Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ የቱርኩን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመሸጥ ለስድስተኛ ጊዜ ጨረታ አወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የሚገኘውንና ብድሩን ባለመክፈሉ የወረሰውን ‹‹ኢቱር ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ለመሸጥ ለስድስተኛ ጊዜ ጨረታ አወጣ፡፡

ባንኩ አሥር ሔክታር መሬት ላይ ያረፈውን የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ግንባታዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ተያያዥ ንብረቶችን ለመሸጥ ያቀረበው የጨረታ መነሻ ዋጋ 1.13 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አሸናፊ የሚሆነው ተጫራች ከግዥው ዋጋ በተጨማሪ፣ በክምችትና በጉዞ ላይ ያሉ ግብዓቶችና ምርቶችን በርክክብ ወቅት በሚደረስበት የትመና ዋጋ መሠረት ክፍያ ፈጽሞ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

ዩክሰል ቲክስቲል (Yüksel Tekstil) በተባለው የቱርክ ኩባንያ ባለቤትነት ሥር በ2002 ዓ.ም. የተቋቋመው ኢቱር በግንቦት 2013 ዓ.ም. በንግድ ባንክ አስተዳደር ሥር የሆነው፣ ቱርካዊዎቹ ባለሀብቶች ብድሩን ሳይከፍሉ ከአገር ከወጡ በኋላ ነው፡፡

ባንኩ የሰጠው ብድር ባለመከፈሉ የፋብሪካውን አስተዳደር ከተረከበ በኋላ የመጀመሪያውን የሐራጅ ጨረታ ሐምሌ 2013 ዓ.ም.፣ ሁለተኛውን ደግሞ ከሁለት ወራት በኋላ መስከረም 2014 ዓ.ም. አውጥቷል፡፡ ለሁለት ጊዜያት በወጣው ሐራጅ ያልተሸጠው ኢቱር የልማት ባንክ ንብረት ሆኖ የተጠቃለለ ሲሆን፣ ከተጠቃለለ በኋላ የአሁኑን ጨምሮ ለአራት ጊዜ ጨረታ ወጥቷል፡፡

ለቱርክ ባለሀብቶች ተሰጥው ከተበላሹ ብድሮች መካከል ብዙዎቹን ለግል ባለሀብቶች ያስተላለፈው ልማት ባንክ፣ አሁን በእጁ ላይ የሚገኙት ኢቱርና አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ የፋብሪካው አስተዳደር በባንኩ ሥር ከሆነ በኋላ፣ የሥራ ማስኬጃ በጀት ከልማት ባንክ ተበጅቶለትና አዲስ አስተደዳር ተሹሞለት የማገገም ሒደት ላይ ነው፡፡

ኢቱር አሁን ትርፋማ እንደሆነ ለሪፖርተር የተናገሩት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ ከዚህ ቀደም የወጡት ጨረታዎች ስላለመሳካታቸው፣ ‹‹ከዚህ በፊት ያልተሳካው ገዥ ስላልተገኘ ወይም [የመጡት ገዥዎች] የሚገባውን ስላላሟሉ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ የባንኩ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ፋብሪካው በተበዳሪ እጅ እያለ የነበረበትን ዕዳ መክፈል እንዳይችል ካደረገው ችግር የማውጣት ሒደት ላይ እንደነበረ አስታውሰው፣ ጨረታዎቹ ያልተሳኩት ፋብሪካው የማገገም ሒደቱን ስላላጠናቀቀ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸው ተናግረዋል፡፡

ከፋብሪካ ተረፈ ምርት ከሆኑ የጨርቅ ቁርጥራጮች ክር፣ እንዲሁም ብትን ጨርቅና ያለቀለት ልብስ የሚያመርተው ኢቱር ቴክስታይል፣ በአሁኑ ጊዜ 1,007 ሠራተኞች አሉት፡፡ በቱርካዊ ባለሀብቶች ሥር በነበረበት ጊዜ በተወሰነ መጠን ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ይሞክር እንደነበር ያስታወሱት የፋብሪካው የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ኩራባቸው መንበር፣ አሁን ምርቶቹን በሙሉ የሚያቀርበው ለአገር ውስጥ ገበያ እንደነሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ2006 ዓ.ም. የመጀመሪያው ሩብ በጀት ዓመት 29 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምርት ኤክስፖርት ማድረጉን አስታውቆ ነበር፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተበላሸ የብድር መጠኑ 40.9 በመቶ በመድረሱ እንዲፈርስ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦበት የነበረው ልማት ባንክ፣ የአሁኑ ፕሬዚዳንቱ ዮሐንስ (ዶ/ር) ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተሾሙ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ መሾም በኋላ ብድራቸው ተበላሽቶ የነበሩ 207 ፕሮጀክቶች ለግል ባለሀብቶች ተላልፈዋል፡፡ ባንኩ ከ15 በመቶ ምጣኔ በታች ለማድረስ ጥረት ሲያደርግም ነበር፡፡

ይሁንና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ 24.3 በመቶ መድረሱን ባንኩ አስታውቋል፡፡ አንደ ባንኩ ገለጻ 19.2 ቢሊዮን ብር ከሆነው አጠቃላይ ታማሚ ብድር ውስጥ፣ አሥር ቢሊዮን ብር በትግራይ ክልል ውስጥ ያለ ነው፡፡ በትግራይ ክልል የተሰጠው ብድር ቢወጣ የባንኩ የታማሚ ብድር ምጣኔ ወደ 12 በመቶ እንደሚወርድ ፕሬዚዳንቱ ዮሐንስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡ በትግራይ ክልል ባለው የተበላሸ ብድር ምክንያትም ባንኩ 4.1 ቢሊዮን ብር መጠባበቂያ ከትርፉ ላይ ለመያዝ የተገደደ ሲሆን፣ ይህም ትርፉን ከ7.8 ቢሊዮን ብር ወደ 3.7 ቢሊዮን ብር እንዲወርድ አድርጎታል፡፡

ባንኩ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ባለሀብቶች ብድር ሲሰጥ የነበረው፣ ባለሀብቶቹ የፕሮጀክቱን 30 በመቶ ፋይናንስ ሲያቀርቡ እንደነበር፣ በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሰውአገኝ ጫኔ ባለፈው ሳምንት ለዘ ሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡ ይኼ አሠራር የባንኩ የተበላሸ ብድር በከፍተኛ መጠን ከፍ እንዲል ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ሰውአገኝ፣ አብዛኞቹ ባለሀብቶች በብድር የተሰጣቸውን 70 በመቶ ፋይናንስ ማጥፋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ባለሀብቶች ውስጥም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የቱርክ ባለሀብቶች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

አሁን ባንኩ ለባለሀብቶች ብድር የሚያቀርበው የፕሮጀክቱን 50 በመቶ ፋይናንስ ሲያቀርቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች