Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ውጤት ዝቅ ባትልም አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ  ግን ቀንሷል

ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ውጤት ዝቅ ባትልም አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ  ግን ቀንሷል

ቀን:

በዓለም ላይ ካሉ አገሮች 90 በመቶ የሚሆኑት በሰብዓዊ ልማት ውጤት (Human Development Index) መውረድ ሲያሳዩ፣ የኢትዮጵያ ውጤት ግን አለመውረዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዓመታዊ የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ጠቆመ፡፡ ሆኖም ሪፖርቱ እ.ኤ.አ. በ2020 ተመዝግቦ የነበረው የ66.6 ዓመት አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 65 ዓመት ዝቅ ማለቱን ያሳያል፡፡

ላለፉት 31 ዓመታት በየዓመቱ የዓለም አገሮችን ሰብዓዊ ልማት የሚያጠናው የተመድ የልማት ፕሮግራም (United Nations Development Program-UNDP) በሦስት መለኪያዎች ምርመራ አካሂዶ የ191 አገሮችን ውጤት አሳውቋል፡፡ መለኪያዎቹም ጤናማና ረዥም ዕድሜ መኖር፣ በትምህርት ዕውቀት መቅሰምና ጥሩ የምጣኔ ሀብት አቅም ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ በእነዚሀ መለኪያዎች ከ191 አገሮች 0.498 በማምጣት 175ኛ ወጥታለች፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ደረጃ ባለፈው ዓመት 173ኛ ቢሆንም ውጤቷ ግን 0.485 ነበር፡፡ ይህ የደረጃ ዝቅ ማለት ባለፈው ሪፖርት ተካትተው ያልነበሩ ሁለት ተጨማሪ አገሮች በመካተታቸው መሆኑን፣ የተመድ ልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት አቶ ኃይሌ ክብረት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የልማት ፕሮግራሙ የአገሮችን ውጤት የሚይዘው ከአንድ ሲሆን፣ ካወጣቸው ውጤቶች ውስጥ 0.385 በማምጣት የመጨረሻ ደረጃውን የያዘችው ደቡብ ሱዳን ናት፡፡ በአንደኝነት ደረጃ ደግሞ ስዊዘርላንድ 0.962 በማምጣት ተጠቅሳለች፡፡

ማክሰኞ መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል የልማት ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ቢሮ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት የ14.4 ዓመት ጭማሪ በማሳየት፣ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን አሳይቶ ነበር፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በአጠቃላይ ደረጃ አራተኛ ብትሆንም ሆንግ ኮንግ (ቻይና) በ85.5 ዓመት አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ ከፍተኛዋ አገር ስትሆን ቻድ ደግሞ በ52.5 ዓመት አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ ዝቅተኛዋ አገር ሆናለች፡፡

እንደ አቶ ኃይሉ ገለጻ፣ ለጤናማና ለረዥም ዕድሜ መለኪያ መሥፈርት አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ ዋነኛው መለኪያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በዚህ በኩል ትልቅ ዕድገት ስታሳይ ነበረ፡፡ ሆኖም በዚህኛው ዓመት የታየውን ዝቅተኛ አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ በሌሎች መለኪያዎች ዕድገት በማስመዝገብ አጠቃላይ ውጤቱ ባለበት ሊቆይ እንደቻለ አክለው ተናግረዋል፡፡

‹‹የትምህርት ተደራሽነትና ጥቅል አገራዊ ገቢ በነፍስ ወከፍ ሲለካ የታየው ዕድገት፣ በአማካይ የመኖሪያ ዕድሜ ላይ የታየውን ቅናሽ አካክሶታል፤› ሲሉ አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ሌሎች መለኪያዎች የትምህርት ተደራሽነትና ጥቅል አገራዊ ገቢ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያም በትምህርት ተደራሽነት በኩል ዕድገት ማስመዝገቧ ተገልጿል፡፡ በአማካይ አንድ ዜጋ በትምህርት እንዲያሳልፍ የሚጠበቅበት ዓመት፣ ባለፈው ዓመት ከነበረው 8.8 በዚህኛው ዓመት ወደ 9.7 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ ጥቅል ዓመታዊ ገቢ በነፍስ ወከፍ ተሰልቶም የሚመጣው አምና ከነበረው 2,207 ዶላር ወደ 2,361 ዶላር አድጓል፡፡

ሪፖርቱ ይፋ ሲደረግ በተካሄደው የፓናል ውይይት፣ ከተወያዮች ለመንግሥት የፖለሲ አቅጣጫ ሊሆን የሚችሉ ነጥቦች ቀርበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ መምህር ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) አንደኛው ተሳታፊ ሲሆኑ፣ በእሳቸው በኩል የቀረቡት የፖለሲ አቅጣጫ ሊሆኑ የሚችሉት አገሪቱን ወደ ሰላም ማምጣት፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና የመንግሥትን አቅም በሰው ኃይል ማሳደግ ናቸው፡፡

ከተመድና ከአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈው የነበረ ሲሆን፣ የፖሊሲ አቅጣጫ ይሁን ብለው የጠቆሙት በተመሳሳይ ጦርነቱ አብቅቶ ሰላም ማስፈን፣ የተቋማትን አቅም ማጎልበት፣ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠቀምና ፈጠራን ማበረታት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ