Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከዕለት ዕርዳታ ራስን ወደ ማስቻል

ከዕለት ዕርዳታ ራስን ወደ ማስቻል

ቀን:

የታረዘን ማልበስ፣ የተራበን ማብላት፣ በአጠቃላይ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን “ከጎናችሁ ነን! አለንላችሁ!” ማለት ከጥንት ሲያያዝ የመጣ ብርቅዬ ባህል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ባህል ተተኪው ትውልድ በበለጠ አጠናክሮ ይዞታል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የማዕድ ማጋራት፣ የአልባሳት፣ የገንዘብና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ወዘተ ድጋፍ ማድረጉ መቀጠሉ ነው፡፡

የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች መንፈሳዊ በዓላት በተቃረቡና በመጡ ጊዜ እየተደረገ ያለው ይህ ዓይነቱ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በብዙኃኑ አስተያየት የተሰጠበት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለዘለቄታው ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ማሰብ፣ መቀየስ ቸል ሊባል የማይገባው ጉዳይ መሆኑንም ይወሳል፡፡

 እንደባለሙያዎች አገላለጽ፣ ይህ ካልሆነ ዘንዳ የተረጂነት መንፈስ ሥር ሰዶ ይንሠራፋል፡፡ እንደ ባህልም ይዳብራል፡፡ ከዳበረና ሥር ከሰደደ በኋላ ደግሞ ለመመለስና ለማስተካከል ፈታኝ ይሆናል፡፡ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ መተካት ሲገባው ሁልጊዜ የዕርዳታ እጅ የሚጠባበቅ ዜጋ ሆኖ ይቀራል፡፡

ጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ለማውጣት፣ በአጠቃላይ ችግረኛ ወገኖችን ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ኃላፊነት በአንድ ተቋም ብቻ የሚወሰን መሆን የለበትም፡፡ ስለሆነም ችግረኛ ወገኖችን ከተረጂነት መንፈስ ለማላቀቅና ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል ባሀብቶችና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መንቀሳቀስና ዕቅዶቻቸውንም በዘላቂ ነገር ያተኮረ እንዲሆን ማድረጉ ግድ ይላል፡፡

የተረጂነትን መንፈስ ለማስወገድ አቅም በፈቀደ መጠን ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት መካከል የጳጉሜን አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅት ያከናወናቸውን ተግባራት ለአብነት ይጠቀሳል፡፡ የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ገሠሠ እንደገለጹት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ከሚገኙት ችግረኞች መካከል አቅም በፈቀደ መጠን 150 ያህሉን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፀው ለተግባራዊነቱ ደፋ ቀና እየተባለ ነው፡፡፡፡

የጎዳና ሕይወትን የሚኖሩ፣ ቀን ጨልሞባቸው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ እነዚህን ወገኖች ከተረጂነት የማላቀቁ ሥራ የሚከናወነው በኮንስትራክሽንና በጨርቃ ጨርቅ (ጋርመንት) ሥራዎች ላይ በማሰማራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንና በሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ላይ ያተኮረ ሥልጠና ቀደም ሲል እንደተሰጣቸው፣ በሥልጠናውም ያገኙትን ዕውቀት የማጠናከር ሥራ ላይ ያተኮረ ሌላ ሥልጠናም በቅርቡ እንደሚሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡

ሁለተኛው ዙር ሥልጠና የሚሰጠው በወረዳው የቀድሞ የወጣቶች ማዕከል በአሁኑ ጊዜ የወረዳው ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል መሆኑንና ከሥልጠናውም በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ የሚሰማሩበት መንገድ የሚመቻች መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ችግረኞቹን አሠልጥኖ ወደ ሥራ የማስገባቱ እንቅስቃሴ የሚካሄደው ከወረዳው የወጣቶችና ስፖርት፣ የሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ከኅብረሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመቀናጀት መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ አባባል በፕሮጀክቱ ለታቀፉት ለእነዚሁ 150 ችግረኞች የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት፣ የአልባሳት፣ የአስቤዛና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ውዝፍ የቤት ኪራይ ላለባቸው ደግሞ ውዝፉ እንዲሸፈንላቸው መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በአዲሱ ዓመት ከተረጅነት ተላቅቀው ወደ ሥራ ዓለም ለመግባት እንዲያስችላቸው የሥነ ልቦና እና የአካል ዝግጁነታቸው ላይ ያተኮረ ትምህርት አዘል ገለጻ እንደተደረገላቸው፣ ገለጻውንም ያደረጉት የቀድሞ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩበት በአሁኑ ጊዜ በማማከር ሥራ ላይ የተሠማሩ ተሾመ ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) መሆናቸውን ነው ሥራ አስኪያጁ ያመለከቱት፡፡

የወረዳው የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ደበላ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ‹‹ግብረ ሠናይ ድርጅቱ እያከናወነ ካለው የግብረ ሠናይ ሥራ በተጨማሪ አቅም ያላቸውን በኮንስትራክሽንና በወረቀት ፋብሪካ ውስጥ ሥራ እንዲያገኙ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም እንቅስቃሴ ላይ ጽሕፈት ቤቱ የግል ባለሀብቶችንና ተቋማትን  በማስተባበር ረገድ የተቻለውን ያህል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ሥራ የማግኘት ዕድል ያላቸውም የወረዳው ነዋሪና ለዚህም መታወቂያ ያላቸው ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...