Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልባለ ጳጉሜን 6ቷ አዲስ ዓመት

ባለ ጳጉሜን 6ቷ አዲስ ዓመት

ቀን:

እነሆ አዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት 2015 ዓ.ም. በፍጥረት የመጀመርያ ቀን አንደኛ የሚል ትርጉም ባለው ዕለተ እሑድ ባተ፡፡ ‹‹ዕንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ›› ተብሎም ተዜመ፡፡ የአዲስ ዘመን አብሣሪዋ አደይ አበባም በምድሪቱ አብባም ታየች፡፡ ልጃገረዶችም ‹‹አበባ አየህ ወይ… ለምለም››ን ዘመሩ፡፡

መስከረም ጠባ እንጂ ክረምቱ ገና የሚያበቃው የመስቀል ደመራው በተለኮሰ በሳምንቱ መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ 

የአዲስ ዘመን ብስራት በአንድ ጎኑ መሬት ከፀሓይ ጋር ካላት ግንኙነት የሚከሰት ነው፡፡ አንድ ዓመት፣ ሁለት ዓመት እየተባለ የሚጠራው መሬት በፀሓይ ዙሪያ ጉዞዋን ለማድረግ የሚፈጅባትን የ365 ከሩብ ቀናት ጉዞ ነው፡፡ በነዚህ የዐውደ ዓመት ቀናት አራቱ ወቅቶች ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ይፈራረቃሉ፡፡

ዘንድሮ አዲሱ ዓመት የሚያበቃው እንደ አዘቦት ዓመት 365ኛ ቀን ላይ ሳይሆን ሩብ ሩቦቹ ተሰባስበው ከአራት ዓመት በኋላ በሚያስገኙት ጳጉሜን 6 ቀን ላይ ነው፡፡

ባለ ጳጉሜን 6ቷ አዲስ ዓመት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በመካከለኛው ኢትዮጵያ በሙገር ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የደርባ ፏፏቴና አደይ አበባ ፎቶ፡ አድቬንቸርስ ኢን ኢትዮጵያ

አደይ አበባና መስከረም

የብርሃን መንገዶቹ ፀሓይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩት ለዕለቶች፣ ለዓመቶች፣ ለዘመኖች (ወቅቶች) እና ለምልክቶች ለማገልገል እንደሆነ የዘፍጥረት ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከሦስቱ ብርሃኖች በተጨማሪ በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ የተፈጠሩት ዕፀዋት፣ አዝርዕትና አትክልትም ከዘመን ብስራት ጋር ቁርኝት አላቸው፡፡ አንዱ ማሳያ በኢትዮጵያ አዲስ ዘመን መባቻ በጠንካራው የክረምት ወቅት መገባደጃ አካባቢ ብቅ የምትለዋ የአደይ አበባ  ናት፡፡ በጳጉሜን በኩል ክረምቱ ሲሻገር፣ መስከረምን የምታደምቀው ዋዜማውን ጨምራ በመስከረም የምትፈነዳውና ለኢትዮጵያ ምድር ጌጧ፣ ሽልማቷም የሆነችው አደይ አበባ ናት፡፡

የሬዲዮ ሞገዶችም የበኩር ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን ከአዲስ ዓመት መባቻ ጋር የተያያዘውን ዘፈን ማስተጋባታቸው አልቀረም፡፡ 

‹‹በፀሐይ ብርሃን ደምቃ ክረምትና በጋ

የትውልድ ሃገር ያላት የ13 ወር ፀጋ…

አቤት አዲሱ ዓመት ዘመኑ ሲለወጥ

የአበቦቹ ሽታ መዓዛው ሲመስጥ፡፡››

ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት እንደተተረጎመው፣ አደይ ማለት የበጨጨ፣ ቢጫ የሆነ አበባ ማለት ነው፡፡ ‹‹አደየ›› በጨጨ፣ ቢጫ መሰለ፤ ነጣ፣ ነጭ ሆነ ሲልም ይፈታል፡፡

ስለአደይ አበባ ተክል ምንነት ሳይንሳዊ መግለጫ ወፍ ዘራሽ አበቦች (Wild Flowers for Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው ከበደ ታደሰ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ አደይ አበባ ከምትበቅልበት ከተለያዩ ከፍታዎች አንፃር ሁለት መልክ አላት፡፡ የተከፋፈሉ ሰፊ ላይዶ ቅጠሎችና ስምንት የተበተኑ መልካበቦች ያሉት ዓመታዊ ሐመልማል፣ ከመንገድ ዳር ዳር እና ከቃሊም፣ እንዲሁም በከፍተኛና ድንጋያማ ተዳፋት፣ ከ400 እስከ 2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ይበቅላል፡፡ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥም ያብባል፡፡ በሌላ በኩልም እስከ ኅዳር ድረስ የሚያብበው የሚገኘው ከ2,000 እስከ 3,600 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ አደይ አበባ ረዣዥም ግንድና ሰፋ ያለ ላይዶ ቅርፅ ያላቸው ቅጠሎች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚበቅል ከረም ሐመልማል ነው ይሉታል፡፡ መሀላቸው ብርቱካንማ የሆነ ብጫ አበቦች በግንዱ ጫፍ ሰብሰብ ብለው ይታያል፡፡

በየመዝሙሩም አደይ አበባ ትገለጻለች፡፡

‹‹አደይ አደይ የመስከረም

እንዳንቺ ያለ የለም

አደይ አበባ የመስከረሙ

እነ ጉብሌ ወዴት ከረሙ

አደይ አበባ የሶሪ ላባ

እፍ እፍ በዪ እንደ ገለባ››

በሌላ በኩል ከወፎች ወገን የሆነች በበጋና በመጋቢቱ ፀደይ መደበኛ መልኳን ይዛ የምትበረው ‹‹የመስቀል ወፍ›› በነባር ስሟ ‹‹የመስከረም ወፍ›› ክረምቱ ሲያልፍ ጥቢው የመፀው (የአበባው) ወቅት ሲመጣ ደምቃና ተውባ ትመጣለች፡፡

ከዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የልጃገረዶች ‹‹አበባየሽ ወይ/ አበባ አየህ ወይ›› ነው፡፡ ወንዶችም ከዘመኑ መቀየር ጋር የሚጫወቱት በተለይ ‹‹ሆያ ሆዬ . . . ሆዬ›› ይጠቀሳል፡፡ በነሐሴ አጋማሽ አካባቢ ከደብረ ታቦር ጋር ተያይዞ ልጆች የሚጫወቱት ሆያ ሆዬ ከመስከረም ዋዜማ እስከ መስቀል በዓል ድረስም ይዘልቃል፡፡ ይህም በተለያዩ አካባቢዎች በትውፊትነቱ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ አካባቢዎች መካከል ላስታ ላሊበላ ይጠቀሳል፡፡

በላስታ ላሊበላም ሆያ ሆዬ እንደ ሌሎቹ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ይከወን እንጂ ዛሬ ድረስ እየተከናወነ የሚገኝ ጨዋታ ነው፡፡ ሆያ ሆዬ በአብዛኛው በቡሄ ሰሞን በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ ከቡሄ ጀምሮ እስከ መስቀል ድረስ ባሉት ይከናወናል፡፡

በባህልና ቋንቋ ባለሙያው መምህር ዓለሙ ኃይሌ በተዘጋጀው ዘመን ተኮር ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደተጠቀሰው፣  በመስከረም ላስታ ላሊበላ ዙሪያዋ ያምራል፣ አካባቢው ያብባል፣ እህሉ ያሸታል፣ አዝመራው ይደርሳል፣ ወንዙ ይጠራል፣ ፏፏቴው ይወርዳል፤ መሬቷ ታሸበርቃለች፤ ፍጥረት ትስቃለች፤ ምድር ትፈነድቃለች፤ የወጣቱ ልብም ይደሰታል፤ ፊቱ ያብባል፤ ገጹ ይፈካል፡፡ የላስታ ወጣት ይህን ስሜቱን ከሚገልጽበት ሕይወቱን ከሚያድስበትና ደስታውንም ከሚያካፍልበት አንዱና ዋናው ‹‹ሆያ ሆዬ›› ነው፡፡

የሆያ ሆዬ ጨዋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት የሚጀምረው ዕለተ በዓሉ ከመከበሩ አምስት ቀናት ቀድሞ (ከጳጉሜን አንድ) ጀምሮ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ወጣት ወንዶች ወንዝ እየወረዱ ገላቸውን ይታጠባሉ፣ ልብሳቸውን ያፀዳሉ፣ ለጭፈራው ዋና መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን ዱላ ያዘጋጃሉ፡፡ ለጨዋታ የሚያስፈልጋቸውን ግጥምም ያጠናሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አለቃና ገንዘብ ያዥም ይመርጣሉ፡፡

የዘመን መለወጫ ዕለትም ሁሉም በየቤቱ የተገኘውን ሲበላና ሲጠጣ ይውልና ወደ ማታ ጅራፍ በማጮህ ይሰባሰባሉ፡፡ ያልወጣውን ለማስወጣት፣ ያልመጣውን ለማስመጣት ሲሉ በየአደባባዩ እየዞሩ ይጣራሉ፣ እየተቀባበሉም ይዘፍናሉ፣ ይጨፍራሉ፡፡ የጭፈራ ሰዓቱ ማታ ማታ የሚከወን ሲሆን፣ ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ገበሬና ከብት ጠባቂ በመሆኑ ከየሥራ ሥምሪቱ ሲመለስ በሥራ የደከመ አካሉንና አዕምሮውን የሚያሳርፍበት፣ የሚዝናናበትና ሕይወቱን ደስ የሚያሰኝበት በመሆኑ ነው፡፡

የዘመን አዋጅ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊት መስከረም አንድ ቀንን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ በርሱ መሰየሙ ይወሳል፡፡

በዕለቱ በቤተክርስቲያኒቱ ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡

የዘንድሮው አዲስ ዓመት 2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ትውፊት መሠረት ዘመነ ሉቃስ ይባላል፡፡ በአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዐውደ ጳጉሜን››/ ‹‹ዐውደ ወንጌላውያን›› 2015 ለ4 ተካፍሎ 503 ደርሶ ቀሪው 3 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዘመኑ የሉቃስ መሆኑ ያመለክታል (1 ከቀረ ማቴዎስ፣ 2 ከቀረ ማርቆስ፣  ቀሪ ከሌለው አራተኛው ዮሐንስ ይሆናል)፡፡  ዘንድሮ የዓለም ፍጥረት መነሻ በሆነው በዓመተ ዓለም ሲቆጠር 7515 ዓመተ ዓለም መሆኑና ስምንተኛው ሺሕ ከገባ 514 ዓመት ማለፉንና 515ኛ ዓመት ላይ መገኘቱን ስሌቱ ያሳያል፡፡

አራቱ ወቅቶች

ዘመን ከሚሞሸርባት፣ ዓመት ከሚቀመርባት ከወርኃ መስከረም የሚነሣው የኢትዮጵያ ዓመት ቁጥር በአራት ወቅቶች የተመደበ ነው፡፡ አራቱ ወቅቶች (ዘመኖች) ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ናቸው፡፡

ሰኔ 26 ቀን የተጀመረው ክረምት (ዝናም፣ የዝናም ወራት) መስከረም 25 አብቅቶ የአበባ ወቅት የሆነው መፀው  በማግስቱ ገብቶ፣ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን ድረስ ለ90 ቀን ይቆያል፡፡  ሌላው መጠርያው መከር ይሰኛል፡፡

አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ›› በሚለው ድርሳናቸው እንዳመሠጠሩት፣ የክረምት ተረካቢው መፀው የተባለው ክፍለ ዘመን እንደ ክረምት የውኃ ባሕርይ ያፈላል፡፡ ይገናል፡፡ እንቡር እንቡር ይላል፤ይዘላል፤ ይጨፍራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወንዞች ይመላሉ፡፡ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡ አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን ፍጥረታት ሆነው ይነሳሉ፡፡ ይበቅላሉ ይለመልማሉ፡፡ አበባና ነፋስን ቀላቅሎ የያዘው ዘመነ መፀው ምሥጢሩ መዓዛ መስጠት፣ እንቡጥና ፍሬ ማሳየት ነው፡፡

ከታኅሣሥ 26 በኋላ የሚመጣው በጋ ሐሩራማ፣ ደረቃማ ነው፡፡ ደረቅነት የሚፀናበት፣ የሚግልበት የሚጋይበት ስለሆነም ሐጋይ ይባላል፡፡  ዘመኑን መጋቢት 25 ቀን ከፈጸመ በኋላ በማግስቱ ለፀደይ (በልግ) ያስረክባል፡፡

በጋ እንደተፈጸመ የሚከተለው ፀደይን፣ የኪወክ መዝገበ ቃላት የአጨዳ ወራት ዘመነ በልግ ይለዋል፡፡ በወዲያ መከር በወዲህ በልግ የሚደርስበት የሚታጨድበት ወዲያውም የሚዘራበት የዘር ወር ሲልም ያክልበታል፡፡ በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት የሚዘንበው ዝናብ የበልግ ዝናብ በመባልም ይጠራል፡፡ ፀደይም ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25 ቆይቶ በማግስቱ ለክረምት ቦታውን ይለቃል፡፡ ቀለልና ለስለስ ያለ ዝናብ የሚኖርበት በልግ በከፊል በጋ ላይና ፀደይ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡

አደይ ሲፈነዳ መስከረም ሲጠባ የሚዜመው ኢዮሃ አበባዬ የመስቀል ደመራው በሚለኮስበት መስከረም 17 ቀንም ይስተጋባል፡፡

‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ

መስከረም ሲጠባ ወደ አገሬ ልግባ›› እየተባለም ይዘመራል፡፡ ኢዮሃ ማለቱ እይ ውሃ ያደረገውን ተአምር ተመልከት ሲሉም ይገልጹታል፡፡ የደስታና የምሥራች ቃል የሆነው ኢዮሃ አበባዬ ወንዶች የደመራ ዕለት እየዘፈኑ ድምሩን የሚዞሩበት የአበባ ዘፈን ነው፡፡

እጓለ ገብረዮሐንስ (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ ባሉት መጽሐፋቸው፣ ከስድስት አሠርታት ግድም በፊት በአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ላይ፣ ባደረጉት ንግግር ማሰሪያቸውን እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡

 ‹‹በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ሲተካ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም ‹በተውሳከ መብልዕ ወመስቴ› [ምግብና መጠጥን በመጨመር] እየተደሰተ፣ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው መሻገሩን በሚያከብርበት ዕለት ትንሽ ጊዜ አስተርፎ ስለጠቅላላው የሕይወት ጉዞ ለሚያስበው ረድኤት ይሆን ዘንድ፣ ለማያስበው ደግሞ እንዲያስብ ምክንያት ይሆን ዘንድ፣ እሊህን ሐሳቦች ለማቅረብ ደፈርን፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...