይዘዋል ቢባል የተጋነነ አይመስልም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፓርላማ ማብራሪያ ማግሥት የጠባው ሰኔ ብዙ ገጠመኞችን አስተናግዶ ያለፈ ነበር፡፡

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ እጅግ አጨቃጫቂ ሆኖ ያለፈበት ይህ ወር፣ ለሰሜኑ ጦርነት የድርድር ተስፋ የፈነጠቀበት ወር ነበር፡፡ ሰላምና ድርድር ጎልተው እየተነሱ ባሉበት በዚህ ወር ግን በወለጋ አካባቢ በአማራ ተወላጆች ላይ ከባድ ጭፍጨፋ መፈጸሙን በሚጠቁም ዜና ተሞላ፡፡ ዓለም አቀፍ ውግዘትን ጭምር ያስከተለው ይህ የጭፍጨፋ ዜና ሳይበርድ ደግሞ፣ በጋምቤላ ክልል ሌላ ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቶ አገሪቱ በሐዘን ዜናዎች ተሞላች፡፡ ይህ ሁሉ ሳይበርድ ደግሞ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀች መባሉ በሰኔ ወር ኢትዮጵያ እጅግ አሥጊ ሁኔታ ላይ የወደቀች ነበር ያስመሰላት፡፡

የከተሞች የሕንፃ ቀለም ግራጫ ይሁን መባሉ በ2014 ዓ.ም. ግራ አጋቢ ስሜትን የመፍጠሩን ያህል፣ ዜጎች ቢሞቱም ችግኝ መትከላችንን እንቀጥላለን የሚለው የመንግሥት አቋምም ሌላው አወዛጋቢ ወይም አከራካሪ የፖለቲካ ጉዳይ መባሉ አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. አዲስ ክልል ያገኘችበት ዓመት ሲሆን፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት መሥርቶ ራሱን ችሎ መተዳደር መጀመሩ ትልቅ ጉዳይ ሊባል ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. የታየው የፌደራል መንግሥት ምሥረታ ሒደት በልዩ ሥነ ሥርዓቱና ገጠመኞቹ ከሁሉም የሚጠቀስ ነበር፡፡ የውጭ አገሮች መሪዎች በተገኙበት የተካሄደው የመስከረሙ የአዲስ መንግሥት ምሥረታ፣ ደስታውን የሚያደበዝዙ ዜናዎች ባይከቡት ኖሮ የተዋጣለት በዓል ሊባል ይችል ነበር፡፡

ለእንቁጣጣሽ ኢትዮጵያዊያንን ባልተለመደ ሁኔታ እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ የታዩት የአሜሪካው መሪ ጆ ባይደን መስከረም 7 ቀን የማዕቀብ ፕሬዚዳንታዊ ሕግ በመፈረም የደስታ ምኞታቸውን በተቃራኒው አጠፉት፡፡ በአውሮፓ ኅብረት የማዕቀብ ማስፈራሪያ የተጋመሰው መስከረም የኋላ ኋላ የኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ዕድል መሰረዝ ያሰማ ወር ሆነ፡፡ ከጦርነትና ግጭት ዜና ሳይላቀቅ ያለፈው መስከረም ከተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች መባረር ጋር ተያይዞ፣ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫዎች የተዳረገችበትም ነበር፡፡

አገራዊ ምክክር፣ ሰላም፣ ድርድርና ዕርቅ ተደጋግመው በተጠሩበት በ2014 ዓ.ም. አገሪቱ ያስተናገደችው አስከፊ ጦርነት ደግሞ ከሁሉ በላይ የዓመቱ ከባድ ፈተና እንደነበር ሳይጠቀስ ማለፍ አይቻልም፡፡ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ፣ አጣዬ እያለ በአማራ ክልል በኩል እስከ ደብረሲና ጦርነቱ አካለለ፡፡ በአፋር ጭፍራ፣ ባቲ፣ ሰርዶ እያለ ሚሌ አፋፍ ላይ ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወንድማማች ሕዝቦች ተገዳደሉ፡፡ ተሰናባቹ 2014 ዓ.ም. በብዙ ድብልቅ ስሜቶች የሚገለጽ ዓመት ቢሆንም፣ ይህ ጦርነት ያደረሰው ዕልቂትና ውድመት ግን ሁሌም በታሪክ እንዲነሳ የሚያደርገው ነበር፡፡

መስከረም

–       የዕርዳታ መኪኖች ከትግራይ አለመመለስ

–       የሶማሌ ክልል ምርጫ

–       የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምሥረታ

–       መንግሥት ምሥረታ

–       የአጎዋ ንግድ ማዕቀብ

መጋቢት

–       የብልፅግና ጉባዔ

–       የፓርቲ ሽኩቻ

–       የሕዝብ ውይይት

–       የደቡብ ሱዳን ስምምነት

ጥቅምት

–       አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

–       አማራና አፋር ክልሎች ወረራ

–       የቦረናና ጉጂ ድርቅ

–       የክተት ጥሪ

ሚያዝያ

–       የጂንካና አካባቢው የማንነት ግጭት

–       የአጣዬ ግጭት

–       የሃይማኖት ግጭት

–       የወልቃይት ጉዳይ

–       የኦሮሞና አማራ ልሂቃን ውዝግብ

ኅዳር

–       ኅዳር 13 ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ግንባር ዘመቱ

–       ደቡብ ምዕራብ ክልል በይፋ ተመሠረተ

–       የበቃ (No More) ዘመቻ

–       ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማሰባሰቢያ በአይዞን (Eyezone)

–       ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ከኢትዮጵያ ለቀን እንውጣ ጥሪ

ግንቦት

–       የጦርነት ጉሰማ

–       የሕንፃ ቀለም ውዝግብ

–       የሕግ ማስከበር ዘመቻ

–       የጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እስር

ታኅሳስ

–       የሶማሌ ክልል ድርቅ

–       ኦሚክሮን የኮሮና ሥርጭት ሥጋት

–       የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ

–       ክስ ማቋረጥና የታሳሪዎች መፈታት

–       ወደ አገር ቤት የመግባት ጥሪ ለዳያስፖራው

–       የጋዜጠኞች እሥራት

–       በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ጉዳይ

ሰኔ

–       የጋምቤላ ግጭት

–       የወለጋ ጭፍጨፋ

–       የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች

–       የሕግ ማስከበር ዘመቻ

–       የሱዳን ትንኮሳ

–       የድርድር ሐሳብ

–       የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ

–       የኢዜማ ፓርቲ ምርጫ

–       የቻይና አፍሪካ ሰላም ጉባዔ

ጥር

–       የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ

–       የቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውዝግብ

–       የሚቺሌ አባገዳዎች ግድያ

–       ፋኖና ኢመደበኛ አደረጃጀት ጉዳይ

ሐምሌ

–       የሰርጌ ላቭሮብ ጉብኝት

–       የማንነት ጥያቄዎች በደቡብ

–       የአልሸባብ ወረራ

የካቲት

–       የኅዳሴ ግድብ የመጀመርያ ኃይል ማመንጨት

–       የዓብይ (ዶ/ር) የመጀመርያ የፓርላማ ውሎ

–       የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት

ነሐሴ

–       የክላስተር አደረጃጀት ተቃውሞ

–       የድርድር ተስፋ ማጨለም

–       ዳግም ጦርነት

–       የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -