Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የአዋጭነት ጥናት ጨረታ ወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድን ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት የሚያደርጉ ድርጅቶችን የሚጋብዝ ዓለም አቀፍ የፍላጎት ማሳወቂያ ጨረታ አወጣ፡፡

በሚኒስቴሩ የወጣው የፍላጎት ማሳወቂያ ጨረታ መንግሥት በአገር ውስጥ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን መጠን የብረት ውጤት የማምረት አቅም ያላቸውን ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችል የቴክኒካዊና በኢኮኖሚ የአዋጭነት ጥናት የሚያደርጉ ብቃቱና ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተናጠልም ሆነ ኅብረት ፈጥረው መሳተፍ እንዲችሉ የሚጋብዝ  ነው፡፡

የአዋጭነት ጥናቱ ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ የብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካዎችን በአማካሪው በሚወሰን ተስማሚ በሆነ ቦታ ለማቋቋም የሚደረገውን የአዋጭነት ጥናት የሚመለከት ሲሆን፣ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች የሚያደርጉት ጥናት ሦስት ጉዳዮችን የሚሸፍን መሆኑን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረበው መሥፈርት ያስረዳል፡፡ የመጀመሪያው ቴክኒካዊ አዋጭነትን ማጥናት ነው፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊና የፋይናንስ ግምገማ ማድረግ፣ እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማና ቅነሳ ግምገማዎች ሌሎች በጥናቱ የሚሸፈኑ ናቸው ይላል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የአማካሪ ኩባንያዎቹ ምርጫ ሒደት የሚመራው በኢትዮጵያ ባሉ ሕጎች ነው፡፡ እነዚህም የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001፣ እንዲሁም በ2002 ዓ.ም. የወጡ የፌዴራል የመንግሥት ግዥ መመርያዎች ናቸው፡፡

በፍላጎት ማሳወቂያ እንዲሳተፉ የተጋበዙ አማካሪዎች የሚመሩባቸው የተለያዩ ድንጋጌዎች፣ የግምገማ መሥፈርቶች፣ የሥራ ቆይታ፣ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በጨረታ ሰነዱ መሥፈርት መሠረት መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የአዋጭ ጥናት ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች በሁለት ሳምንት ውስጥ መልሳቸውን እንዲያሳውቁ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት አስቀድሞ በኢትዮጵያ ደቡብ ምሥራቅ ክፍል በኦጋዴን ቤዚን በጥናትና በቁፋሮ የተገኘውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ለኢንቨስትመንት ጥቅም እንዲውል፣ ከአሜሪካው ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሼትስ ኢንክ ኩባንያ የአራት ወራት ጥናት የሀብት መጠን ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መረከቡ ይታወሳል፡፡

የአሜሪካው ኩባንያ ለአራት ወራት ባደረገው ጥናት ለሀብቱ መጠን ማረጋገጫ በመስጠቱ፣ መንግሥት ሰርቲፊኬቱን በመያዝ ‹‹ልምድ፣ የፋይናንስና ቴክኖሎጂ ሀብት አላቸው›› የሚላቸውን ኩብንያዎች በራሱ እንደሚያፈላልግ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ገልጸው ነበር፡፡

በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. በዱከምና በቢሾፍቱ ከተሞች የሚገኙ በብረታ ብረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን እንቅስቃሴ የጎበኙት ታከለ (ኢንጂነር)፣ በብረት ምርት ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግን ጨምሮ ከጥሬ ዕቃ አንስቶ በአገር ውስጥ እንዲመረት የማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለው፣ ከውጭ የሚገባውን ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ምርት መጠን የመቀነስ ዕቅድ መያዙን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች