Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየ‘ወጣቷ ንግሥት’ ዳግማዊት ኤልሳቤጥ የጉብኝት ትውስታ በኢትዮጵያ

የ‘ወጣቷ ንግሥት’ ዳግማዊት ኤልሳቤጥ የጉብኝት ትውስታ በኢትዮጵያ

ቀን:

ዘመኑ 1957 ዓ.ም. ወሩ ጥር፣ ሦስተኛ ሳምንት ላይ ነበር በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩት የእንግሊዝ ንግሥት ግርማዊት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ የነገሥታት ንጉሥ ምድር በነበረችው ኢትዮጵያ ለአንድ ሳምንት ጉብኝት ነበር አዲስ አበባ የዘለቁት፡፡

የዕድሜ ባለጸጎች በዘመኑ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በታሪካዊው የሰሜን ኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ መስመር የነበሩ የንግሥቲቱን ጉብኝት ያስታውሳሉ፡፡ ከእነዚህም የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ታሪክ የጻፉት ልጅ አስፋወሰን አሥራተ ካሳ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ እንደሳቸው አገላለጽ፣ በሠላሳዎቹ መገባደጃ ላይ የነበሩት ወጣቷ ንግሥት አዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ሲደርሱ ንጉሠ ነገሥቱ የተቀበሏቸው የኢትዮጵያን የፊልድ ማርሻል ኦፊሴሊያዊ ዩኒፎርም ለብሰው ነበር፡፡ አለባበሳቸው ራሳቸው ላይ ከደፉት አንፋሮ በስተቀር እንግሊዝ ጠቀስ ነው፡፡ የራስ መጎናፀፊያው ባለ ሁለት ጠርዝ ወርቃማ አንፋሮ ነበር፡፡

ለአፄ ኃይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዩ ተብሎ በተሠራው ወርቃማው ሠረገላ ንግሥቲቱ በጎዳናው ሲጓዙ በአውራ ጎዳናው ግራና ቀኝ የተሠለፈው በደስታ የተሞላው ሕዝብ ታላቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡ ንግሥቲቱን ለመቀበል የመንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ተዘግተዋል፡፡ ከቦሌ እስከ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በነበራቸው ጉዞ ግማሹን በአውቶሞቢል ከተጓዙ በኋላ ቀሪውን መንገድ በስድስት ነጫጭ ፈረሶች በሚጎተተው ወርቃማ ሠረገላ ነበር የተጓዙት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ‘ወጣቷ ንግሥት’ ዳግማዊት ኤልሳቤጥ የጉብኝት ትውስታ በኢትዮጵያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ዘጋርዲያን የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ‹‹ኢትዮጵያን ንግሥቲቷን ተቀብላለች›› (Ethiopia Welcomes the Queen) በሚል ርዕስ እንደዘገበው፣ ሠረገላው የአንበሳ ጎፈር ባጠለቁ በ100 የክብር ዘበኛ ፈረሰኞች የተከበበ፣ ሁለቱን ማይል ለመንዳት ከአንድ ሰዓት በላይ ፈጅቶበታል፡፡

በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት የሚታየው ሕንፃ በዘመኑ የአፍሪካ መሪዎች የቅኝ ገዢዎችን ለማውገዝና የደቡባዊው አፍሪካን ነፃ የመውጣት ዕቅድን ለማውጣት የአፍሪካ መሪዎች የተገናኙበት የአፍሪካ አዳራሽ ይመለከቷል፡፡

ነገር ግን የሚለው ዘገባው በመንገዱ ላይ የታየው ባነር ‹‹የታላቋ ብሪታኒያና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ለዘላለም ይኑር›› ይላል፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ባሻገርም ኢትዮጵያን ከጣሊያኖች ነፃ ለማውጣት የረዱ በሦስት የእንግሊዝ ጄኔራሎች ዌቪል፣ ዊንጌት እና ካኒንግሃም የተሰየሙ መንገዶች አሉ፡፡ ዘጋርዲያን እንደዘገበው ያኔ ብሪታኒያ በኢትዮጵያውያን ዓይን ከቅኝ ገዢ ይልቅ ታላቋ አገርና ነፃ አውጪ ነበረች፡፡

ንግሥቲቱ በአዲስ አበባ ከጎበኟቸው የተከበሩ ሥፍራዎች መካከል መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና አፍሪካ አዳራሽ ይገኙበታል፡፡

የንግሥቲቱ መምጣት የዋና ከተማዋን ብቸኛ ዕለታዊ ጋዜጣ [አዲስ ዘመን] የሴቶች ገጽን ለመክፈት አነሳስቶታል ብሏል ዘገባው፡፡

ምሽት ላይ ከሺሕ በላይ እንግዶች በታደሙበት ለንግሥቲቱ ክብር በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የግብር አዳራሽ በታላቁ ሲደገስ ለባሕር ማዶ እንግዶቹም በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥትም ተደግሷል፡፡

በማግስቱ ንጉሠ ንግሥቱና ንግሥቲቱ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት ባህላዊ ገጽታን የሚያሳዩ አካባቢዎችን መጎብኘት የጀመሩት ጢስ ዓባይን በመመልከት ነበር፡፡

የላሊበላን አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት እንዲሁም የጥንታዊቷንና የዘውዳዊ ሥርወ መንግሥት መነሻ የሆነችውን አክሱም ከተማ ሐውልቶቹን ብቻ አልጎበኙም፡፡ በትግራይ ጠቅላይ ገዢ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም አማካይነትም በዚያው ዓመት የተመረቀው የአክሱም ጽዮን ማርያም አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን (ሴቶች ጭምር የሚገቡበት) ጎብኝተዋል፡፡

በአስመራ ከተማ በሚገኘው ዮሐንስ 4ኛ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እንደደረሱም በሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ክብር አቀባበል ያደረጉላቸው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ገዢ ልዑል አስራተ ካሳ ናቸው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የከተማው ነዋሪ ካደባባይ ወጥቶ ተቀብሏቸዋል፡፡

ለሰባት አሠርታት የዘለቀው ንግሥና

የንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊት ረዥሙ የ70 ዓመታት የንግሥና ዘመን ጠንካራ በሆነ የኃላፊነት መንፈስ ሕይወታቸውን ለዘውድና ለሕዝባቸው በመስጠት የሚገለጽ ነው ያለው ቢቢሲ የዜና ማሠራጫ ነው፡፡

ጳጉሜን 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ዜና ዕረፍታቸው የተሰማው ንግሥቲቱ የተወለዱት ሚያዝያ 13 ቀን 1918 ዓ.ም. ሲሆኑ፣ የአባታቸው የንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ሁለተኛ ልጅ ነበሩ፡፡ ንጉሥ ጆርጅ (ኪንግ ጆርጅ) ለኢትዮጵያና ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተለይ ፋሺስት ጣሊያንን ካገር ለማስወጣት ላደረጉት ድጋፍ በአዲስ አበባ ወደ ስድስት ኪሎ የሚወስደው መንገድ በስማቸው መሰየሙ ይታወቃል፡፡

ኪንግ ጆርጅ የሚባል ሆቴልም በፒያሳ ነበር፡፡ ንግሥት ኤልሳቤጥ ከባለቤታቸው የኤደንብራ መስፍን ከሆኑት የወለዷቸው የበኩር ልጃቸው አሁን ዘውድ የጫኑት ንጉሥ ቻርልስና ልዕልት አን ይጠቀሳሉ፡፡

በ1969 ዓ.ም. የነገሡበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ባከበሩ በሁለተኛው ዓመት የመጀመርያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ማርጋሬት ታቸር ነበሩ፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ በርዕሰ ብሔሯና በርዕሰ መንግሥቷ መካከል የነበረው ግንኙነት አንዳንዴ በውጥረት የታጀበ ነበር፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ለሚታገሉላቸው ዓላማዎችም አዛኝ የነበሩት ንግሥት ኤልሳቤጥ ከታቸር ጋር እንዳይግባቡ ካደረጓቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የደቡብ አፍሪካውን የአፓርታይድ ሥርዓት በመቃወም ማዕቀብ ለመጣል ያለመፈለጋቸው ነበር፡፡

ንግሥት ኤልሳቤጥ ከልዕልትነታቸው ጀምሮ አፍሪካን መጎብኘት የጀመሩት በሰባ ዓመት ንግሥናቸውም ከ20 በላይ የአፍሪካ አገሮችን አዳርሰዋል፡፡

በቀናት ውስጥ ሥርዓተ ቀብራቸው የሚፈጸመው ንግሥቲቱን ለመሰናበት ትናንትና ሰኞ ከሃያ ሺሕ በላይ የሚቀጠሩ ሰዎች 1.6 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሠልፍ ይዘው ይጠብቁ እንደነበር ቢቢሲ ከስፍራው ዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...