Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዘመን መለወጫ ከጎዳናው ጓዳ

የዘመን መለወጫ ከጎዳናው ጓዳ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ የበዓል መዳረሻ ላይ ከሚታዩ ትዕይንቶች መካከል በጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር እዚያው ቡና ሲያፈሉ ማየት አንዱ ነው፡፡ እነዚሁ ልጆችና እናቶች ቄጠማ ጎዝጉዘው ፈንዲሻ አፈንድተው ቡና የሚያፈሉት ለቡና ጥማታቸው ሳይሆን፣ ምናልባትም በደረቁ ከመለመን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እያስተላለፉ ባፀፋው እንዲመፀወቱ ነው፡፡ እነዚሁ በበዓል መዳረሻ  ሰሞን የሚጠይቁት ምፅዋት አንድም የዕለት ጉርሳቸውን በሌላ በኩል ደግሞ የበዓሉ ወቅት ተሰብስበው ለማክበር የሚጠቀሙበት ነው፡፡

ረከቦቱ በነጫጭ ሲኒ በጀበናና በቀጤማ ያጀቡት የጎዳና ተዳዳሪዎች ‹‹ወንድም እህት እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ መልካም ምኞታቸውን በሚገልጹበት ወቅት ልቡ የራራላቸው ሰው አምስትም አሥርም ብር ጣል አድርጎ ያልፋል፡፡ የዚህን ጊዜ ከእናትና አባቶቻቸው የወረሱትን ምርቃት እንደ ጉድ ሲያጎርፉትና የመልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ ይታያል፡፡

የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓል መምጣትን ተከትሎ ራሳቸውን ለመለወጥ ዕቅድ ከያዙት መካከል እነዚሁ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ይገኙበታል፡፡ ጎዳና ላይ ወጥታ መኖር ከጀመረች ከአራት ዓመት በላይ ያስቆጠረችው ወጣት ሰላም ወንደሰን እንደምትለው ከሆነ፣ የአዲስ ዓመት በዓልን ለማክበር በዋዜማው በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ቡና እያፈሉ ገንዘብ እየሰበሰቡ ይገኛል፡፡ በአዲሱ ዓመት ከሲጋራ፣ ከማስቲሽ ከተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች ለመውጣት ማቀዷን በመናገርም በከተማዋም ሆነ በተለያዩ ክልሎች ጎዳና ላይ ወጥተው የሚኖሩ ሕፃናትና ልጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ መልካም ምኞቷ መሆኑን ገልጻለች፡፡

እንደ ወጣት ሰላም ገለጻ እስከ ቅርብ ጊዜ በስታዲየም አካባቢ ከጓደኞቿ ጋር ሆና እየለመነችና በየሆቴሉ በመዞር ምግብ እየጠየቀች ትኖር እንደነበር በአዲሱ ዓመት የፀባይም ለውጥ በማምጣት ከቤተሰቧ ጋር ለመኖር ዕቅድ መያዟን አስታውሳለች፡፡

ጎዳና ላይ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ብርድና ዝናቡ ሲፈራረርቅባት እንደነበርና በዚህም የተነሳ የጤና ዕክል አጋጥሟት የሞት አፋፍ ላይ ደርሳ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ከወላጆቿ ጋር ትኖር የነበረችው ሰላም፣ እናቷን በልጅነቷ ማጣቷንና እንዲሁም ደግሞ ተደራራቢ የሆኑ ችግሮች ሲገጥማት የጎዳና ሕይወትን እንደተቀላቀለች ትናገራለች፡፡ ጎዳና ላይ ሕይወትን ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ በየአጥሩ ጥግ ሥር ከሴትና ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር ብጭቅጫቂ ልብስ አድርጋ ኑሯዋን ትገፋ እንደነበር ባልታሰበ ወቅትም እዚያው ጎዳና ላይ ከወጣ ወንድ ጓደኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀምራ እንደነበር አልሸሸገችም፡፡ በቅርቡም ሽሮ ሜዳ አካባቢ ከሚኖረው አያቷ ጋር አብራ ለመኖርና መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡

ከዚህ በፊት ከጎዳና ሕይወት ለመውጣት ጥረት ብታደርግም፣ ሳይሳካላት በመቅረቱ ላልተፈለገ ሱስ ልትጋለጥ እንደቻለች ለሪፖርተር አስረድታለች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በክርስትናም ሆነ በሙስሊም ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩ በዓሎች በሚመጡ ጊዜ አብዛኛዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቤተሰቦቻቸውን እንደሚናፍቁ ትናገራለች፡፡ በከተማዋ የሚኖሩ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ታሳቢ ያደረገ ነገር ባለመኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ካሉበት ሱስ ሊወጡ አልቻሉም የምትለው ወጣቷ፣ መንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች የጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግር በመመልከት ለውጥ ማምጣት አለባቸው ብላለች፡፡

በተለይ ሴት ልጅ ጎዳና ላይ ወጥታ ስትኖር ብዙ ፈተና እንደሚገጥማት እሷም የዚህ ችግር ሰለባ ሆና እንደነበር በአዲሱ ዓመት ግን ሴት ልጆችም ሆኑ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ከጎዳና ሕይወት ወጥተው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ መሠራት አለበት ትላለች፡፡

በጎዳና ላይ አብዛኛውን የሴት ጓደኞቿ በሱስ ተዘፍቀው ብርድና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው መሆኑን የምትናገረው ሰላም፣ እነዚህም ጓደኞቿ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ገብተው እንዳይኖሩና ያሉትን ችግር እንዲፈቱ ሱሳቸው እንደከበዳቸው ታስረዳለች፡፡

ከዚህ በፊት ከቤተሰብ ጋር እያለች ጀብሎ ሆና የተለያዩ ነገሮችን በመሸጥ ቤተሰቧን ትረዳ እንደነበር በሒደት ግን ወደ ጎዳና ሕይወት ገብታ ራሷን ችግር ውስጥ እንዳገኘችው አብራርታለች፡፡

በሌላ በኩል በሰሜ የተከሰተው ጦርነት ማብቂያውን አግኝቶ አገሪቱ ሰላም የምትሆንበት፣ ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞቷን ገልጻለች፡፡ የኑሮ ውድነትና ግጭት የሚያበቃበት ዓመት ይሁን የምትለው ጎዳና ላይ ሕይወቷን ያደረገችው ስሟ እንዳይጠቀስ የምትፈልገው ወጣት ናት፡፡

በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከተለያዩ ሱሶች ተላቀው የተሻለ ሕይወት የሚኖሩበት ዓመት እንዲሆን መንግሥት መሥራት አለበት የምትለው ይህቺ ወጣት በጎዳና ላይ መኖር ከጀመረች ከአራት ዓመት ጊዜ በላይ ማስቆጠሯን ታስረዳለች፡፡

ጎዳና ላይ ከመውጣቷ በፊት ጥሩ ኑሮ እንደምትኖር እናትና አባቷ ሲጋጩ ግን ጎዳና መውጣትን የገለጸችው፡፡ ወጣቷ አብዛኛውን ጊዜ በመለመንና በየሆቴል ቤቱ ትራፊ በመጠየቅ የጎዳና ሕይወትን እየገፋች ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እየበዛ ነው የምትለው ወጣቷ ይኼም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት አንድም በአገሪቷ የሚታየው ጦርነት በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነት እንደሆነ ተናገራለች፡፡

በአዲሱ ዓመት ከቤተሶቦቿ ጋር ተቀላቅላ አቋርጣ የነበረውን ትምህርት ለመጀመር ዕቅድ እንዳላት ቤተሰቦቿም ያለችበትን ሁኔታ ተረድተው ከጎዳና ሕይወት እንዲያወጧት ፍላጎት እንዳላት አስረድታለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውራ በየጢሻውና በየትቦ ሥር እየኖረች እንደሆነ፣ በተለይም ለብርድ ተብሎ የምትወስደው አደንዛዥ ዕፅ ጤናዋ ላይ ችግር እየፈጠረባት እንደሆነ ይኼንንም በአዲሱ ዓመት ለማቆም ማቀዷን ተናግራለች፡፡

ጫት፣ ሲጋራ፣ ማስቲሺ እየሳበች መኖር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ሰውነቷን እንደተጎዳ ከዚህም ችግር ለመውጣት ለውጥ ማምጣት እፈልጋለሁ ብላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...