‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በሚሉት መጽሐፋቸው ሀብተማርያም አሰፋ (ዶ/ር) መስከረምን እንዲህ ገልጸዋታል፡፡
መስከረም ‹‹ምስ-ከረም›› ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው፡፡ የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ወንዞች ንጹሕ ውሃ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት ማለት የተዘሩት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚቆጠቆጡበት ነው ይሉታል፡፡
እንዲህም በመሆኑ የጨለማ የችግርና የአፀባ ጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ የሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ሕዝቡ ስለሚያምንበትም የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው እንስሳ አርዶ ደም አፍስሶ ይቀበለዋል፡፡ ያከብረዋል ሲሉም አክለውበታል፡፡